ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ በቅርቡ የቴሌኮም አገልግሎቱን በይፋ እንደሚጀምር የሚጠበቀው የኬንያው ሳፋሪኮም ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ ግብይት አገልግሎትን ፍቃድ ጭምር እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን የገንዘብ ሚንስትር ደዔታ እዮብ ተካልኝ ለኬንያው ቢዝነስ ደይሊ ጋዜጣ ተናግረዋል።

መንግሥት በቅርቡ ላልተወሰነ ጊዜ ካራዘመው ሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ ውስጥ የሞባይል ገንዘብ ዝውውርና ግብይት አገልግሎትን እንዳስወጣው እዮብ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እና ግብይት ፍቃድ እንዲሰጥ የሚያስችለው የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ እንደሆነ እና እስከ ቀጣዩ ግንቦት ወር ሳፋሪኮም ፍቃዱን ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ እዮብ አክለው ጠቁመዋል።


መንግሥት ቀደም ሲል የሞባይል ገንዘብ ግብይትን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንደማያደርግ በማሳወቁ፣ ሳፋሪኮም ኩባንያ አምና ተወዳድሮ ባሸነፈበት የመጀመሪያው የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እና ግብይት አገልግሎት ፍቃድ አልተካተተም ነበር። ሆኖም መንግሥት አምና በግንቦት ወር ላይ እንደገና አቋሙን ቀይሮ የኬንያውን ሳፋሪኮም ጨምሮ የውጭ ኩባንያዎች በሞባይል ገንዘብ ግብይት አገልግሎት ጭምር እንዲሳተፉ መፍቀዱ ይታወሳል።


መንግሥት ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙን ባለፈው ታኅሳስ ያስታወቀው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገሪቱ በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ሳቢያ ብቃት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች በጨረታው ላይሳተፉ ይችላሉ ብሎ በመስጋቱ እና በጨረታው የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎችም ጊዜው እንዲራዘምላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እንደሆነ ቀደም ሲል አስታውቋል።

ሚንስትር ደዔታ እዮብ ግን ሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ፣ ሳፋሪኮም ኩባንያን የሞባይል ገንዘብ ግብይት ፍቃድ ከማግኘት እንደማያግደው፣ መንግሥት ለኩባንያው የገባውን ቃል እንደማያጥፍ እና ኩባንያው በአፍሪካ በቀዳሚነት የሚታወቅበትን በሞባይል ገንዘብ የመገበያየት እና የማዘዋወር አገልግሎት ፍቃድ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ እንደሚያገኝ ቃል ገብተዋል።ሳፋሪኮም ኩባንያ አምና በኢትዮጵያ ጨረታ ያሸነፈበትን የቴሌኮም አገልግሎት እስከ መጭው ሚያዚያ ድረስ እንደሚጀምር ቀደም ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።


ሳፋሪኮም ኩባንያ በኬንያ ከ15 ዓመታት በፊት በጀመረው “ኤምፔሳ” (M-pesa) በተባለው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እና ግብይት አገልግሎቱ በሀገሪቱ ከ50 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ በአፍሪካም ግዙፉ በሞባይል የገንዘብ መገበያያ እና ማዘዋወሪያ አገልግሎት ነው። የሳፋሪኮም እህት ኩባንያ የሆነው የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም ደሞ በታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሶቶ፣ ጋና፣ ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ግብጽ ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል። [ዋዜማ ራዲዮ]