PM Abiy Ahmed and IMF Director Kristalina Georgieva

ዋዜማ ሬዲዮ: አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ በየሁለት አመቱ በሚያወጣው የአለም ኢኮኖሚ ምልከታ ሪፖርት ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) ትንበያ ሳያካትት ቀርቷል፡፡


ይህ ክስተት በበርካታ ጫና ውስጥ ላለው የሀገራችን ኢኮኖሚ መልካም ዜና አይደለም። ኢትዮጵያ በትንበያው ያልተካተተችው በትግራዩ ጦርነት ሳቢያ ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር ለገባችበት ውዝግብ ጫና ለማሳደር ነው ብለው የሚያምኑ ባለሙያዎች አሉ። የዓለም ባንክ መስራች የሆነችው ሀገራችን ከትንበያው መገለሏ በእርግጥ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አለውን? ባለሙያዎች አነጋግረናል።


ከታች ያያዝነው የድምፅ ዘገባ ደግሞ የሌሎች ባለሙያዎችን አስተያየትና ትንታኔ አካቷል። አድምጡት


የሁሉንም የአለም አገራት የአገር ውስጥ የምርት እድገት ትንበያ ባሳለፍነው ሳምንት ያወጣው ተቋሙ የኢትዮጵያን ያላካተተበት ምክኒያት ትንበያውን ለማድረግ የሚያዳግቱ ያልተረጋገጡ ነገሮች እንዳሉ ብቻ ነበር የጠቆመው፡፡


ምንም እንኳን ሀገራት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የየራሳቸውን የሀገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) እየሰሩ ይፋ ቢያደርጉም እንደ አይ ኤም ኤፍ ያሉ አለም አቀፍ ተቋማት የሚያወጡት ትንበያ በአንዲት ሀገር ቀጣይ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ቦታ ያለው ነው፡፡


ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ የሆኑት አቶ ጌታቸው አስፋው በበኩላቸው “እኛ የራሳችንን ጂዲፒ በፕላን ኮሚሽን አማካኝነት ሰርተን ይፋ ብናደርግም ማን ያምነናል? ከእኛ ይልቅ የአለም አቀፍ ሪፖርቶችን ነው መመልከት የሚፈልጉት፡፡” ይላሉ፡፡
አክለውም “አይ ኤም ኤፍ አሁን ሀገሪቷ ውስጥ ባለው ሁኔታ እና በጦርነቱ ምክኒያት ትንበያውን ማድረግ አልቻልንም ሊል ይችላል ነገር ግን ትንበያ እስከሆነ ድረስ እነዛ ነገሮች ከግምት ውስጥ ገብተው መውጣት ይችል ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ በዚህ ሪፖረት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሁኔታ አለመተንበዩ በተለያየ መንገድ ሊጎዳን ይችላል”


“ አንዱ ሙዋለ ነዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ላይ የሚፈጥረው የአለመተመማን ስሜት ነው፡፡ እንዲህ መሆኑ የሀገሪቱን የወደፊት የንግድ እንቅስቃሴ መተንበይ ስለሚዳግት የውጭ ኢንቨስተሮች ከመምጣት ሊቆጠቡ ይችላሉ፡፡” ይላሉ አቶ ጌታቸው ።


“ባለሀብቶችን የሚያሸሸው ጂዲፒ አለመተንበዩ ብቻ አይደለም” የሚሉት ሌላኛው ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ዶ/ር አጥላው አለሙ በበኩላቸው አይኤም ኤፍ ከሚያወጣው ሪፖርት በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ነገሮች እንደሚጠኑ ያስረዳሉ።

“ይህቺ ሀገር ሙዋለ ነዋይ ለማፍሰስ ታዋጣለች ወይ? የሚለውንም ያያሉ፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያ እንኳን ለኢንቨስትመንት ለመጎብኘትም አዳጋች የሆነ ሁኔታ ውስጥ ነች፡፡” ይላሉ፡፡


ከዚህ በተጨማሪ የአይኤምኤፍ ሪፖርት ኢትዮጵያን አለማካተት በአበዳሪዎች ዘንድ የሚኖረውን ምልከታም ሊቀይር እንደሚችል ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡


“በእርግጥ አበዳሪዎች የሚያዩት ብደር የመክፈል አቅምን ነው፡፡ ነገር ግን እሱን ለመመርመርም ሀገሪቱ የተጠራቀመባትን ውጭ እዳ ከሀገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) ጋር ነው የሚያወዳድሩት፡፡ ጂ ዲፒ ከሌለ ከምን ጋር ያወዳድሩታል? የድህነት ቅንሳው ፣የኑሮ ምጣኔው፣ የነፍስ ወከፍ ገቢው ሁሉ የሚሰራው ጂዲፒ ላይ ተንተርሶ ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥጥታ ተፅኖ የለውም እንኳን ብንል በተዘዋዋሪ የራሱ ተፅኖ አለው፡፡” ይላሉ አቶ ጌታቸወ፡፡ [ ዋዜማ ሬዲዮ]

ከታች ያያዝነው የድምፅ ዘገባ ደግሞ የሌሎች ባለሙያዎችን አስተያየትና ትንታኔ አካቷል። አድምጡት

https://youtu.be/huVdvzaoLCM