ዋዜማ ራዲዮ- ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በርካታ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን መውሰዳቸው ርግጥ ነው፡፡ በዚያው ልክ ደሞ መንግሥታቸው በሀገር ውስጥ እየተነሱ ያሉ በርካታ ጥያቄዎችን ተስፋ ሰጭ በሆነ ሁኔታ መመለስ አልቻለም፡፡ መንግሥታቸው መዋቅራዊ የሆኑ የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ፍላጎቱ፣ አቅሙ እና ቁጠርኝነቱ አለው ወይ? በሀገር ውስጥ ችግሮችን ሳይቀርፉ በቀጠናዊ ዲፕሎማሲ መጠመዳቸውስ ተገቢ ነውን? የሚሉ ጥያቄዎች ጎልተው እየወጡባቸው ነው፡፡ ቻላቸው ታደሰ ይህን ፅፏል

ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው የሚመሩት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ወዶም ይሁን ተገዶ ወደ አክራሪ ብሄርተኝነት እያዘነበለ ስለመሆኑ አንዳንድ ምልክቶች አሉ፡፡ መቸም ኦዴፓ ሰሞኑን ስለ አዲስ አበባ ባለቤትነት ያወጣው መግለጫ ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ደሞ የኦዴፓ ሊቀመንበር ስለሆኑ ለሚመጣው አደጋ ድርብ ሃላፊነት አለባቸው፡፡

በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት አስጊ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ማለት ይቻላል፡፡ ፍጥጫ እየበረታ ነው፡፡ በተለይ መጭዎቹ ሀገር ዐቀፉ ሕዝብ ቆጠራ፣ የማንነትና ወሰን ማካለል ጥናት እና ሀገር ዐቀፉ ምርጫ የተለያዩ ግጭቶችን እንዳይቀሰቅሱ ከፍተኛ ስጋት አለ፡፡ አማራ እና ትግራይ ክልሎችም ስለ ጦርነት ቃላት መለዋወጣቸው አሳሳቢ ሊያሳስባቸው የሚገባ ችግር ነው፡፡ በቅርቡ በሐይማኖት አባቶች አቀራራቢነት የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች አንድ ጊዜ ከመወያየታቸው ውጭ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደ ጠቅላይ ሚንስትርነታቸው ወይም እንደ ኢሕአዴግ ሊቀመንበርነታቸው የማቀራረብ ሙከራ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡

በተያዘው የፈረንጆች ዐመት ሀገሪቱ 8 ሚሊዮን ተረጅዎች እንደሚኖሯት ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡ መንግሥት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል ይበል እንጅ 2 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ዛሬም በተለያዩ መጠለያዎች ተጠልለው አስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊ እንደሆኑ የተመድ አስቸኳይ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ገልጧል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ ለፋይናንሸል ታይምስ በሰጡት ቃለ ምልልስ 60 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት ባወጣ ዐለም ዐቀፍ አድናቆት ይጎርፍልኛል ብለዋል፡፡ እዚህ ላይ ጥያቄው ሚሊዮኖችን ከድህነት የሚያወጣ ይቅርና እንዲያው በጠቅላላው በጥቅሉ ግልጽ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ አላቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ እስካሁን ይፋ ያደረጉት በመርህ ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የለም፡፡ ሀገሪቱን ለቀውስ የዳረጋትን የሥራ አጥነት ማነቆን የመፍታት ጉዳይም ገና ከምር አልጀመሩትም፡፡

ባጠቃላይ እነዚህና ሌሎች ውስጣዊ ችግሮች ናቸው እንግዲህ የጠቅላይ ሚንስትሩ የትኩረት ቅደም ተከተል ላይ ጥያቄ ያስነሱት፡፡ ጥያቄው ግን ለምን በቀጠናዊ ጉዳዮች ትከኩረት ሰጡ? የሚል አይደለም፤ ውስጣዊ ችግሮችነ ለመፍታት በቂ ጊዜ እና ጉልበት ተጠቅመዋል ወይ? የሚል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በኤርትራ የጀመሩትን የሰላም ጥረት አጠናክረው ቀጥለው በተለይ በቅርቡ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በርካታ ጉብኝቶችን አድርገዋል፡፡ የጎረቤት ሀገራት መሪዎችንም ወደ አዲስ አበባ እየጋበዙ አወያይተዋል፡፡ ስለ ውይይታቸው በይፋ የሚነገረው ቀጠናዊ ሰላምን እና ትብብርን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ነው፡፡

