Meskel Square /Exhibition center
Meskel Square /Exhibition center

ዋዜማ ራዲዮ- የሚንስትሮች ምክር ቤት ኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን ያወጣው አጭር ረቂቅ አዋጅ ለ26 ዓመታት ሲንከባለል ለኖረው ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መልስ ለመስጠት መሞከሩ አወንታዊ ርምጃ ቢሆንም የረቂቅ አዋጁ ይዘት ግን የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾችን ያረካ አይመስልም፡፡

እንዲያውም ረቂቅ አዋጁ በዋነኛነት ማህበራዊ አገልግሎቶችን እና አስተዳደራዊ ሥራዎችን በማቀናጀት እና ማስተሳሰር ላይ ማተኮሩ በእንጥልጥል ላይ ያለውን አወዛጋውን የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ዕቅድ (Master Plan) በአዋጁ ሽፋን በተዘዋዋሪ ለመተግበር እንደተፈለገ ቆጥረውታል፡፡ በርግጥም የሚንስትሮች ምክር ቤት ረቂቁን አዋጅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የአዲስ አበባን መሪ ዕቅድ በስም ባይቅሰውም መንፈሱ ግን ይህንኑ ጥርጣሬ የሚያጠናክር መሆኑን ብዙ ወገኖች ይጋሩታል፡፡ በውጭ ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ከማስከበር ይልቅ በህዝቦች መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር ያለመ መሆኑን በመጥቀስ ከወዲሁ እያወገዙት ሲሆን ሌሎች የኦሮሞ ብሄርተኞችም ረቂቅ አዋጁን መሠረታዊ ህገ መንግስታዊ መብቶችን መልሶ በችሮታ መልክ በመስጠት በኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ላይ የቀለደ አዋጅ አድርገው አጣጥለውታል፡፡ ባንጻሩ ሌሎች ወገኖች “ረቂቅ አዋጁ ከተማዋን ለኦሮሚያ ክልል አሳልፎ የሰጠ ነው” በማለት እያወገዙት ይገኛሉ፡፡ ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከግርጌ ይመልከቱ 
ይህንን መነሻ በማድረግ ባጠቃላይ ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ ኦሮሚያ ክልል፣ የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾች እና ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ከረቂቅ አዋጁ ምን ያተርፋሉ? ምንስ ያጣሉ? ረቂቅ አዋጁ ወደፊት ምን ዓይነት አንድምታዎች ሊኖሩት ይችላሉ? የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ካነሷቸው የመብት ጥያቄዎች አንጻር የብሄሩ መብት ተሟጋቾች ረቂቁን አዋጅ እንደምን ያዩታል? የሚሉት ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡
ለዓመታት ሲንከባለል የኖረው ህገ መንግስታዊው ልዩ ጥቅም ቁልፍ ፖለቲካዊ እና ህጋዊ ጉዳይ ቢሆንም በ1997ቱ ምርጫ ማግስት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ከመሆኗ ውጭ ክልሉ ሌላ ልዩ መብት ተከብሮለት አያውቅም፡፡ ጉዳዩ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ መስተዳደር እና በፌደራሉ መንግስቱ መካከል የሞቀ ክርክር እና ፍትጊያ ተደርጎበት አያውቅም፡፡ ጉዳዩ ዋና ፖለቲካዊ አጀንዳ መሆን የጀመረው የኦሮሚያዊ ህዝባዊ አመጽ በተቀጣጠለ ማግስት ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የልዩ ጥቅሙን ጉዳይ የትግላቸው ማጠንጠኛ አድርገውት ቆይተዋል፡፡
