ዋዜማ ራዲዮ- በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረውና እና ታስረው በነበሩ ግለሰቦች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈፅመዋል የተባሉ 33 የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ባለሞያዎች፣ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች እና የማረሚያ ቤቶች ሀላፊዎች ታስረው በህግ ጥላ ስር እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

የፖሊስ ምርመራ ካበቃ በኋላም አቃቤ ህግ በሶስት ምድብ ከፍሏቸዋል፡፡
ከነዚህ ውስጥ 15ቱ የደህንነት የቀድሞ አባላት ለየብቻ መዝገብ ከተከፈተባቸው የቀድሞ የስራ ሂደት ሀላፊዎቻቸው አቶ ያሬድ ዘሪሁንና አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ጋር በአንድ ላይ በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀዳሚ ምርመራ ምስክር ተሰምቶ አልቆ ክስ በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡
የፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች የነበሩት አስሩ ደግሞ በልደታ ምድብ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የክስ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡

ቀሪዎቹ ስምንት የማረሚያ ቤት አስተዳደር የቀድሞ ሀላፊዎች ደግሞ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ በቀጠሮ ተገኝተዋል፡፡

የካቲት 12 ቀን 2011 ዓም የክስ መዝገብ የተከፈተባቸው ተከሳሾቹ የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያቸውን ከዚህ ቀደም በፅሁፍ በጠበቃቸው በኩል አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህ መዝገብ የተጠቃለሉት ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ፣ሱፐር ኢንተንደንት አስገለ ወልደጊዮርጊስ፣ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ፣ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ገብረእግዚአብሔር ገብረሀዋርያት፣ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ተክላይ ሀይሉ ፣ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አቡ ግርማ ፣ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አዳነ ሀጎስ እና ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ገብራት መኮንን የተባሉት ተከሳሾች የቂሊንጦ ፣የዝዋይ እና ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤቶች የቀድሞ የስራ ሀላፊዎች የነበሩ ናቸው፡፡

ነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ በፌደራል ማረሚያ ቤት የቂሊንጦ ማረፊያ ቤት ላይ ተከስቶ የነበረውን እሳት አደጋ ተከትሎ ታዲያ እሳቱን አስነስተዋል ተብለው የተጠረጠሩት እስረኞችን ወደ ሸዋሮቢት ተሀድሶ ልማት ማረሚያ ቤት በመውሰድ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈፀሙ መሆኑን እና ሰኔ 11 2009 በቂሊንጦ ተፈጠሮ የነበረውን ግጭት ተከትሎ ደግሞ 20 የሚሆኑ እስረኞችን ወደ ዘዋይ በመወሰድ የተለያዩ ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶችን እንደፈፀሙባቸው የአቃቤ ህግ ክስ ገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎም ለከባድ የአካል ጉዳት እና ለህልፈተ ህይወት መንስዔ ሆነዋል በማለት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የእያንዳንዱን ተከሳሽ ወንጀል በተናጠል ዘርዝሮ በክሱ አካቶ ነበር፡፡
በዚህ መቃወሚያ ላይ ዛሬ የአቃቤ ህግን ምላሽ በፅሁፍ ለመቀበል የተቀጠረ ሲሆን ክሱ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በህመም ምክኒያት ችሎት ተገኝተው የማያውቁት 2ኛ ተከሳሽ ዛሬ እንዲቀርቡም ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡

የመቃወሚያው ምላሽ ላይም ተከሳሾች ድርጊቱን ለመፈፀም የሚያስችል የስራ ሀላፊነት አልነበረንም ያሉትን መቃወሚያ በማንሳት ሀላፊነታቸው በማስረጃ ዝርዝር ላይ በግልፅ ያስቀመጠን በመሆኑ የተከሳሾች ክርክር ማስረጃ ስናሰማ የሚረጋገጥ ነው ስለዚህም ውድቅ መሆን አለበት በማለት በፅሁፍ አስቀምጧል፡፡

በተጨማሪም ዋና ወንጀል አድራጊ መሆናቸውን በበቂ እና ግልፅ ሁኔታ ያስቀመጥን በመሆኑ ወንጀሉ የተፈፀመው ስራችንን ለመስራት በሚል እንጂ አስበን ሰው ለመጉዳት አይደለም የሚሉትን የተከሳሾች መቃወሚያ የማስረጃ ክርክር እንጂ የመጀመርያ መቃወሚያ ላይ የሚቀርብ አይደለም ብሏል፡፡
ሌላኛው አቃቤ ህግ ምላሽ የሰጠበት የተከሳሾች መቃወሚያ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 423 እና 424 መሰረት እንጂ አሁን በቀረበብን አይደለም የሚለውን ነው፡፡

