African Avenue Building Construction, Addis Abeba
African Avenue Building Construction, Addis Abeba
  • በአዲስ አበባ የአርማታ ብረት ዋጋ ሰማይ እየነካ ነው፡፡
  • የዶላር ግዢ በጥቁር ገበያ 35 ብር ደርሷል
  • ብረት 9 ወራት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል
  • በአዲስ አበባ ብቻ 26ሺህ የሕንጻ ግንባታዎች ሊስተጓጎሉ ይችላሉ

ዋዜማ ራዲዮ- የውጭ ምንዛሬ መንጠፍን ተከትሎ የግንባታ ግብአቶች ዋጋ መናርና ብሎም ከገበያ ጨርሶዉኑ መጥፋት በግንባታ ኢንደስትሪው ላይ ሁሉን አቀፍ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡ አዲስ አበባም በቅርብ ጊዜ ታሪኳ አይታው የማታውቀው የግንባታ መፋዘዝ ሊያጋጥማት ይችላል፡፡

በተለይም የአርማታ ብረት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በውድ ዋጋ እንኳ ከገበያ ፈልጎ ማግኘት ፈተና ሆኗል፡፡ ባለፉት ዓመታት አንድም ጊዜ ቢሆን የዋጋ መዋዠቅ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለ የብረት ከገበያ መሰወር ተከስቶ እንደማያውቅ ተቋራጮች ይናገራሉ፡፡ 9 ወራት በፊት 110 ብር ይሸጥ የነበረ 12 ሜትር ርዝመት ያለው ባለ 8 ሚሊ ሜትር አርማታ ብረት ከሰሞኑ ዋጋው እጥፍ ሆኖ 195 ብር እስከ 210 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ዘጋቢዎቻችን ተመልክተዋል፡፡ ኾኖም ለናሙና ያህል በተዘዋወሩባቸው የተክለኃይማኖትና የመገናኛ ሱቆች በተጠቀሰው ዋጋም ቢሆን ለእውቅ ደንበኞች እንጂ ለእንግዳ ሸማቾች ብረት አይሸጡም፡፡ 

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ከሁለት ሳምንት በፊት 15 ግዙፍ የብረት ነጋዴዎችን ሐሳዊ የዋጋ ንረት በመፍጠር ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት በጋራ ወጥናችሁ ተንቀሳቅሳችኋል በሚል መጋዘኖቻቸውን ያሸገባቸው ሲሆን ክስም እንደመሰረተባቸው የሚታወስ ነው፡፡

‹‹አሁን እኮ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ብቻ አይደለም፡፡ በውድ ዋጋም ብረት እንደልብ ማግኘት አልተቻለም›› ይላል ዋዜማ ያነጋገረችው የአማካሪ ድርጅት ሬዚደንት መሐንዲስ፡፡ ክስተቱ የሕንጻ ተቋራጮችና አስገንቢዎችን ከዚህ ቀደም ያላዩት ፈተና ውስጥ እንደሚከታቸውም ይኸው መሐንዲስ ይተነብያል፡፡ ‹‹አሁን አሁን ኮንትራክተሮች ጋር ያለው ስሜት ጥሩ አይደለም፤ ችግሩ ከገመቱት በላይ ኾኖባቸዋል፡፡››

ላለፉት ሁለት ዐስርት ዓመታት አዲስ አበባ ከጫፍ ጫፍ ከፍተኛ የሕንጻ ግንባታ የሚካሄድበት ከተማ ሆና ቆይታለች፡፡ ሁሉም የግል ባንኮች ማለት በሚቻል መልኩ በሰንጋ ተራና አካባቢው 30 ወለል በላይ የሆኑ ዋና መሥሪያ ቤቶችን እያስገነቡ ይገኛሉ፡፡ ንግድ ባንክም በአገሪቱ ታሪክ ረዥሙን ባለ 46 ወለል ሕንጻ በማስገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ግዙፍ ግንባታዎች ሌላ ከሰማንያ ሺህ ቤቶች በላይ በመንግሥት የጋራ ቤቶች ፕሮጀክት እየተገነቡ ሲሆን ወደ ኮርፖሬሽንነት ያደገው የቀድመው ኪራይ ቤቶችም 30 ቢሊዮን ብር በመመደብ 16 ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለመንግሥት ሹመኞችና ሠራተኞች ለማስረከብ ዝግጅት እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡ በከተማዋ በግል አልሚዎች የሚገነቡ ሕንጻዎች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ባለሞያዎች እንደሚሉት የብረት ዋጋ ንረት የአዲስ አበባን ያህል ተጽእኖ የሚያደርስበት ሌላ የዓለም ከተማ ላትኖር ትችላለች፡፡