መንግስትም ለሀዝባዊ አመጽ መነሻ የሆነው “መሪ ዕቅዱ በቂ ውይይት ሳይደረግበት አይተገበርም”፤ ሌላ ጊዜ ደሞ “ጭራሹን ተዘርዟል” እያለ ሲያድበሰብሰው ከቆየ በኋላ ትኩረቱን ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ባለው ልዩ ጥቅም ላይ ማድረግን ነበር የመረጠው፡፡ የኦሮሞ አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው እንደሚያፈናቅል የሚነገርለትን የአዲስ አበባን መሪ ዕቅድ በመቀበሉ ለከባድ ትችት የተዳረገው ኦሕዴድ-መራሹ ክልላዊ መንግስትም በአመጹ ማግስት ህገ መንግስታዊውን ልዩ ጥቅም የሚመለከት ረቂቅ ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ባይታወቅም የፌደራል መንገስቱም ከይዞታቸው ለሚፈናቀሉ ኦሮሞ አርሶ አደሮች ተገቢውን ካሳ መክፈል እንደሚጀመር ከገለጸ በኋላ መሪ ዕቅዱን ግን መተግበር እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል፡፡
ባሁኑ የልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጅ የተካተቱት ድንጋጌዎች የአግልግሎት አቅርቦትን፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን፣ አካባቢ ጥበቃን፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶችን እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ እንጂ እምብዛም ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው አይደሉም፡፡ በአዋጁ የተቀመጡትን ልዩ ጥቅሞች አፈጻጸም የሚከታተል ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት የሆነ ከክልሉ እና ከከተማ አስተዳደሩ የተውጣጣ የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም መገለጹ የአዋጁ ቁልፉ አስተዳደራዊ ክፍል ነው፡፡ በዚሁ አስተዳደራዊ ልዩ ጥቅም ረገድ በአዋጁ ፍሬ ያለው ነገር የተካተተው የከተማዋ አስተዳደር እና የክልሉ መንግስት በጋራ እንደሚያቋቁሙት የተገለጸው የጋራ ምክር ቤት ነው፡፡ ከጋራ ምክር ቤቱ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ እና መማሪያ ቋንቋ እንዲሆን መደረጉ አንዱ ለኦሮሚያ ክልል ከተጠበቁለት ጥቅሞች ፖለቲካዊ አንድምታ ያላው ጥቅም ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል፡፡
አንዳንድ የኦሮሞ ብሄርተኞች በህገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀስ 5 ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ “ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም…” የሚለው አንቀጽም ፖለቲካዊ አንድምታ በመስጠት የክልሉ መንግስት በከተማዋ ምክር ቤት ከምርጫ ሥርዓት ውጭ በሆነ መልኩ ግፋ ቢል እኩል ካልሆነም በኮታ የሚሰጥ ውክልናን ሊያካትት እንደሚገባ እና ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል ሙሉ ቁጥጥር ስር እንድትሆን ሲወተውቱ ቢኖሩም ጥያቄው ግን ባሁኑ አዋጅ ፍሬ አላስገኘም፡፡
ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ላለፉት 26 ዓመታት የክልሎችን የርስበር ግንኙነት እንዲሁም ክልሎች ከፌደራሉ መንግስት ጋር ያላቸውን ህገ መንግስታዊ ግንኙነት (inter-governmental relations) በህግ ማዕቀፍ ስላልደነገገ ግንኙነቱ ሲመራ የኖረው በኢመደበኛ አሠራሮች እና ደብዳቤ ልውውጥ ብቻ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ግን መንግስት የበይነ-መንግስታቱን ግንኙነት የሚወስን ዝርዝር ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን ገልጧል፡፡ የዚሁ ረቂቅ አዋጅ ይዘት ገና ባይታወቅም የተሟላ አዋጅ እንዲሆን ከተፈለገ ግን አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ከአጎራባች ክልሎች ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ጭምር መሠረታዊ መርሆዎችን እንደሚደነግግ መገመት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ህገ መንግስታዊ ጥቅም በአዋጅ ከመደንገጉ በፊት ተፈጻሚ ቢሆን ጠቃሜታው የጎላ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ ህዝባዊ አመጽ ከተቀጣጠለበት ወዲህ በአዋጅ ላይ አዋጅ እየደራረበ የሚገኘው ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት የትኛውን ረቂቅ አዋጅ ቀድሞ አጽድቆ ሥራ ላይ እንደሚያውለው ግን ወደፊት ማየቱ ይሻላል፡፡
