• አዲሱ መመሪያ ትችት ሲበዛበት የነበረውንና እንዲቀር የተወሰነውን የ27 በመቶ ቦንድ አሰራርን በእጅ አዙር የመተግበር ያህል ነው ተብሏል።

ዋዜማ ራዲዮ- እየተቋቋመ ባለው የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በልዩ ሁኔታ እንዲጠቅም የሚያስችል ህግ ለመንግስት መቅረቡን ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። ይህም የሚሆነው ንግድ ባንኮች በካፒታል ገበያ ውስጥ ሲሳተፉ በገበያው ከሚቀርበው ቦንድ ወይንም ሰነድ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚያቀርበውን ቦንድ ሌሎች አካላት ከሚያቀርቡት ሰነድ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲገዙ የሚያስገድድ ህግ ነው። በህጉ መሰረት ባንኮች በካፒታል ገበያ ውስጥ እየተሳተፉ ሰነድ ለመግዛት የሚያወጡትን ገንዘብ ለልማት ባንክ በሰነድ ለማበደር ቅድሚያ ይሰጣሉ።

አስገዳጁ ሰነድ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተዘጋጀ ሲሆን እንዲጸድቅም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ መቅረቡን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። ነገሩም ከወዲሁ ባንኮችን ያስደሰተ እንዳልሆነ መረዳት ችለናል። ህጉ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነም ንግድ ባንኮች በካፒታል ገበያ ውስጥ ሲሳተፉ የመተማመኛ ሰነድን ተቀብለው ለሚያዋጣቸው አካል ገንዘብ የማበደር እድላቸውን ያጠበዋል።

በዚህ የሰነድ ወይንም የካፒታል ገበያ ውስጥ ቦንድን ለመግዛት የተሻለ ወለድን ለሚያቀርብ ገንዘብን የማበደር አዝማሚያ ይኑር እንጂ ልማት ባንክ ይጽደቅልኝ እያለ ያለው ህግ ባንኮች ከቆጣቢዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ የተሻለ ትርፍ ያስገኝልናል ላሉት አካል ሳይሆን ወለዱ ዝቅተኛ ቢሆን እንኳ ለልማት ባንክ በሰነድ ለማበደር ይገደዳሉ ።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአንድ ባንክ ከፍተኛ ሀላፊ አስገዳጅ ህጉ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ማለት “ከዚህ ቀደም እንዲቀር የተወሰነውን የ27 በመቶ ቦንድ አሰራርን በጓሮ በር እንዲተገበር ማድረግ ነው ” ሲሉ ለዋዜማ ራዲዮ ተናግረዋል።

ከ2003 አ.ም ጀምሮ እስከ 2012 አ.ም ድረስ የግል ንግድ ባንኮች ከሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በቦንድ ያበድሩ እና ብሄራዊ ባንክ ደግሞ ገንዘቡን መንግስት በፖሊሲ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች እንዲያበድር ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይሰጠዋል።

የግል ንግድ ባንኮች ለብሄራዊ ባንክ በቦንድ የሰጡት እያንዳንዱ ብድርም አምስት አመት ሲሞላው ነበር የሚመለስላቸው። አሰራሩ የግል ንግድ ባንኮች ሳያስደስት የቆየውም ባንኮቹ ለሌሎች ተበዳሪዎች ቢሆን ከ12 በመቶ ጀምሮ ባለ ወለድ ሊያበድሩ የሚችሉትን ብር ለብሄራዊ ባንክ በወቅቱ በነበረ ዝቅተኛ የአስቀማጮች ወለድ 5 በመቶ እና ቀጥሎ በተስተካከለው 7 በመቶ ነበር እንዲያበድሩ ሲገደዱ የነበሩት። ወለዱ አዋጭ ባለመሆኑ ይቀየር ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተው በ2012 አ.ም ነው አጠቃላይ አሰራሩ እንዲቀርላቸው የተወሰነው።

አሁን ታድያ መልኩን ቀይሮ የተዘጋጀው ተመሳሳይ አዝማሚያ ያለው አስገዳጅ ህግ ነው ። ነገሩም መንግስት ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ብድር ማቅረቢያ በርካታ አማራጮችን ማቅረብ እንዳልቻለ ማሳያ ሆኗል። የ27 በመቶ ቦንድ አሰራሩ የአሁኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሀንስ አያሌው (ፒኤችዲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት እያሉ ለልማት ባንክ ያስተገበሩት አሰራር ሲሆን አሁን ደግሞ ልማት ባንኩን ራሳቸው እየመሩት አሰራሩ ለሚመሩት ባንክ በካፒታል ገበያው እንዲደገምላቸው ተቋማቸው ህጉን ለመንግስት አቅርቧል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን የቀረበው ረቂቅ ህግ መንግስታዊውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይመልከተው አይመልከተው ግን ግልጽ አይደለም። የ27 በመቶ የቦንድ አሰራር ንግድ ባንክን ሳይመለከተው መቆየቱ ይታወቃል።

ልማት ባንክ ከዚህ ቀደም በ27 በመቶ ቦንድ አሰራር ከ115 ቢሊየን ብር በላይ በብሄራዊ ባንክ በኩል ተሰብስቦለት ነበር። በነበረው ብልሹ የብድር አሰጣጥ ለበርካታ ብክነት ተጋልጦ ቆይቶ ተገቢ ህጋዊ እርምጃ ሳይወሰድ አሁንም በሌላ መልክ የገንዘብ ምንጭ እንዲዘጋጅለት መደረጉ ተገቢ አይደለም የሚል ትችትም ከባለሙያዎች እየቀረበበት ነው።

ለነበሩ ብልሹ አሰራሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጉዳያቸው ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የተላኩ ግለሰቦች ጉዳይም ተድበስብሶ ቀርቷል። ልማት ባንኩ በቅርብ አመታት ከሰጠው ብድር 51 በመቶ ያህሉ የተበላሸና የማይመለስ እስከመሆን ደርሶ ነበር። አሁንም ልማት ባንኩ ከተመሳሳይ የብክነት ስራ ወጥቷል ማለት አይቻልም። ከዮሀንስ አያሌው በፊት የነበሩት የባንኩ ፕሬዝዳንት ሀይለኢየሱስ በቀለ በዚሁ ከብድና ተያያዥ ጉዳዮች ሳቢያ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]