ከሳምንት በፊት ዐቢይ የሱማሊያውን ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፎርማጆን ከሱማሌላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር ፊት ለፊት ለማገናኘት ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ለጊዜው አልተሳካም፡፡ እንደ ታዛቢዎች ዕምነት ከሆነ ፕሬዝዳንት የፊት ለፊት ውይይቱ በሚካሄድበት ቦታ እና በአቀራራቢው ላይ ቀደም ሲል ስምምነት ባለመደረሱ በውይይቱ ለመገኘት አልፈቀዱም፡፡ በርግጥ የሱማሊያ መሪዎች ላለፉት 30 ዐመታት ከራስ ገዝ አስተዳደሯ መሪዎች ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ስለማያውቁ የፊት ለፊት ግንኙነቱና ውይይቱ ቢሳካ ኖሮ ዐቢይ በቀጠናው ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ነጥብ ማስመዝገብ በቻሉ ነበር፡፡ ሙከራቸው ቀደምቶቻቸው ይከተሉት ከነበረው የውጭ ፖሊሲ የተለየ ይመስላል፡፡

በቅርቡ ደሞ ወደ ናይሮቢ ተጉዘው የሱማሊያን እና ኬንያን መሪዎች የማቀራረብ ጥረት አድርገዋል፡፡ ለሦስት ሳምንታት በባሕር ወሰን ይገባኛል ጥያቄ ሲወዛገቡ የነበሩት የሁለቱ ሀገሮች መሪዎችም ፊት ለፊት ተገናኝተው መወያየት ችለዋል፡፡ ያም ሆኖ ዐቢይ የማቀራረብ ሥራውን ሰርተው ይሆናል እንጅ የሁለቱን ሀገሮች ውዝግብ አጢነው አሸማግለዋል የሚያስብል ነገር አልታየበትም፡፡ ሚናውን የተጫወቱት ምናልባት ፕሬዝዳንት ፎርማጆ ወይም ፕሬዝዳንት ኬንያታ በግል ጠይቀዋቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደሞ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ስለሆኑ የራሳቸው ተነሳሽነት ሊሆን ይቻላል፡፡ ከጅምሩም ቅራኔው ያን ያህል የተካረረ አልነበረም፡፡ ጉዳዩ በቀጠናው መገናኛ ብዙኻን ትልቅ ሽፋን ባያገኝም የጠቅላይ ሚንስትሩ ሙከራ ግን ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ አስተዋጽዖ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ኬንያና ሱማሊያ ወደከረረ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ቢገቡ ምናልባት ኬንያ በአሚሶም ሰላም አስከባሪ ስር ሱማሊያ ውስጥ ያሏትን ወታደሮች እንድታስወጣ ምክንያት ሊሆናት ይችላል፡፡ ያ ደሞ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጠናው ጸጥታ አሉታዊ አንድምታ ይኖረው ነበር፡፡

በመሠረቱ ለቀጠናዊ ትብብር እና ሰላም ከመሪዎች ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት እና ፖሊሲ አንጻር ካሁን በፊትም ብዙ ተሂዶበታል፡፡ ምንም እንኳ ተግባራዊነቱ ወደኋላ ቢጓተትም ቅሉ… ቀጠናዊ ትብብር ተቋማዊ መሠረት ካልያዘ ደሞ ሀገራቱን አይጠቅምም፡፡ ችግሩ ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለቀጠናዊ ትብብር የሚያግዝ አዲስ በይነ-መንግሥታዊና ተቋማዊ አሰራር ገና አልታየም፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የደረሰችው የሰላም ስምምነት እና ንግድ ትስስርም ቢሆን ገና በመሪዎቹ ብቻ ተንጠልጥሎ ያለ እንጅ ተቋማዊ መሠረት አልያዘም፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ቁም ነገሩ ሀገሪቱ ካለችበት ቅርቃር አንጻር ቀጠናዊ ትብብርን ማቀላጠፍ የዐቢይ ተቀዳሚ ትኩረት መሆን አለበት ወይ? የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምስ የቱ ነው- ውስጣዊ ሰላምን እና ሀገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ከውስጥ ወደ ውጭ መመልከት ወይስ ከቀጠናዊ ትብብር ጀምሮ ወደ ውስጥ ማየት? የሀገር ውስጡ ችግርስ ከቀጠናው ጋር ምን ያህል ጥብቅ ትስስር አለው? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግር በዋናነት ውስጣዊ ችግር እንጅ ከቀጠናው ጋር የተያያዘ ውጫዊ ችግር አይደለም፡፡ መፍትሄውም በዋናነት ሀገር በቀል የፖለቲካና ኢኮኖሚ መፍትሄ ነው፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ገዥ መርህ ደሞ ከውስጥ ወደ ውጭ በማየት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ መንግሥት በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞች ሁሉ በማንኛውም ቦታ የመንቀሳቀስ እና ሥራ የመስራት መብት ሲሰጥ ትችት የቀረበበት ውሳታ ከዐለም ዐቀፍ ሕግጋት አንጻር መጥፎ ሆኖ ሳይሆን መጀመሪያ የሕዝቡን ሰላም እና የመንቀሳቀስ መብት ማስከበር ነበረበት ከሚል መነሻ ነበር፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ለቀጠናዊ ትብብር ግልጽና ሁሉን ዐቀፍ የሆነ ፖሊሲ የሌለው መሆኑም ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ከወራት በፊት በጎረቤት ሀገሮች ጠንካራና አንጋፋ አምባሳደሮች እንደሚሾሙ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም በተግባር ግን እምብዛም ለውጥ አልታየም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩም ዲፕሎማሲን የሚመሩበት መንገድ ያልተለመደ እና ኢመደበኛ መሆኑም ጥንቃቄ የሚፈልግ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አንድ ቀን ሳት ካለ ያልተታሰበ የዲፕሎማሲ አደጋ ሊጋብዝ ይችላል፡፡