የአሁኑ ረቂቅ አዋጅ የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም የክልሉ እና የአዲስ አበባ አስተዳደር የሁለትዮሽ ጉዳይ አድርጎ ነው ያቀረበው፡፡ በተጨባጭ ሲታይ ግን የአዲስ አበባ አስተዳደር በጉዳዩ ብዙም ሚና የሚኖረው አይመስልም፡፡ ባንድ በኩል ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት የሆነው የከተማዋ አስተዳደር የክልል መንግስት ያህል ሉዓላዊ ህገ መንግስታዊ ሰውነት ስለሌለው ከኦሮሚያ ክልል ጋር በእኩልነት ለመደራደር የሚያበቃው ህጋዊ እና ፖለቲካዊ ቁመና የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ መሪ ዕቅድ ዝግጅትም ሆነ የሙከራ ትግበራ ሂደት ምን አስተዋጽዖ እንደነበረው ድምጹን አሰምቶ አያውቅም፡፡ ይልቁንስ በከተማዋ ስም በአደባባይ ዋናውን ሚና ሲጫወት የታየው ፌደራል መንግስቱ ብቻ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደሞ ከተማዋ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ፌደራሉ መንግስቱ ግልጽ ህጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ስላሉት ጥቅሞቹን ለማስከበር ሲል የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናይ መሆኑ አይቀርም፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ ከመሪ ዕቀዱ በበለጠ አንገብጋቢ የሆነውን ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በትግበራውም ፌደራል መንግስቱ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ በርግጥ የከተማዋ አስተዳደር እና ኦሮሚያ ክልል ወደፊት በሚያቋቁሙት የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ለፌደራል መንግስቱ ውክልና አላገኘም፡፡ ፌደራል መንግስቱ ግን ጥቅሞቹን ከጀርባ ሆኖ ለማስጠበቅ የሚችልበት ዕድል አሁንም ሰፊ ሲሆን እጁን ለማስገባት ከሚረዱት የፌደራል ተቋሞች መካከልም ፌደሬሽን ምክር ቤትን፣ ፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴርን እና የከተማ ልማት ሚንስቴርን ግምት ውስጥ ማስገባት ይቻላል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የከተማዋ አስተዳር እና ክልሉ የሚያቋቁሙት የጋራ ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስቱ መደረጉ ደሞ ለፌደራል መንግስቱ ተጨማሪ ዕድል ይፈጥርለታል፡፡ በርግጥ የጋራ ምክር ቤቱ ተጠሪነት ለፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር ይሁን ወይንስ ለተወካዮች ምክር ቤት በግልጽ ባይደነገግም ከአዋጁ መንፈስ መረዳት የሚቻለው ግን ተጠሪነቱ ለሥራ አስፈጻሚው አካል እንደሚሆን ነው፡፡ በረቂቅ አዋጁ መሰረት ለጋራ ምክር ቤቱ የተሰጠው ሚና በአዋጁ የተደነገገውን ልዩ ጥቅም አፈጻጸም መከታተል እና ድጋፍ መስጠት ሲሆን የጋራ ፖሊሲዎችን የመንደፍ ሙሉ ስልጣን ይኑረው አይኑረው ግን ገና ገልጽ አልሆነም፡፡ ለነገሩ ፖሊሲ እና ደንብ የማውጣት ሥልጣን ቢኖረውም ዞሮ ዞሮ ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት መሆኑ የመጨረሻው የበላይ ሥልጣን ባለቤት እና ይሁንታ ሰጭው ፌደራል መንግስቱ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር በልዩ ጥቅሙ አፈጻጸም ቁልፍ ሚና እንዲኖረው ከተፈቀደለት ግን ጉዳዩ ከሁለትዮሽ ጉዳይነት ይልቅ የሦስትዮሽ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ከተማዋ በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ያደረገችው አስተዋጽዖ አነስተኛ ቢመስልም ወደፊት መንግስት አዋጁን ለማዳበር በምን መልኩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን እንደሚያሳትፍ ግልጽ አይደለም፡፡ ከተማዋ ግን አዋጁን በሚያጸድቀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግን 23 መቀመጫዎች ስላሏት ጥቅሞቿን ማስጠበቅ የምትችልበት ዕድል አሁንም ገና አልተዘጋም፡፡ በዚህ ረገድ ያለፉ ልምዶች ተስፋ ሰጭ ባይሆንም ከተማዋ በቀጣዩ የፓርላማው የሥራ ዘመን ዕድሏን ትጠቀምበት አትጠቀምበት ወደፊት ጊዜው ሲደርስ ማየት የሚሻል ነው የሚሆነው፡፡
ሀገሪቱ ባስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ባለችት ሁኔታ ፌደራል መንግስቱ ረቂቅ አዋጁን እንዳሻው እንደቀረጸው ነው መታዘብ የሚቻለው፡፡ የሚንስትሮች ምክር ቤት ቁመናውን በማይመጥን ቋንቋ ያወጣው መግለጫም ወቅታዊውን ፖለቲካዊ ትኩሳት ለማብረድ ሲል ፖለቲካዊ ትክክለኛነትን ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው አዋጁ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም እንደማይሸራርፍ አፋዊ ዋስትና ለመስጠት የሞከረው፡፡ አዋጁ ከወጣ በኋላም ለክልሉ የተጠበቀለት ልዩ ጥቅም ከኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ጥቅም በግልጽ ተለይቶ ስላልቀረበ መዘበራረቅ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳ ለህግ ተርጓሚዎች የሚተው ቢሆንም አዋጁ በከተማዋ ላይ የሚነሳውን የባለቤትነት ጥያቄም ቢሆን በማያሻማ ሁኔታ መመለስ የቻለ አይመስልም፡፡ የከተማዋ የባለቤትነት ጥያቄ አንገብጋቢ የሚሆነው የተሻሻለው የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግስት የክልሉ የግዛት ወሰን ከጫፍ እስከ ጫፍ የማይከፋፈል መሆኑን መደንገጉ አዲስ አበባን የክልሉ የግዛት አካል እንዳደረጋት የህገ መንግስት ባለሙያዎች ደጋግመው ስለሚገልጹ ነው፡፡ የክልሉ እና ከተማዋ ድንበር ወሰን ገና አለመካለሉ ደሞ ሁኔታውን የበለጠ አወሳስቦታል፡፡ ከኦሮሞ ብሄርተኞች በተቃራኒ የቆሙ በርካታ የከተማዋ አንዳንድ የቦታ ስያሜዎች በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እንዲሰየሙ አዋጁ መፍቀዱ የከተማዋን ባለቤትነት ለኦሮሚያ ክልል አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል በማለት ነው እያወገዙት ያሉት፡፡
ባጠቃላይ የከተማዋን መሪ ዕቅድ በተናጥል ለመተግበር መሞከሩ ዋጋ እንዳስከፈለው የተረዳ የሚመስለው ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት በልዩ ጥቅሙ ረቂቅ አዋጅ ሽፋን መሪ ዕቅዱን መልሶ መተግበር ከቻለ በርግጥም ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደመታ ይቆጠራል፡፡ ምንኳ ዘላቂ መፍትሄ ባይሰጥም ከፖለቲካ አንጻር ሲሰላ ዋናው አትራፊ ሊሆን ይችላል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ እየቀረበ ያለው ትችት ግን ክልል-አቀፍ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ መነቃቃት ለመፍጠር እየሞከረ ላለው አዲሱ የኦሕዴድ አመራር ከባድ ፈተና መደቀኑ አይቀርም፡፡ መንግስት የብሄር ፖለቲካውን በማጦዙ እና ጉዳዩን ለዓመታት ያስተናገደበት መንገድ ከፍትሃዊነት እና የህግ የበላይነት ይልቅ ጊዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ለማካበት ያለመ በመሆኑ የልዩ ጥቅም ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የከተማዋ የባለቤትነት ጥያቄም ጭምር የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾች የትግል አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=M-HT3TD_daY