ዋዜማ ራዲዮ- ለሶስት ቀናት ህዳር (2-4/2009) በዩናይትድ ስቴትስ አትላንታ ከተማ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች የታደሙበት ጉባዔ ተካሂዷል። ጉባዔው በሶስት አጀንዳዎች ላይ የተነጋገረ ሲሆን በዋና አጀንዳነት ስፊ ውይይት የተደረገበት የኦሮሞ ቻርተር ነው።

በጉባዔው ላይ የተሳተፉ የዋዜማ ምንጮች እንደገለፁልን ስብሰባው በኦሮሞ የትግል አቅጣጫና የኦሮሞ የተለያዩ ቡድኖችን ወደ አንድነት ለማምጣት ሰፊ የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት ነበር። የኦሮሞ ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት የኦሮሞ ህዝብ በቀጣይ ፍላጎቱ ተጠይቆ  የሚወሰን መሆኑንም በጉባዔው መግባባት ተደርሶበታል።
“ከሞላ ጎደል ጉባዔው የተሳካ ነበር፣ ለአሁኑ የኦሮሞ ድርጅቶችን የሚያስተባብር አንድነት በመፍጠርና የወደፊት አቅጣጫ በማስቀመጥ ስምምነት ላይ ደርሷል” ይላል ስሙን የሸሸገው ተሳታፊ።
“በረጅም ጊዜ በኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ሰፊ ተቃርኖና መጠላለፍ መኖሩንና ይህም ትግሉን ወደፊት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳው እንደሚችል ባደረግናቸው ውይይቶች በግልፅ ተንፀባርቋል” ሲል ያክልበታል

ጉባዔው በሀገር ሽማግሌ ምርቃት የተከፈተ ሲሆን የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ(OMN) ስራ አስኪያጅና የጉባዔው አዘጋጅ ጃዋር መሀመድ የመግቢያ ንግ ግር አድርጓል።
“ይህ የምንወነጃጀልበት ቦታ አይደለም፣ መወነጃጀል ነፃነት ቢያመጣ ኖሮ ገና ድሮ ነፃነት ባገኘን ነበር” ሲል የጉባዔው ተሳታፊዎች በገንቢ ውይይትና በአንድነት ላይ እንዲያተኩሩ ተማፅኗል።
ለውይይት የቀረበው ቻርተር/ሰነድ የኦሮምኛ ቋንቋን ለማያነቡ ግን ደግሞ ለሚሰሙ ተሳታፊዎች በእንግሊዘኛ ተባዝቶ የተሰራጨ ሲሆን፣ የጉባዔውን ውይይት በድምፅም ሆነ በምስል መቅረፅ ተከልክሎ፣ የተመረጡ ቅንጫቢ ምስሎችና የመክፈቻ ስነስርዓት በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ(OMN) በኩል ተለቋል። ጉባዔውን ከሰርጎ ገቦች ለመታደግ ተሳታፊዎች ኦሮሞ ስለመሆናቸውና የግብዦ ወረቀት ያላቸው ስለመሆኑ ማጣራት መደረጉንም ከተሳታፊዎች ተረድተናል።