‹‹ይህ የሆነው ያለምክንያት አይመስለኝም፡፡ አንድም ባለሐብቶች አቋራጭ ቢዝነስ ላይ እንጂ ዘላቂ ልማት ላይ ለመሳተፍ ባለመፍቀዳቸው ነው፡፡ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ይኖራል ብለው አለማመናቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ይሸሻሉ፡፡ ሁሉም ፎቅ ጠፍጥፎ ማከራየት ነው የሚፈልጉት›› ይላሉ ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያወያየናቸው የህግ አማካሪና ጠበቃ፡፡

በአዲስ አበባ የሕንጻ ተቋራጭና የአስገንቢ እሰጣገባ ከወዲሁ መሰማት የጀመረ መሆኑን የነገሩን እኚሁ የሕግ አማካሪ  ከግንባታ ጋር የተያያዙ ወደ ሕግ እየሄዱ የሚገኙ  ክሶችም ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑን በግላቸው እንደሚረዱ ይናገራሉ፡፡

የዋጋ ጭማሪ ሳይጠይቁ በቁርጥ ዋጋ (Lump-sum) ግንባታ ጥንቅቅ አድርጎ በመጨረስ ቁልፍ ለማስረከብ የተዋዋሉ ሕንጻ ተቋራጮች ከሰሞኑ ያልጠበቁት የአርማታ ብረት ጭማሪ መከሰቱን ተከትሎ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መዘፈቃቸው በስፋት እየተሰማ ነው፡፡ ከፊል ተቋራጮች ከአልሚዎች ጋር ድርድርና ሽምግልና የተቀመጡ ሲሆን ወደ ግልግል ፍርድ ቤት እያመሩ ያሉ ጉዳዮችም ቁጥራቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡

‹‹በተለምዶ እንዲህ አይነት ዋጋ ንረት ከተከሰተ በሚል በግዙፍ ግንባታዎች የግንባታ ውል ላይ Escalation Clouse ማካተት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ማለት የነዳጅ፣ የብረት፣ መሠረታዊ የግንባታ ግብአቶች ወይም የፊኒሺንግ ዕቃዎች ድንገት በዓለም ገበያ ቢንሩ ጭማሪውን አስገንቢው እንዲሸፍን የሚያስገደድ የውል አንቀጽ ማካተት ማለት ነው፡፡ ውላቸው ላይ ይህን ያላካተቱ በዋናነት በሰሞኑ ጭማሪ ምስቅልቅል ውስጥ ይገባሉ›› ይላሉ ዋዜማ ያነጋገርናቸው እኚህ የሕግ አማካሪና ጠበቃ፡፡ ‹‹በመርካቶ ባልደረባዬ የሚወክላቸው አዲስ የገበያ ማዕከል እያስገነቡ ያሉ አክሲዮን ማኅበር ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ወደ ሕግ እንዳመሩ አውቃለሁ›› ብለውናል፡፡

ከባለ 6 ሚሊ ሜትር እስከ 32 ሚሊ ሜትር ያሉ ባለ 40 60 ግሬድ አርማታ ብረቶች አገር ውስጥ ባሉ 11 ግዙፍ የብረት አምራቾች ይመረታሉ፡፡ ኾኖም የአገር ውስጥ ብረት ፋብሪካዎች ሚናቸው ልቅምቃሚ ብረታ ብረት አቅልጦ ቅርጽ ከማውጣት ያለፈ አይደለም፡፡ ድፍድፍ ብረት (Steel Billet) ሙሉ በሙሉ ከውጭ ነው የሚገባው፡፡ ይህ ምርቱን ለማምረት ከሚያስፈልገው 70 እስከ 80 ከመቶ የሚሆነውን ግብአት የሚሸፍን ነው፡፡ ሁሉም በውጭ ምንዛሬ ነው የሚገባው፡፡ ኾኖም የአገር ውስጥ ብረት አምራቾች እሴት ጭማሪ ከጠቅላላ ምርቱ 30 በመቶም እንደማይበልጥ በዘርፉ የተደረጉ ልዩ ልዩ ጥናቶች ይመሰክራሉ፡፡

‹‹መንግሥት ትልቁ የአርማታ ብረት ሸማች ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ ብዙ ቀውስ ሊያስከትል የሚችለውም ለዚሁ ነው፡፡ በተለይም እንደ የጋራ መኖርያ ቤት ያሉ ሕዝባዊ ፕሮጀክቶች ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ይዘገይ ይሆናል እንጂ የዋጋ ማስተካከያ መደረጉ የማይቀር ነው፡፡›› ይላል ዘጋቢያችን ያነጋገረችው የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ባልደረባ፡፡ 

