Thomas Staal
Thomas Staal

(ዋዜማ)-የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ያለው ድርቅ ክፉኛ ያሳሰበው ይመስላል። ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ባለስልጣኖችን በአጭር ጊዜ ልዩነት እየላከ የጉዳቱን መጠን በአካል እንዲመለከቱ እና ሁኔታውን እንዲያጠኑ እያደረገ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን ከጎበኙት ኮንግረስማን ማይክል ኮንዌይ ተከትሎ የአሜሪካን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ—USAID) ምክትል ኃላፊ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል ።

በዩኤስ ኤይድ የዲሞክራሲ፣ ግጭት እና ሰብዓዊ እርዳታ ቢሮ ረዳት አስተዳዳሪ የሆኑት ቶማስ ስታል አዲስ አበባ የገቡት ባለፈው እሁድ ሲሆን ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ በማምራት የተለያዩ አካባቢዎችን ሲጎበኙ ቆይተዋል። ኃላፊው የተመለከቷቸው አካባቢዎች በድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቃታቸው ቀዳሚ ትኩረት እንዲሰጣቸው የተደረጉ ወረዳዎችን ነው።

እንደ ዋዜማ ምንጮች ገለጻ ምክትል ኃላፊው ስታል  ማክሰኞ በምስራቅ ሐረርጌ ውስጥ የምትገኘውን ሜኤሶ ወረዳ ጎብኝተዋል። በአፋር ክልል ወደሚገኙ ወረዳዎች ተጉዘው አዋሽ፣ ገዋኔ እና አሚባራን መመልከታቸውንም ይናገራሉ።

ቶማስ ስታል እ.ኤ.አ ከ2009—2012 በኢትዮጵያ የዩኤስ ኤይድ ሚሸን ዳይሬክተር ሆነው የሰሩ በመሆኑ ሀገሪቱን በቅጡ የሚያውቁ ናቸው። ከኢትዮጵያ በፊት በሱዳን እና በኬንያ በእርዳታ ሰራተኝነት ያሳለፉ መሆናቸውም የምስራቅ አፍሪካን ችግር እንዲረዱ አስችሏቸዋል።

ከመስክ ጉብኝታቸው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት ስታል በነገው ዕለት ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል። ከውውይታቸው በኋላ አሜሪካ ለድርቁ የምትሰጠውን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ በጋራ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በድርቁ የተጎዱ 10.2 ሚሊዮን ዜጎቿን ለመርዳት 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ያሳወቀች ቢሆንም የመንግስትን ድጋፍ ጨምሮ እስካለፈው ወር ማግኘት የቻለችው 800 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል። ከተገኘው ዕርዳታ ውስጥ አብዛኛውን የሸፈነችው ደግሞ አሜሪካ ናት።

ቀሪውን የእርዳታ መጠን ከዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ለማግኘት ያለመ የሰብዓዊ ዕርዳታ ቡድን ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአውሮፓ እና አሜሪካ ሲዞር ሰንብቷል። በኦስሎ ኖርዌይ ጉብኝቱን የጀመረው ቡድኑ ወደ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ አቅንቶ የሚመለከታቸውን ባለስልጣናት አነጋግሯል። ወደ አሜሪካ ተሻግሮም በዋሽንግተን እና ኒውዮርክ ለሚገኙ ለጋሾች የአፋጣኝ ዕርዳታ ጥያቄን አቅርቧል።

አሜሪካ ለቀረበው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ሰጥታለች። ሀገሪቱ ባለፈው ጥር ለድርቁ ተጎጂዎች የሚውል የ97 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ የለገሰች ሲሆን በነገው ዕለት ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የእዚህን እጥፍ እንደሚሆን ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል።

አሜሪካ እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2014 ጀምሮ ለድርቁ የለገሰችው ዕርዳታ 532 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።