20160229_155314
(ዋዜማ ራዲዮ)- የዘመናችን ‹‹ማሞ ዉድነህ›› እያሉ የሚጠሩት አሉ፡፡ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደን፡፡ ያለምክንያት አይደለም፡፡ መረጃን በማሰናዳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አመርቂ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ‹‹ማዕቀብ›› የሚለው መጽሐፉ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡
እንዳለጌታ ትናንት ማለዳ ሽንጣም መጽሐፍ ለገበያ አቅርቧል፡፡ 440 ገጾች ያሉት ይህ ጥራዝ የበዓሉ ግርማን ሕይወት ከኢሊባቡር ሱጴ አንስቶ እስከ ሳርቤቱ የ‹‹ቤርሙዳ›› እስር ቤት ድረስ ይተነትነዋል፡፡
በዓሉ ግርማ ስሙን ያወጡለት ሕንዳዊ አባቱ ናቸው፡፡ ‹‹በዓሉ›› የሚለው ስም በአጋጣሚ በአማርኛም ትርጉም ያለው ቃል ሆነ እንጂ መሠረቱ ሕንድኛ ነው፡፡ ‹‹በዓሉ›› ማለት በሕንድ ቋንቋ ‹‹እድለኛ›› ማለት ነው፡፡ የበዓሉ ወላጅ አባት አቶ ጂምናዳስ ሲባሉ እምነታቸው ደግሞ ሂንዱይዝም ነው፤ የጨርቃ ጨርቅና የሸቀጥ ነጋዴ ናቸው ይላል ሰፋ ያለ ጥናት ተደርጎ የተጻፈ የሚመስለው የዚህ መጽሐፍ የመክፈቻ ምዕራፍ፡፡
በዓሉ ወጥቶ የቀረበት ዕለት ሐሙስ በመሆኑ ላይ ብዙዎች ቢስማሙም ባለቤቱም ሆነች፣ አስፋው ዳምጤ እንዲሁም እስከዛሬ በርሱ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች የሚጠቅሱት ቀን ግን ካሌንደር ሐሙስ እንዳልዋለ ይመሰክራል ይላል ደራሲው ፡፡

የበዓሉ ባለቤት አስፋው ዳምጤን ለበዓሉ መሰወር ምክንያት ማድረጋቸው ከምን የመነጨ እንደሆነ ያብራራል፡፡ በአንጻሩ ደራሲ እንዳለ አስፋው ዳምጤ ጋር ቁጭ ብሎ በጉዳዩ ላይ በስፋት ያወራቸው ሲሆን በዓሉ ያን ቀን ከሌላ ሴት ፍቅረኛው ቤት ከርሞ እንደመጣ፣ ከትዳሩ ዉጭ የሚጎበኛቸው ቆነጃጅት እንደነበሩ የሚያመላክቱ መረጃዎችን ሳያቀብሉት አልቀሩም፡፡

በደርግ ምርመራ ክፍል በሾፌርነት ይሰራ የነበረ ተረፈ ዘመድ አገኘሁ በዓሉ ግርማ እስር ላይ እንዳለ ማየቱን የሚጠቅሰው ደራሲ እንዳለጌታ ሌሎች የሰነድ መረጃዎችም በዓሉ ‹‹ከመገደሉ›› በፊት በእስር መሰቃየቱንና መገረፉን እንደሚያመላክቱ ለማሳመን ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ ‹‹ቤርሙዳ ከተባለው አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ከሚገኝ ቤት ዉስጥ አንድ እስረኛን ሦስት ጊዜ አመላልሻለሁ፡፡ ሁለት ጊዜ ተሸፍኖ ስለነበር ማንነቱን አለየሁትም፡፡ በ3ኛ ጊዜ ግን ተገልጦ ስለነበር አይቼዋለሁ›› ይላል ይኸው መስካሪ ተረፈ ዘመድአገኘሁ፡፡

በአራት ክፍሎች የተዋቀረው ይህ መጽሐፍ በምዕራፍ አንድ በዓሉን ‹‹ከልጅነት ቀናቱ እስከ ጉብዝና ወራቱ›› ይሸፍናል፡፡ ምዕራፍ ሁለት ማኅበራዊ ሕይወቱና ሙያዊ አበርክቶቱን ይዳስሳል፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለት ምዕራፎቹ ‹‹ወዴት ተሰወረ?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚመስሉ ሌሎች ጥያቄዎች ያነሳል፡

ሙሉጌታ ሉሌ፣ አስፋው ዳምጤ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ለማ አበራ፣ ፀሐዬ ደባልቄ፣ የሻዕብያ ሰላዮች፣ የኢህአዴግ መንግሥት እንዲሁም ባለቤቱ ወይዘሮ አልማዝ ጭምር ለበዓሉ መሰወር ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያውቁት አለ በሚል ሰፊ ቃለመጠይቆችና መላምቶችን ተነስቶባቸዋል፡፡

በመጽሐፉ እስከዛሬ ያልተነበቡ የበዓሉ አጫጭር ማስታወሻዎች ከነእጅ ጽሑፉ ጭምር ታትመው ተተንትነዋል፡፡ ለምሳሌ ገጽ 348 ላይ ለኢትዮጵያ መጽሐፍት አሣታሚ ድርጅት ባለቤት ለአቶ ተስፋዬ ዳባ የጻፈው ማስታወሻ እንዲህ ይላል፡፡
ወንድሜ ተስፋዬ! መጥቼ ነበር፡፡ ታመህ ቤት መሆንህን ሰማሁ፡፡ ቶሎ እንደሚሻልህ ተስፋ አለኝ፡፡ ቶሎ እንዲሻልህም እፈልጋለሁ፡፡ ትዕዛዝ ነው፡፡ ለምን መሰለህ? ጓድ ዋና ፀሐፊ ጠርተው መጽሐፌን ጠየቁኝ፡፡ (‹‹ጓድ ዋና ፀሐፊ የሚለው ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ነው፡፡)….
በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ያንተው በዓሉ ግርማ

