PM Abiy Ahmed

ዋዜማ ራዲዮ- በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተጋጋመው ጦርነት እያስከተለ ያለው የኢኮኖሚ ጫና ምልክቶቹ እዚህም እዚያም መታየት ጀምረዋል። ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ለጋሾች ድጋፍ ማቋረጥ ጀምረዋል። አሜሪካ ለሀገራችን የሰጠችውን የቀረጥ ነፃ መብት ለመሰረዝ ከጫፍ ደርሳለች። የውጪ ባለሀብቶች ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አዳዲስ መዋለ ነዋይ ለማፍሰስ ፈቃደኛ አይደሉም። በዚህ ሁሉ ጫና መካከል መንግስት በተያዘው አመት ሊያሳካቸው ያሰባቸው ግዙፍ ዕቅዶች አሉ። ዋዜማ የመንግስትን ዝርዝር የዕቅድ ሰነድ ተመልክታ የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅታለች። አንብቡት

በፕላንና ልማት ኮሚሽን የተሰናዳው ይህ ሰነድ “የ2014 በጀት አመት ሀገራዊ የልማት እቅድ” ላይ የ2013 በጀት አመት እና የሶስት አመቱ የ”ሀገር በቀል” የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንደ መነሻ ተቀምጠዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ እቅድ በሚለው ንኡስ ክፍል ውስጥም የ2014 አ.ም አጠቃላይ የመንግስት ወጪ 732.2 ቢሊየን ብር እንደሆና ጠቅላላ የመንግስት ገቢ ደግሞ 600.9 ቢሊየን ብር እንደሚሆን አስቀምጧል። ከመንግስት ገቢ ውስጥ 83 በመቶው ከታክስ የሚገኝ ሲሆን ገቢው በእቅዱ ልክ እንዲሆን የታክስ ህጎችና ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያዎች እንደሚተገበሩ ሰነዱ ያስረዳል።በገቢም በወጪም ረገድ ካለፈው አመት አንጻር በዚህ አመት ከእጥፍ በላይ አፈጻጸሞች ይጠበቃሉ ።


በእቅድ አመቱ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ; ከውጭ ኢንቨስትመንት ፣በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውን ከሚልኩትና ከቱሪዝም በድምሩ ከ23 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የመንግስት የዚህ በጀት አመት እቅድ ዋና አካል ነው። ከዚህ ውስጥ 5.25 ቢሊየን ዶላር ከሸቀጦች የወጪ ንግድ እንዲገኝ የታሰበ መጠን ነው። ካለፈው በጀት አመት አንጻር ከ1.6 ቢሊየን ዶላር በላይ ብልጫ እንዲኖረው ተፈልጓል።

ግብርና ፣ ኢንዱስትሪና የማዕድን ዘርፎች ለገቢው የላቀ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ታምኗል። መንግስት በሪከርድነት ለመዘገበው የባለፈው አመት የውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቁን ድርሻ የወሰደው ማዕድን ፣ ከማዕድንም የወርቅ የወጪ ንግድ መሆኑ ይታወሳል። ዘንድሮም አጠቃላይ ከወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ ከታሰበው 5.25 ቢሊየን የውጭ ምንዛሬ ውስጥ ማዕድን ብቻውን 1.3 ቢሊየን ዶላር ያስገኛል ተብሎ በእቅዱ ተስፋ ተጥሎበታል።

የውጭ ኢንቨስትመንት ከ2013 በጀት አመት የ2 ቢሊየን ዶላር ብልጫ ኖሮት 6 ቢሊየን ዶላር እንዲያስገባ ፣ በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚልኩት ምንዛሬ ደግሞ 5 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ አለ። ዕቅዱ ካለፈው አመት ጋር ተቀራራቢ ነው።


ቱሪዝም ከሁሉም የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ዘርፎች ትልቁ ግብ የተጣለበት ነው ፣ ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች ብቻ 7.12 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲገኝ በእቅድ ተይዟል። ይህን ለማሳካት 2.14 ሚሊየን ቱሪስቶች ሀገራችንን መጎብኘት አለባቸው። ባለፈው አመት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር 200 ሺህ ብቻ ናቸው። ለቁጥሩ መውረድ የኮሮና ቫይረስና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። ዘንድሮ ከሁለት ሚሊየን በላይ የውጭ ጎብኝዎች ከውጭ ይመጣሉ ተብሎ ሲጠበቅም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ጥረት ይደረጋል ቢባል እንኳ የሰሜኑ ጦርነት ላይ ግልጽ መቋጫ እየታየ ባለመሆኑ የሚጠበቀውን ቁጥር የተጋነነ አስመስሎታል።


በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ አዳዲስ ይከፈታሉ ተብለው በሚጠበቁ ከ3 ሺህ በላይ ፋብሪካዎች ለበርካቶች ስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል።አጠቃላይ የሰብል ምርትን 2013 አ.ም ከነበረበት 543 ሚሊየን ኩንታል በዚህ አመት ወደ 593 ሚሊየን ኩንታል ማሳደግም የአመቱ የልማት እቅድ አካል ነው።


በከተማ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ 400 ሺህ ቤቶች በዚህ አመት እንዲገነቡ ግብ ተቀምጧል። ቤቶቹ በግል ፣ በሪልስቴት ኩባንያዎችና በመንግስት በጥምረት የሚገነቡ እንደሆነ ሰነዱ ይጠቁማል። ተቋራጮች እያጋጠማቸው ካለው ችግርና ከመንግስት የመፈጸም አቅም አንጻር ቤቶች ላይ የተጣለው ግብ የተጋጋነ መስሏል። ባለፈው አመት እንኳ የአዲስ አበባ ቤት አቅርቦት ቢታይ ይህ ነው የሚባል የጋራ መኖርያ ቤቶች ግንባታ ስኬት አልተመዘገበም።በዚያው አመት 350 ሺህ ቤቶችን በሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች ለመገንባት ታቅዶ ነበር። የአፈጻጸም ሪፖርቱ ግን ባለመጠናቀቁ በእቅድ ሰነዱ አልተካተተም። [ዋዜማ ራዲዮ]