Demeke Mekonen
Demeke Mekonen
  • በሺህ የሚቆጠሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በሊስትሮነት ለማሰልጠን ታቅዷል
  • ከህዝባዊ አመፁ በኋላ በእስር ያሳለፉና ስልጠና የወሰዱ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተብሏል

ዋዜማ ራዲዮ-የፌዴራል መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች፣ እንዲሁም የክልልና ከተማ መዋቅሮች በሙሉ ለሥራ አጥ ወጣቶች የሚኾኑ ሥራዎችን በአስቸኳይ ፈልገው እንዲያዘጋጁ መመሪያ ተላለፈ፡፡

መንግሥት ለወጣቶች ፈንድ የመደበውን 10 ቢሊየን ብር በአመጽ ለተሳተፉና ሥራ አጥ ለነበሩ ወጣቶች እንዲዉል የሕግና አተገባበር ማዕቀፍ እያዘጋጀ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ይህ ትዕዛዝ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መውረዱ የወጣቶች የአመጽ መሳርያ መኾን መንግሥትን ምን ያህል እያሳሰበው እንደመጣ አመላካች ነው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሥራ አጥ ወጣቶች በግላቸው እንዲደራጁና መንግሥት በሚያቀርብላቸው ብድር አነስተኛ ሥራ እንዲጀምሩ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ቡድን አዲስ የወጣቶች ስትራቴጂን ነድፎ በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የስትራቴጂው ግብ ወጣቶቹን በሚቻለው ፍጥነት ሁሉ ከነውጥ ወደ ለውጥ ጎዳና ማምጣት ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ሁሉም መሥሪያ ቤቶች የወጣቶች ጉዳይ ክንፍ (መምሪያ) ቢሮ እንዲከፍቱ ታቅዷል፡፡ እስከዚያው ግን የተደራጁ ወጣቶች ሊሠሯቸው የሚችሉ ማንኛቸውም ሥራዎችን በጥብቅ አፈላልገው እንዲያቀርቡ ሁሉም የፌዴራልና የክልል መሥሪያ ቤቶች ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከድህነት በታች ከሚኖሩ 22 ሚሊዮን ዜጎች ዉስጥ 18 ሚሊዮን የሚኾኑት ወጣቶች ናቸው፡፡

በመንግሥት በኩል በቅድሚያ እንዲደራጁና ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ከሚታሰቡ ወጣቶች መሐል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ላለፉት ወራት በአዋሽ፣ አላጌና ብር ሸለቆ ማዕከላት ፖለቲካዊ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ በቁጥር 6ሺ የሚጠጉ ወጣቶች ናቸው ተብሏል፡፡ ይህም አገሪቱ ላይ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ቅድሚያ ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብለው የሚታሰቡ ወጣቶችን ለማለዘብ የታለመ ሳይኾን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡

በአዲስ አበባ መስተዳደር ደረጃ ከባለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በጉዳዩ ላይ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ስብሰባ የተቀመጡ ሲኾን ክፍለከተሞች ከማዕከል እስከ ቀበሌ በሁሉም መዋቅር፣ በሁሉም ጽሕፈት ቤቶችና ቢሮዎች የሚገኙ ኃላፊዎች በአስቸኳይ ክፍት የሥራ ቦታ ፈልገው ምን ያህል ወጣቶችን ለመቀበል እንደተዘጋጁ የሚገልጽ ሰነድ ወደ ማዕከል እንዲልኩ ከድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ቀጭን ትእዛዝ ተላልፎላቸውል፡፡

