AAU gateየአገር ፖለቲካ ትኩሳት መገንፈያ ስድስት ኪሎ ዙፋን ከመነቅነቅ ጀምሮ ንጉስ እስከመገልበጥ፣ ደርግንም እሰከ ማርበድበድ፣ የኢህአዴግም እራስ ምታት ከመሆን ተመልሶ አያውቅም፡፡
ከ1993 የተማሪ ግርግር በኃላ በስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ በመንግስት ላይ ይህ ነው ሚባል የተማሪዎች ጥያቄ እንዳይፈጠር እና እንዳይታሰብ በዩንቨርስቲው ተማሪ ውስጥ እና በዩኒቨርሰቲው ማህበረሰብ ብርቱ የመሰነጣጠቅ እና የደህንነት ስራዎችን በስኬት የተጎናፀፈው መንግስት በዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ የሚካሄዱ ማናቸውንም የመማር እና ማስተማር አካል የሆኑ ተግባራት ለደህንነት ስጋት ያላቸው ሚና ተፈትሾ ነው ይሁንታ የሚያገኙት፡፡

በዩኒቨርስቲው በየዓመቱ የሚከናወነው አመታዊ የመፀሐፍ አወደ ርዕይም ከዚህ የደህንነት ስጋት እይታ አላመለጠም፡፡ በተለየዩ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በአውደ ርዕዩ መፀሐፎቻቸውን ለሽያጭ እንዲያቀርቡ ተሳታፊዎች እንዲገኙ በተደጋጋሚ ግብዣ የተደረገላቸው ቢሆንም እስከ አርብ መጋቢት 23 ቀን ድረስ ግን የት እንደሚደረግ ሳይነገር ቆይቷል፡፡

እንደዋዜማ ምንጮች ከሆነ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች አውደ ርዕዩን አስታከው ግርግር ሊፈጥሩ ይችላሉ በሚል የደህንነት ስጋት አውደ ርዕዩ ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውጪ እንዲደርግ ተወስኗል፡፡ በሌሎች የዩኒቨርስቲው ግቢዎች የተማሪዎች ግርግር እና ጥያቄ እምብዛም ስላተልመደ አምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ለዚህ ስራ ታጭቷል፡፡
አስር ቀናት የሚቆየው የመፀሐፍ አውደ ርዕዩ የአስር አመት የስድስት ኪሎ ቆይታው አብቅቶ ዘንድሮ በአምስት ኪሎ የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ይዘጋጃል፡፡

ሰኞ መጋቢት 26 ተጀምሮ እሰከ ሚያዚያ 2 የሚቆየው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የመፀሐፍ አውደ ርዕይ በከተማዋ የጠፉ አሮጌ መፀሐፍቶችን ይሁን አዳዲስ መፀሐፍቶች ለመሸመት ሁነኛ አጋጣሚ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል፡፡

ወደ 70 የመፀሐፍ ሻጮችን በአንድነት የሚገኙበት  አውደ ርዕዩ- በጎብኚዎችም ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ ብቸኛ በከተማዋ አስር አመታት መዝለቅ የቻለ የመፀሐፍ አውደ ርዕይ ስለመሆኑ የመፀሐፍት ሻጮችም ይመሰክሉ፡፡ በተለይ ዩንቨርስቲው የሚያሳትማቸው የተለያዩ የታሪክ መፀሐፍትን እና የምርምር ስራዎችን ለማግኘት አወደርዕዩ ብቸኛ አጋጣሚ ነው፡፡

የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ 44 መፀሐፍትን ለገበያ ይዞ የሚቀርበው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለዚሁ አውደ ርዕይ የአመቱ አዳዲስ ገና ለገበያ ያለበቁ ሶስት መፀሓፍቶችን ያቀርባል፡፡

“ግብረገብና ስነምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች” በሚል ርዕስ የዩኒቨርስቲው የኤቴክስ እና ፍልስፍና መምህር   ዶ/ር ጠና ደዎ ያዘጋጁት ባለ531 ገፅ መፀሐፍ፣ የአርበኞች ማህበር አመራር አባል በሆኑት አምባሳደር አለማየሁ አበበ የተዘጋጀው “የሸንቁጥ ልጆች- የፀረ ፋሽስት ኢጣሊያ ተጋድሎ በመርሃቤቴ ከ1928 – 1933 እና በዩኒቨርስቲው የዲቨሎፕመንት ሰተዲስ መምህር ዶ/ር በላይ ስማኔ የተዘጋጀ Building Community Resilience to Climate Change የምርምር ስራ ለአውደ ርዕዩ ዩኒቨርስቲው ያቀረባቸው አዲስ ስራዎች ናቸው፡፡

በቀጣይ ሁለትና ሶስት ወራትም ዩኒቨርስቲ ፕሬሱ የፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላን የህይወት ታሪክ” ከጉሬዛ ማርያም እስከ አዲስ አበባ” የሚል መፅሀፍ ያሳትማል፡፡