በዚህ ላይ እነዚህ ሁለት የህግ ድንጋጌዎች የሚጠቀሱት በምርመራ ወቅት ታሳሪው ጥፋቱን በግድ እንዲያምን ለማስገደድ የሚደረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተገናኘ የወንጀል ድርጊት ነው ብሏል፡፡ ተከሳሾቹ አሁን ፈፀሙ የተባለው የወንጀል ድርጊት ግን ከዚህ ጋር በፍፁም የማይገናኝ በመሆኑ እነዚህ አንቀፆች የሚደረጉበት ምንም መሰረት የለውምና ውድቅ ይደረግልኝ ብሏል፡፡
ችሎቱ ከዚህ ቀደም በቀረበው የተከሳሾች የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ እና የአቃቤ ህግ መልስ ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 19 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ችሎቱ ያስተናገደው ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ክስ ከተመሰረተበት ቀን ጀምሮ በችሎት ተገኝተው መከታተል ያቻሉትን 2ኛ ተከሳሽ ሱፐር ኢንተንደንት አስገለ ወልደ ጊዮርጊስ ጉዳይ ነበር፡፡
እስካሁን በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ተከሳሹ ዛሬ በችሎት ሲቀርቡ በዊልቼር ነበር የመጡት፡፡
እስካሁን በህመም ምክኒያት መቅረብ እንዳልቻሉ ለችሎቱ ካስረዱ በኋላ በሁለተኛ ዳኛ አማካኝነት ዘግይቶም ቢሆን ክሱ ተነቦላቸዋል፡፡

የ8ቱንም ጉዳይ የያዙት ጠበቃቸው ክሱ ከተነበበ በኋላ ከዚህ በፊት ለሌሎቹ በገባው የክስ መቃወሚያ ተጠቃሎ ለእሳቸውም እንዲያዝላቸው ከተናገሩ በኋላ የመብት ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ምንም እንኳን ክሱ በተመሰረተበት ወቅት የዋስትና መብት የተከለከለ ቢሆንም ደምበኛዬ ካሉበት ከባድ ሁኔታ አንፃር የዋስትና መብት ይፈቀድላቸው በማለት ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሹም በበኩላቸው በእስር ላይ እያሉ ይሄ የጤና እክል እንደገጠማቸው ለችሎቱ የገለፁ ሲሆን ከፖሊስ ሆስፒታል ወደ ጥቁር አንበሳ እንዲዘዋወሩ እንደተደረገ እና ሽንትም ሆነ ሰገራ መቆጣጠር አቅቷቸው በካቴተር እየተየቀሙ መሆኑን ለችሎቱ የለበሱትን ገልፀው በማሳየት አስረድተዋል፡፡
የተባለውን ድርጊት አለመፈፀማቸውን በመጥቀስም ለረጅም አመታት ለሀገር ያገለገሉ መሆኑን እና የጤና ሁኔታቸው ከግምት ገብቶ ዋስትና እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዳኞችም በተባለው ጉዳይ ላይ አቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥበት ባዘዙት መሰረት የተመሰረተው ክስ ላይ ያሉት አንቀፆች የዋስትና መብትን የሚያስከለክሉ ናቸው በማለት የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡
አክሎም የፌደራል ማረሚያ ቤት እንደሂህ አይነት ልዩ ክትትል የሚያስፈልጋቸው እስረኞች ሲኖሩ ሀኪም እና አስታማሚ መድቦ የሚያሰራበት ልዩ አሰራር ያው በመሆኑ ያንን እንዲያቀርብላቸው ታዞ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩና ክሳቸውን እንዲከታተሉ ይደረግልን ብሏል፡፡

ችሎቱም ለማረሚያ ቤት ተወካዮች ተከሳሽ ማለት ወንጀሉን ስለመፈፀሙ በማስረጃ እና በምስክር እስኪረጋገጥ ድረስ ጥፋተኛ አይደለም ብለው በመምከር ያለምንም አድሎ ተከሳሹን እንዲንከባከቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ የዋስትናውን ጥያቄ በተመለከተ ደግሞ መርምሮ ለመወሰን ለቀጣይ ቀጠሮ ቀን ማለትም መጋቢት 19 ጠዋት ቀጥረዋል፡፡

ችሎቱ ከማብቃቱ በፊት ግን ተከሳሾቹ ጠዋት እዚህ ችሎት ስንመጣ ሌሎች ባለጉዳዮም ስድብ እና ዛቻ እየደረሰብን በመሆኑ ችሎቱ የኛን ጉዳይ ከሰዓት ይይልን ብለው ነበር፡፡

ሆኖም ይህ ነፃ ችሎት ነው እነሱ የመንግስት ባለስልጣን በመሆናቸው ጉዳያቸው ተለይቶ ታየ ተብለን መታማት የለብንም ልክ እንደሌላው ሁሉ የእናንተም ጉዳይ በጠዋት ችሎት ነው የሚታየው በማለት ዳኞች ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]