በወቅቱ ምን ዓይነት ክፍት ቦታዎች ላይ እንዴት ያሉ ሥራዎችን ለወጣቶች መፍጠር ይቻላል በሚለው ነጥብ ዙርያ በመስተዳደሩ ጠንከር ያለ ዉይይትና ክርክር ተደርጓል፡፡ አንዳንድ ኃላፊዎች በሚያስተዳድሯቸው ቢሮዎች ዉስጥ ለወጣቶች የሚኾን ሥራ እምብዛምም የሌለ መኾኑን፤ ክፍት የሥራ ቦታ ቢኖር እንኳ በሞያው ለሰለጠኑ ጥቂት ወጣቶች የሚኾኑ ቦታዎች እንደኾኑ በመናገራቸው ከአወያይ ኃላፊዎች ከፍ ያለ ተግሳጽ ደርሶባቸዋል፡፡ በወቅቱ  ከድርጅት የተወከሉ አንድ አወያይ በቁጣ “ይህ አገር የቆመው በወታደር ነው፣ ወጣቱን ሥራ ካልሰጠነው እኛ እዚህ ቦታ አንኖርም፤ ለወጣቶች የሚኾን ሥራ የለንም ስትሉ እናንተም በወንበራችሁ ላትኖሩ እንደምትችሉ ማሰብ ይኖርባችኋል” ሲሉ ጠንከር ያለ ንግግር ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡

በዚህ ዓመት የሁለቱን ምክር ቤቶች መከፈትን ተከትሎ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የመንግሥትን ቀጣይ አቅጣጫ ባመላከቱበት ንግግራቸው የወጣቶችን የኢኮኖሚ ልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የመንግሥታቸው ተቀዳሚ አጀንዳ እንደሚሆን ጠቁመው ነበር፡፡

ለዋዜማ የደረሰ መረጃ እንደሚያመለክተው አመጹን ተከትሎ በቦሌ ወረዳ 12 አካባቢ የሚገኙ ነባር የወጣት ሊግ አባላት በአካባቢው የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶችን በየቤቱ እየዞሩ መመዘገብ ጀምረው ነበር፡፡ በርካታ ወጣቶች ለመመዝገብ አለመፍቀዳቸውን ተከትሎም በቅድሚያ ሥራ እንሰጣችኋለን በሚል ምዝገባው ዳግም እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ ከብዙ ጉትጎታ በኋላም በርካታ ወጣቶችን ማሰመን ተችሏል፡፡ በዚህ ዙር የተመዘገቡ ወጣቶች በሴቶች ሊግና በወጣቶች ሊግ ከተደለደሉ በኋላ ለአንድ ወር የሚኾን ሥልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ በቀን 50 ብር የዉሎ አበል እየተሰጣቸውና በአይገር ባስ እየተወሰዱ ስልጠና ላይ የቆዩ ወጣቶች በስልጠናው መጨረሻ ሥራ እንደሚያገኙ ከፍተኛ ተስፋ ነበራቸው ይላል ከአስተባባሪዎች አንዱ ለዋዜማ ሲያስረዳ፡፡ ኾኖም በስልጠናው ማብቂያ ዋዜማ አንድ የድርጅት ኃላፊ ተገኝተው “መንግሥት ለጊዜው ለናንተ የሚኾን ሥራ እያዘጋጀላችሁ ነው፤እስከዚያው ግን ለሦስት እየተደራጃችሁ አንድ የጋራ የባንክ ደብተር አውጡና መቆጠብ ጀምሩ” ብለው በመናገራቸው በወጣቶቹ ላይ ብስጭትን ፈጥሯል፡፡ ከዚያ በኋላ ወጣቶቹ ወደ ወረዳ ሲጠሩ ለመሄድ ፍቃደኛ  ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

አሁን በአዲስ መልክ ቤት ለቤት የሥራ ወጣቶች ምልመላ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ሲኾን በጉዳዩ ላይ ዋዜማ ያገኘቻቸው የጽሑፍና የቃል ማስረጃዎች እንደሚያስረዱት ለመመዝገብ ፍቃደኛ በማይኾኑ ወጣቶች ላይ ጠንከር ያለ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች ገና ከአሁኑ ክፍት የሥራ ቦታዎችን እየፈጠሩ ሲኾን አመጽ ቢነሳ ሊያቀጣጥሉት ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ወጣቶችን ፋይል በማዘጋት ሥራም ተጠምደዋል ተብሏል፡፡

