Jeremy Konyndyk USAID/OFDA head
Jeremy Konyndyk USAID/OFDA head

(ዋዜማ ራዲዮ) ጀርሚ ኮንዲያክ በየዓመቱ በአማካኝ በ50 አገራት ለሚከሰቱ ወደ 70 ለሚደርሱ አደጋዎች የሚሰጥ የአሜሪካ ድጋፍን የመምራት ታላቅ ኃላፊነት ተጭኖባቸዋል፡፡ ከደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት እስከ ሶሪያ ጦርነት ድረስ ባሉ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ቀውሶች ተጠምደው የሚገኙት ጀርሚ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ እና እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመግለጽ በዘርፉ ያላቸው የዓመታት ልምድ አልረዳቸውም፡፡

ቅዳሜ መጋቢት 10 በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የድርቁን ስፋት እና መጠን ለመግለጽ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ቃላትና ሀረጎች በአገሪቱ እያንዣበበ ያለውን መጪ ዕልቂት ጠቋሚ ነበሩ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን ሲጀምሩ ድርቁ እልቂት ደረጃ ላይ ባይደርስም በከፍተኛ አደጋነት የሚመደብ እንደሆነ በአጽንዖት የተናገሩ ቢሆንም ግማሽ ሰዓት በፈጀው ቆይታቸው ችግሩን “በ50 ዓመት ውስጥ ያልታየ”፣ “በጣም ግዙፍ” እንዲሁም “ከመጠን በላይ የሰፋ” በሚሉ ቅጽሎች ገልጸውታል፡፡ በሌላው ሀገር እንደተለመደው ችግሩን በቀጥታ ከማስረዳት ይልቅ በ”እልቂት” እና በ”ከፍተኛ አደጋ” መካከል ያለውን ቀጭን መስመር ላለመሻገር ሲጠነቀቁ ተስተውለዋል፡፡

“ይህ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡ ግዴታ እልቂት ነው ማለት አይደለም፡፡ እልቂት እንዲሆን የሚያደርገው ወይም የማያደርገው ለችግሩ የሚሰጠው ምላሽ እና መቆጣጠሩ ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጀርሚ መግለጫውን ከመስጠታቸው በፊት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ይሰተዋልባቸዋል ከሚባሉ ክልሎች አንዱ የሆነውን ትግራይን ጎብኝተዋል፡፡ የክልሉን ፕሬዝዳንት አባይ ወልዱን ጨምሮ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ከጉብኝታቸው እና ከንግግራቸው በኋላ የተሰማቸውን ሲገልጹ “የሚፈለገው እርዳታ ጥልቀት እና ስፋት አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡

“በመስክ ላይ ያየነው የጠቆመን ከፍተኛ የሆነ የእርዳታ መጠን እንደሚያስፈልግ ነው። ብዙ ነገር እሚወሰነው በበልግና እና በክረምት የዝናብ ሁኔታ ነው። አስከፊውን ጊዜ ገና አላየነውም” ይላሉ ጀርሚ። “ይህ ታላቅ ተግዳሮት ነው። የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከተገመተው 10 ሚሊዮን በላይ ጨምሯል።ይህ አሁን ባለው ትንበያ መሰረት ነው። መጪው ክረምት የከፋ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን።”

ይህን አሳሳቢ ከፍተኛ አደጋ ለመቀልበስ ዩ ኤስ ኤይድ ባለሙያዎቹን ከኢትዮጵያ እስከ ጅቡቲ እና ሶማሊያ አሰማርቷል፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱም ለኢትዮጵያ ተብሎ የከፍተኛ አደጋ ምላሽ አስተዳደር ቡድን አቋቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ እና በዋሽንግተን የሚገኙት የዩ ኤስ ኤይድ ቡድኖች አሜሪካ ለድርቁ ከለገሰችው 500 ሚሊዮን ዶላር በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ከመከታተል እና ከመቆጣጠር ባሻገር እርዳታውን በማከፋፈል ላይ ያሉ ችግሮችን እንዲፈቱ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡

ከችግሮቹ መካከል የእርዳታ ማጓጓዣ የጭነት መኪናዎች እና መጋዘኖች እጥረት ነው፡፡ በሀገሪቱ 10.2 ሚሊዮን ለሚሆኑት የምግብ ተረጂዎች እርዳታ በአፋጣኝ ለማድረስ ተጨማሪ የማጓጓዣ መኪናዎች እና መጋዘኖች እንደሚያስፈልጉ ጀርሚ ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ክፉኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው እና አፋጣኝ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች የሚገኙት በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ አፋር እና ድሬዳዋ አካባቢ ያሉ ቦታዎች ናቸው፡፡

እርዳታን በወደብ በቶሎ ከማራገፍ አንስቶ ከጅቡቲ እስከ ድርቅ ተጠቂ ቦታዎች ድረስ ያለው የጉዞ ሰንሰለት ሌላው በችግርነት የሚነሳ ነው፡፡ በጅቡቲ ወደብ የእርዳታ እህልን በማራገፍ የሚታየው መንጓተት እንደ ዩ ኤስ ኤይድ ያሉትን ድርጅቶች በኢትዮጵያ አቅራቢያ ያሉ ሌሎች ወደቦችን እንዲያማትሩ አድርጓቸዋል፡፡ የሶማሌ ላንዱ በርበራ ወደብ ለዚህ ስራ ተመራጭነት የሚያገኝ ይመስላል፡፡ ዩ ኤስ ኤይድ ጉዳዩን ለማጥናት ወደ ቦታው ባለሙያዎችን ልኳል፡፡

ዩ ኤስ ኤይድን ለመሰሉ ድርጅቶች የእርዳታ እህልን በወቅቱ ከማድረስ በተጨማሪ የዘር እህል ማከፋፈልም ሌላኛው ጊዜ የማይሰጠው ስራ ነው፡፡ በመጪው ሰኔ ይዘንባል ተብሎ የሚጠበቀው ዝናብ የሚመጣ ከሆነ ወደ እርሻ ለሚገቡ አርሶ አደሮች የዘር እህል በቶሎ ለማቅረብ ዩ ኤስ ኤይድ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት መሰረት በአሁኑ ወቅት ወደ 3.3 ሚሊዮን የሚጠጉ አርሶ አደሮች የዘር እህል ያስፈልጋቸዋል፡፡