Cereal marketበየካቲት ወር የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው በ8.7 በመቶ ከፍ ማለቱን ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የወጣ መረጃ አመለከተ፡፡

ኤጀንሲው በየወሩ የሚያወጣው የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ እንደሚያሳየው የየካቲት ወር 2008 ዓ.ም የምግብ ዋጋ ግሽበት በየካቲት 2007 ዓ.ም ጋር ከተመዘገበው በ9.2 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በወሩ ውስጥ በምግብ ክፍሎች በተለይም በእህል ዋጋ ላይ መጠነኛ ቅናሽ ቢታይም ምግብ ነክ ባልሆኑ ዘርፎች ላይ ያለው ግሽበት በ8.2 በመቶ መጨመሩን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

“ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በጫት፣ በልብስና መጫሚያ፣ በኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ የማገዶ እንጨት፣ የቤት ዕቃዎችና ማስጌጫዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው” ሲል የኤንጀሲው ሪፖርት ያብራራል፡፡

በዋጋ ግሽበቱ ላይ የታየው ለውጥ “ለኑሮ የሚያስፈልግ ወጪ መጨመርን ያመላክታል” ሲል የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ሰኞ መጋቢት 12 ባወጣው ሳምንታዊ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ የቢሮውን ሪፖርት ባለሙያዎችም ይጋሩታል፡፡ በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ለጭማሪው አስተዋጽኦ እንዳለውም ይናገራሉ፡፡

“እኒህ ቁጥሮች ዋጋ እየተወደደ እንደመጣ የሚያሳዩ ናቸው” ይላል በልማት ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ኢኮኖሚስት፡፡ “”በድርቁ ምክንያት ለምግብ የሚውሉ ጥራጥሬዎች አቅርቦት ስለሚቀንስ የምግብ ዋጋ በመጪዎቹ ወራት በተለይም በሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል፡፡

ከ1998 ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም ያለው አማካይ የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት 17.73 በመቶ እንደሆነ ቁጥሮች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ በከፍተኛነት የሚጠራው የ64.20 በመቶ የዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በሚሊኒየሙ መጀመሪያ በሐምሌ 2000 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ዝቅተኛው -4.10 በመቶ ደግሞ በመስከረም 2002 ዓ.ም እንደነበር “ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ” ከተሰኘው ድርጅት የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