“በኛ ክፍለ ከተማ የነዋሪዎችን ፋይል እንዲያደራጁና የክላሰር ቁጥር እንዲያዘጋጁ፣ ባለጉዳዮች የሚያቆሙባቸውን የመኪና ማቆምያ ፓርኪንግ እንዲሠሩ፣ በዚያውም የመኪና እጥበት ሥራ እንዲጀምሩ፣ ባለጉዳይ ሲመጣ ወረፋ እንዲያሲዙና፣ ሌሎች ተባራሪ ሥራዎችን እየለየንላቸው ነው” ይላል በጉለሌ ክፍለ ከተማ የድርጅት ጽሕፈት ቤቱ ባልደረባ፡፡ በዚህ ወጣት ገለጻ መሠረት ሁሉም ዴስኮች፣ ጽሕፈት ቤቶችና ቢሮዎች ለወጣቶች ሥራ የመፈለግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፣ በአካባቢያቸው ፋብሪካዎች የተተከሉባቸው ዳርቻ ላይ የሚገኙ እንደ አቃቂ ቃሊት ያሉ ክፍለ ከተሞች ደግሞ ከፋብሪካ ባለቤቶች ጋር በአጋርነት በመሥራት ባሉ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ወጣቶችን ተደራድረው ያስቀጥራሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ማስቲሽና ቤንዚል እየሳቡ በየጎዳናው የሚዋልሉ የጎዳና ልጆችን ሰብስቦ መጠነኛ ስልጠና በመስጠት ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ለማድረግ እንደሚሞከር ተመልክቷል፡፡ የጎዳና ልጆቹን ባለፈው ዓመት ለአተት ታማሚዎች ተዘጋጅተው የነበሩ መጠለያዎች ዉስጥ በጊዝያዊነት በማቆየት በዋና ዋና የከተማዋ ኮሪደሮች ሼድ ተዘጋጅቶላቸው የጫማ መጥረግ ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ሼዶቹን በመነገንባትና የሊስትሮ ሳጥኖችን በማዘጋጀት ረገድ እንደ ፔፕሲ ያሉ የግል ኩባንያዎችን እገዛ ለመጠየቅ ታስቧል፡፡ አደባባይ በማስዋብና አረንጓዴ ቦታዎችን በማዘጋጀት የሚታወቁ የመንግሥት አጋር የኾኑ የግል ድርጅቶች ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ መቋቋም የሚችሉትን እንዲያዋጡና በምላሹም ሼዶቹ ላይ ማስታወቂያ እንዲሰራላቸው እንደሚደረግም ተመልክቷል፡፡

በፌዴራል ደረጃ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሥራ አጦችን ስምና አድራሻ ለዚሁ በተዘጋጀ የመረጃ ቋት ከመዘገበ በኋላ ምን ያህል ወጣት በመንግሥት የወጣት ፈንድ እንደታቀፈና ምን ያህሉ ሥራ እንዳገኘ ለማወቅ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት ጨረታ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በባለፈው ዓመት መጀመርያ በተሰበሰበ መረጃ በከተሞች ደረጃ 17 በመቶ ወጣቶች በሥራ አጥነት ላይ ሲኾኑ ከነዚህ ዉስጥ የሚልቁቱ የሚገኙት በድሬዳዋ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ነው፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቅርቡ በባህርዳር በተደረገ የሥር እድል ፈጠራ የንቅናቄ መድረክ ወጣቶችን በየትኛውም የገቢ ማስገኛ መስክ እንዲሰማሩ ቀንተሌት እንሰራለን ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በዚሁ መድረክ አቶ በረከት ስምኦን ለወጣቶች ሥራ መፍጠር የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ሲሉ ተሰምተው ነበር፡፡ በአማራ ክልል ለወጣቶች ሥራ የብድር አገልግሎት የሚውል ወደ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከአበዳሪ ተቋማት መገኘቱ ተገልጧል፡፡ በክልሉ ዘጠኝ መቶ ሺህ  ወጣቶች ሥራ ፈት ናቸው፡፡

ከአራት ወራት በፊት 3ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችን በሚሊንየም አዳራሽ ሰብስበው ለማወያየት የሞከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “70 በመቶ የሚኾነው የአገራችን ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች ነው፤ ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት፤ ስለዚህ በሕዝቦች ፈቃድ ወደ ሥልጣን የሚመጣ መንግሥት የወጣቶች መንግሥት መሆን አለበት” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