‹‹ብዙ ሰዎች የብረት መናር ግድ አይሰጣቸውም፡፡ ኢንደስትሪው እኮ ብዙ ሺህ ሕዝብ ነው የቀጠረው፡፡ ግንባታ ሲቆም  ግሮሮ እንደሚዘጋ መገንዘብ ያስፈልጋል›› ይላል ዋዜማ ያነጋገረችው አማካሪ ሬዚደንት መሐንዲስ፡፡

ከክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ኑሯቸውን የሚደጉሙት በግንባታ ዘርፍ በመሰማራት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከፊንፊኔ ልዩ ዞኖችና ከአዲስ አበባ ጠረፍ ሰፈሮች የሚገኙ በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን የሚገፉ በርካታ ዜጎች ከግንባታ ጋር በተያያዘ በጉልበት ሥራ የተሠማሩ ናቸው፡፡ ግንባታዎች በብረት ዋጋ ንረት ምክንያት መስተጓጎላቸው እነዚህን ዜጎች ከሥራ ውጭ ያደርጋቸዋል፡፡

በሸገር ሬዲዮ የሚተላለፈውና በአርክቴክቸርና የግንባታ ጉዳዮች ትኩረቱን ያደረገው ‹‹ከቤት እስከ ከተማ›› የተሰኘ ሳምንታዊ ፕሮግራም በቅርቡ እንደዘገበው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 26ሺህ ያላነሱ ፎቆች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡

‹‹ችግሩ ቀላል አይደለም፡፡ ለኮንትራክተር አንድ ቀን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ውል ማክበር አለበት፡፡ ዉል ካላከበረ በየቀኑ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ ገንዘብ ካልተለቀቀለት ጭንቅ ነው፡፡ ኮንትራክተር ብዙ ሺህ ሰዎችን ነው ቀጥረው የሚያሠራው፣ አንድ ቀን ያለ ክፍያ ማደር አይችልም፡፡ አማራጭ ሲያጣ ሠራተኛ ይበተናል፤ መንግሥት ቶሎ አንድ መፍትሄ ሊያበጅ ይገባል›› ይላል ዋዜማ ያወያየችው ይኸው መሐንዲስ፣ ‹‹መፍትሄ ከዘገየ ግን የኮንትራክተሮች ዉሎ ሳይት መሆኑ ቀርቶ ፍርድ ቤት ነው የሚሆነው››፡፡

የዶላር መንጠፍን ተከትሎ የተከሰተው የአርማታ ብረት ንረት ብቻ እንዳልሆነና በግንባታ ማጠናቀቂያ እቃዎች ላይም ከፍተኛ ጭማሪ መከሰቱም እየተነገረ ነው፡፡ ‹‹ብረት የሲሚንቶ ያህል ዋና ግብአት ነው፡፡ ፊኒሺንግ ሲወደድ ርካሹን ትገዛለህ፡፡ ብረት ሲወደድ ግን ግንባታ ማቆም ነው ያለህ አማራጭ››

ይህ የሰሞኑ የአርማታ ብረት ፈተና የጋራ መኖርያ ቤት ቆጣቢዎችን መንካቱ የሚያጠያይቅ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በአሁኑ ሁሉን አቀፍ የዋጋ ንረት ስሌት ከተኬደ ቀጣይ 40/60 ቤት እድለኛ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በታች ሳይከፍል ቤት ያገኛል ተብሎ  አይጠበቅም፡፡ ከዚያ በታች በሆነ ተመን ቤት ሊያገኝ የሚችለው መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ካደረገ ብቻ ነው፡፡

በአገር ውስጥ የብረት አምራቾች አማካኝነት በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን ብረት የማምረት አቅም ተደርሷል፡፡ ኾኖም ይህን መጠን ለማምረት ከውጭ የሚገባው ድፍድፍ ብረት ስድስት ሚሊዮን ቶን ይደርሳል፡፡ ይህን ለመግዛት ደግሞ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን አገሪቱ ቆዳ፣ ሌጦና የቅባት እህሎችን ተደማምረው ለውጭ ገበያ ቀርበው በብዙ መከራ የምትሰበስበውን የውጭ ምንዛሬ ሙልጭ አድርጎ የሚወስድ የገንዘብ መጠን ነው፡፡