ሀገራቱ ስለ ቀጠናዊ ትብብር ሲሰብኩ የየራሳቸውን ፍላጎት በጉያቸው ደብቀው እንደሆነም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ላይ ቀጠናው ተለዋዋጭ የውጭና የውስጥ ጅኦፖለቲካዊ ፍላጎቶችንና የሃይል አሰላለፎች የሚስተናገዱበት ቀጠና ነው፡፡ ጅኦፖለቲካዊ ለውጦቹ የወደብ አልባዋን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ደኅንነትና ጥቅም የሚፈታተኑ እንደሆነም መረሳት የለበትም፡፡ ኢጋድ በቀይ ባሕር አካባቢ ባለው ጅኦፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የጋራ አቋም የያዘው እንኳ ገና በቅርቡ ነው፡፡ ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህም ቀጠናው ገና ውሉ ባልለየለት ሽግግር ውስጥ እያለፈ እንጅ ለዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ምቹ ሆኗል ማለት አይቻልም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ የሀገሪቱን የውስጥ ችግሮች አንዳንዴ አቅልለው ቢያቀርቧቸውም የቀጠናው ሀገሮች ግን በአጽንዖት እየተከታተሏቸው እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ አለመረጋጋት በተናጥልም ሆነ ቀጠናውን በጠቅላላው ወደ አዘቅጥ ውስጥ እንደሚከተው ጠንቅቀው ያውቃሉና፡፡ ሀገራችንም ከጎረቤት ሀገሮች ከሚመጡ ስጋቶች ራሷን መጠበቅ የምትችለው ውስጣዊ ድክመቶቿን ፈትታ ተጋላጭነቷን ስትቀንስ ብቻ ይሆናል፡፡

ባጭሩ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለቀጠናዊ ትብብር እና ውህደት ከመኳተናቸው በፊት የሀገራቸውን ምጣኔ ሃብት ለማሳደግ፣ መዋቅራዊ ፖለቲካዊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት እና ሰላም ለማስፈን ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚፈልጉ ወገኖች በርካቶች ናቸው ፡፡ የቀጠናዊ ትብብርና ጸጥታ ዙሪያ የሚደረግ ዲፕሎማሲ ውጤት በዋናነት ሊለካ የሚችለው ከሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም አንጻር ብቻ መሆን እንዳለበት የሚያከራክር አይደለም፡፡ የዲፕሎማሲው ገዥ መርህ ይሄው ሀገራዊ ብሄራዊ ጥቅም ነው፡፡ እሱን ያላስቀደመ ማንኛውም ዲፕሎማሲ፣ የውጭ ፖሊሲ እና ስምምነት ተቀባይነት ሊኖረውም አይችልም፡፡ በቀጠናው ሀገሮች ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊም ምንም እንኳ መሠረታዊ ችግሮችን ባይፈቱም ቅሉ ዋና ትኩረታቸው ግን ሀገር ውስጥ ላይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ] 

https://youtu.be/tSmlntpMKUA