Lemma Megerssa, Oromia regional gov head- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሚያስተዳድራቸው ሁለት መቶ ያህል ወረዳዎች እና 20 የዞን አስተዳደሮች በሀላፊነት ያስቀመጣቸውን አመራሮች በአዳዲስ ለመተካትና አንዳንዶቹንም በአዲስ ሀላፊነት ለመሾም እየተዘጋጀ መሆኑ ተሰማ።

ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንደሰማችውና ከክልሉ አንድ ከፍተኛ ተሿሚ እንዳረጋገጠችው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በሚያስተዳድረው የኦሮምያ ክልል የተሻለ ብቃትና ልምድ ያላቸውን አመራሮች ለመመደብ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ሹም ሽሩ በፓርቲውና በክልሉ አመራሮች በምስጢር ተይዞ መቆየቱንም ስምተናል።
ኦዴፓ ባለፉት ወራት በርካታ ወረዳዎችን በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎችና ደጋፊዎች ተነጥቆ እንደነበር ይታወሳል። አንዳንድ የኦዴፓ አመራሮች ከፅንፈኛ ቡድኖች ጋር በመመሳጠር በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ና በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ከክልሉ መንግስት ባለመታዘዝ ከፍተኛ አስተዳደራዊና የፀጥታ ቀውስ እንዲፈጠር አድርገው ቆይተዋል።

አስተያየታቸውን ለዋዜማ የሰጡ የክልሉ ሹም አዳዲስ አመራሮችን የመመደብ ስራ ከወራት በፊት በዕቅድ ተይዞ ሲሰራበት የቆየና የክልሉን ህዝብ መሰራታዊ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ ያለመ እርምጃ ነው።


በአዲሱ ምደባ የተሻለ ትምህርትና ልምድ ያላቸው በስነምግባርም ህብረተሰቡ እምነት የሚጥልባቸው አመራሮችን ለመመደብ መታቀዱን ባለስልጣኑ ይናገራሉ። ሙስናና ብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁና ህዝቡ ቅሬታ የሚያቀርብባቸው አመራሮች መኖራቸውንና ይህንንም በተግባር ለመመለስ ሹምሽሩ አንድ እርምጃ መሆኑን ነግረውናል።

ኦዴፓ በውስጡ ስር የሰደደ መከፋፈል መፈጠሩንና የጠቅላይ ሚንስትሩን የለውጥ እርምጃ የሚደግፉና ከፅንፈኛ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ያበሩ መኖራቸው በስፋት እየተነገረ ይገኛል። በኦዴፓ ውስጥ ያለውን ሽኩቻ የተመለከተ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/tSmlntpMKUA