ይህ በእጅ ጽሑፉ የጻፈው ማስታወሻ በዓሉ መጽሐፍ በጻፈ ቁጥር የደርግ ሰዎች ተከታትለው ያነቡት እንደነበረ የጠቆመ ሆኗል፡፡
መጽሐፉ ለማጠናቀር አራት ዓመታት እንደፈጀ ደራሲው ይናገራል፡፡ ‹በዓሉ ግርማ፡- ሕይወቱና ሥራዎቹ› በሚል ርዕስ የታተመው ይህ መጽሐፍ ልዩ የሚያደርገው እስከዛሬ በበዓሉ ሕይወትና መሰወር ዙርያ የተባሉ፣ የተጻፉና በቃል የተነገሩ ሐሳቦችን በአንድ ላይ መያዙ ብቻ ሳይሆን በምርመራና ቃለመጠይቅ ንክኪ ያላቸውን ሁሉንም ቁልፍ ሰዎች ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናትን ጭምር በአካል አግኝቶ የመረመረበት፣ በአሉ ግርማን በእስር ላይ ሳለ አግኝተነዋል የሚሉ ግለሰቦችን አፈላልጎ ያገኘበት፣ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ የተገኘበት መሆኑ ነው፡፡

በተለይም በበዓሉ መሰወር ዙርያ እስከዛሬ ያልተጠቀሰ መረጃ ቢኖር ኪሮስ ከተባለ ሰው የተገኘ መረጃ ነው፡፡ ኪሮስ በቀድሞው የኢቴቪ ቴክኒሻን የነበረ ግለሰብ ሲሆን ከረዥም ልፋት በኋላ አግኝቶት ግለሰቡ በዓሉ ግርማን ቤርሙዳ ዉስጥ በታሰረበት ጊዜ በአይኑ በብረቱ እንዳየው፣ ድሮ ጓደኛው እንደነበረ፣ እዚሁ እስር ቤት ዉስጥ በዓሉ ሆዱን አሞት ሐኪም እያናገረው እንደሰማ፣ አላስችል ብሎት አይኑን ሲገልጥ በዓሉን እንዳየው ለደራሲው አብራርቶ ነግሮታል፡፡

በዓሉ የፖለቲካ እስረኛ ሆኖ እስርቤት ቆይቷል እንጂ በተያዘበት ቀን እንዳልተገደለ ማረጋገጫ እንዳገኘ የሚናገረው ደራሲው ይልቅ አደገኛ የሚባሉ የፖለቲካ እስረኞች በገመድ እየታነቁ ይገደሉበት የነበረዉና ብስራተገብረርኤል አካባቢ የሚገኘውን ‹‹ቤርሙዳ›› ወይስ ‹‹ሴፍ ሀውስ›› ተብሎ የሚጠራው እስር ቤት እንደቆየ ይጠረጥራል፡፡

ደራሲው ይህንን እስር ቤት ጎብኝቶ በመጽሐፉ ዘርዘር ባለ መልኩ በመተረከ የፎቶ ማስረጃዎችን ጭምር ካቀረበ በኋላ በዓሉ በዚህ እስር ቤት የመጨረሻዎቹን ቀናት እንዳሳለፈ ከፍ ያለ ጥርጣሬ እንዳለው ያስረዳል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ በተጨማሪ በዓሉ ግርማ አስራተ ካሳ ቤት ዉስጥ ሬሳው ተገኝቶ መውጣቱን ኢቴቪም ይህንን መዘገቡን ከዕዉነት የራቀ እንደሆነ መረጃዎችን ጠቅሶ አፋልሷል፡፡ ይህ በኢቴቪ የቀረበው መረጃ ለተራ የፖለቲካ ፍጆታ የዋለ እንደሆነ ባለቤቱን ጨምሮ የደራሲው እማኞች ይከራከራሉ፡፡ የአስራተ ካሳ ቤት በዓሉ በተሰወረበት ጊዜ ለሌላ አገልግሎት ይውል እንደነበር በመጥቀስ፡፡

መጽሐፉ፣ በዓሉን በሚመለከት ተሸፋፍነው የቀሩ የውልደቱ፣ የዕድገቱ፣ የትምህርቱ፣ የትዳሩ፣ የሥልጣንነት ዘመን፣ የሙያ፣ የእስር ቤት ቆይታውና የአገዳደሉ መላምቶች ዳብሮ የቀረበበት ሥራ ነው፡፡
ደራሲ እንዳለጌታ ይህ መጽሐፉ አስረኛ ሥራዉ ሲሆን በአስር ሺ ቅጂ ብዛት፣ በኤች ዋይ አታሚነትና በሊትማን ቡክስ አከፋፋይነት ለአንባቢ የቀረበ ነው፡፡ ይህንን መጽሐፉን የት እንደወደቁ ላልታወቁ፣ ወግ ያለው የቀብር ሥርዓት ላላዩ፣ አሟሟታቸው ምሥጢራዊ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ መታሰቢያ አድርጎታል፡፡