ዋዜማ- በኦሮምያ ክልል መንግስት ከዘርፍ ቢሮዎች አንስቶ እስከ ዞን ድረስ በሁሉም መዋቅሮች የአመራር ለውጥ ሊደረግ መሆኑን ዋዜማ ከሁነኛ ምንጮቿ ሰምታለች።

የክልሉ ምክር ቤት  (ጨፌው) ትናንት መደበኛ ስብሰባውን የጀመረ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ስለመወያየቱ ግን ማረጋገጥ አልቻልንም። የብልፅግና ፓርቲ የክልሉን ብሎም የተጎራባች ክልሎችን የፀጥታ ይዞታ በገመገመበት ወቅት በቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት የኦሮምያ ክልል አመራሮችን መበወዝ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል።

የአመራር ለውጡ የክልሉን ርእሰ መስተዳድር እና ምክትል ርእሰ መስተዳድሮችን ይመለከታል ወይ ብለን ነሳነው ጥያቄ ; የመረጃ ምንጮቻችን በዚህ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ባይሆኑም : በብዙ የክልሉ መዋቅሮች የአመራር ለውጥ እና ሽግሽጉ እንደሚከናወን ; እንዲሁም በዞን እና መሰል መዋቅሮች አመራሮችን ከተወለዱባቸው አካባቢዎች ውጭ በአመራርነት እንዲመደቡ የማድረግ ዕቅድ እንዳለ ነግረውናል።

የኦሮምያ ክልል በኢትዮጵያ “የፖለቲካ ለውጥ” ከመጣ ወዲህ ከተፈጠሩ ሰፊ የጸጥታ ችግሮች ባለፈ ማንነት ተኮር የሆኑ የነዋሪዎች ግድያ እና ማፈናቀሎች በተደጋጋሚ መከሰታቸውን በሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሳይቀር ተረጋግጧል። ለነዚህ ቀውሶች መነሻውም በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ያሉ አመራሮች የተወለዱበትን  አካባቢ ስለሚመሩ አካባቢያዊነትን መነሻ በማድረግ የገቡበት ፖለቲካዊ ብልሽት አንዱ መነሻ መሆኑን ክልሉ ያምናል መባሉን ሰምተናል። በሚደረገው አዲስ የአመራር ለውጥም የአመራሮች ምደባ እና የትውልድ ስፍራቸው ስብጥር ከግምት እንደሚገባም ሰምተናል።

የክልሉ መንግስት የዞንና ወረዳ አመራሮች የተወለዱባቸውን አካባቢዎች መምራታቸው ማንነት ተኮር ሰብአዊ ጥቃት እንዲያደርሱ መንገድን ከፍቷል የሚል ግምገማ ቢኖረውም : ከተወለዱበት ቦታ ርቀው በአመራርነት የተመደቡ ግለሰቦች በሚያስተዳድሯቸው አካባቢዎችም ተመሳሳይ ማንነት ተኮር ማፈናቀሎች ተጸጽመዋል የሚል ትችትን የሚያነሱ አሉ። ሆኖም የክልሉ መንግስት በቅርቡ በሚተገብረው የአመራር  ምደባ የአመራሮችና የተወዱበትን ቦታ  ማሰባጠርን ለክልሉ የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ እንደ መፍትሄ ወስዶታል።

የኦሮሚያ ክልል ልክ እንደ አማራ ክልል ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች በመንግስት እና በታጣቂ ሀይሎች ግጭት የሚደረግበት ሆኖ ቀጥሏል።

የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ ለማረጋጋት ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጎን ለጎን በፌደራልና በክልል ደረጃ ተከታታይ የሹም ሽር እንደሚኖር ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል። [ዋዜማ]