የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚፈቅደውን የኢትዮጵያ ህገመንግስት በርካታ ሰዎች እጅግ በስጋት እነደሚመለከቱት ይታወቃል። ጊዜ የሚጠብቅ ፈንጂ የሚሉትም አሉ። ጎረቤት ሀገሮችም ይህን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ በስጋት ይመለከቱታል። ጦሱ ለነሱም እንደሚተርፍ ከወዲሁ የሚያስጠነቅቁም አሉ። 

ቻላቸው ታደሰ የሚከተለውን ፅፏል፣ በድምፅ የተሰናዳውንም ግርጌ ላይ ያገኙታል

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ የብሄሮችንና ብሄረሰቦችን የራስን እድል በራስ መወሰን መብት እስከመገንጠል ብትፈቅድም በተግባር ግን ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ጥያቄውን በከፍተኛ በስጋት ነው የሚያየው፡፡ የመገንጠል መብትን ህጋዊ ማድረጓ ግን በቀጠናው የሀገራቱን የግዛት አንድነት ለሚገዳደሩ እና መገንጠልን ለሚሹ ቡድኖች ያለው አንድምታም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡

ራሷ ኢትዮጵያ ካሉባት የመገንጠል ጥያቄዎች በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነትን መፍጠር እና ፍትሃዊ የሃብት እና ስልጣን ክፍፍል ማድረግ ያልቻሉት እንደ ሱዳን፣ ኬንያ እና ኤርትራ ያሉ ሀገሮችም በይፋም ይሁን ውስጥ ለውስጥ የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎች እና አዝማሚያዎች ስላሉባቸው የቀጠናው ሀገሮች የመገነጣጠል እጣ ፋንታ አሁንም ትኩስ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በርግጥ ለአዝማሚያዎቹ መፈጠር የኢትዮጵያውን ህገ መንገስት ተጠያቂ ማድረግ ባይቻልም የቀጠናው መንግስታት ግን የህገ መንግስቱ የመገንጠል አንቀጽ በከፍተኛ ስጋት ነው የሚያዩት፡፡

በርግጥ ከአፍሪካ ቀንድ ክፍለ አህጉር ውጭ በናይጀሪያ የቢያፍራ፣ በኮንጎ የካታንጋ እና በሞሮኮ የምዕራብ ሰሃራ ተገንጣዮች ከመነሳታቸው ውጭ በአፍሪካ የመገንጠል ጥያቄ እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ ከቀዝቃዛው ዐለም ጦርነት ማክተም ወዲህ ግን የኢትዮጵያው ረዥም የርስበር ጦርነት መቋጫ ያገኘው የኤርትራን መገንጠል እውን በማድረግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ውልደት እና ታሪካዊ ጉዞ በውሽልሽል መንገድ ሀገር ከሆኑት ሌሎች አፍሪካዊያን ሀገራት ቢለይም በተግባር የመገንጠል ፈር የተቀደደው እና በኋላም በህገ መንግስት እውቅና ያገኘው በራሷ በኢትዮጵያ መሆኑ ለሌሎች አፍሪካዊያን እንቆቅልሽ የሚሆንባቸውም ለዚህ ነው፡፡

ሌላኛው የሱዳን ረዥም የርስበርስ ጦርነትም እንዲሁ ከኤርትራ መገንጠል በኋላ ለደቡብ ሱዳን ነጻ ሀገርነት መንገድ በመጥረግ ነው የተቋጨው፡፡ ገና ዐለም ዐቀፍ እውቅና ባታገኝም ሱማሌላንድም ራሷን ከሱማሊያ ከገነጠለች ሁለት አስርት ዐመታት አልፈዋል፡፡ ሱማሌላንድ እውቅና ብታገኝ የፑንትላንድ ራስ ገዝ አስተዳደርም ተመሳሳይ መንገድን ልትከተል ትችላለች የሚለው ስጋት ተጨባጭ ስጋት ነው፡፡

አንድ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን የሚገፋፉት ምክንያቶች የባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ርዕዮተ ዐለማዊ ልዩነቶች፣ ከጭቆና ወይም ከመድልዖ ነጻ የመሆን ፍላጎት፣ የሃብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አለመኖር እና የውጭ ሀገራት ስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ሲባል የሚደረጉ ጣልቃ ገብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የሚታዩትም የመገንጠል ጥያቄዎችም ከታሪካዊ በደል፣ ከፖለቲካ ስልጣን እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መገለል፣ ከቅኝ ግዛት ታሪክ እና ከውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት በሃይል እንደተዋሃደ የሚያምነው ታጣቂው የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር የኦጋዴን ጎሳን መሰረት አድርጎ ነጻ የኦጋዴኒያ ሪፐብሊክን ለመመስረት ወይም ከሱማሊያ ጋር ለመዋሃድ ሲፋለም አስርት ዐመታት አስቆጥሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት የቡድኑን አመራሮች በመከፋፈል እና ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻዎች በማድረግ ቢያዳክመውም የመገንጠል አጀንዳው ግን በቀላሉ የሚሞት አይደለም፡፡

የመንግስት ጦር ለዐመታት ባደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳደረሰባቸው የሚናገሩት ኦጋዴኖች አሁንም ከአዲስ አበባው መንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት በውጥረት እና ጥርጣሬ የተሞላ ነው፡፡ ባካባቢው አሁን የሚታየው አንጻራዊ ሰላም በወታደራዊ ክንድ ተጠርንፎ ከመያዙ የመነጨ መሆኑም በሰፊው ነው የሚታመነው፡፡ በተለይ ሱማሊያ ወደፊት የተረጋጋች ሀገር ስትሆን ተገንጣዩ ቡድን ተመልሶ ለማንሰራራት ምቹ ሁኔታ እንደሚያገኝ ጠንካራ እምነት አለ፡፡

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው የኦሮሞ ብሄር የመገንጠል ጥያቄም አሁንም ሁነኛ የፖለቲካ መፍትሄ ሳያገኝ እንደተዳፈነ አለ፡፡ ምንም እንኳ እንደ ቡድን በእጅጉ የተዳከመ ቢሆንም የአጀንዳው አራማጅ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም (ኦነግ)በምዕራብ ሀገራት፣ ወታደራዊ ክንፉ ደሞ ኤርትራ ውስጥ መሽጎ ነጻዋን የኦሮሚያ ሪፐብሊክ እውን ለማድረግ እየታገለ መሆኑን ሲሰብክ ይደመጣል፡፡

ኬንያ የጓዳውን በአደባባይ

በኬንያም ቢሆን የመገንጠል አዝማሚያ በተለያዩ ጊዚያት ሲነሳ ሲወድቅ ኖሯል፡፡ ቅኝ ገዥዎች ባሁኗ ኬንያ ስር የከለሏቸው የሰሜን ምስራቅ ኬንያ ሱማሌዎች በሃይል ተጨፈለቁ እንጂ በነጻነት ማግስት ተገንጥለው ሱማሊያ ጋር ለመዋሃድ ተደጋጋሚ አመጻ አድርገዋል፡፡ ከጥቂት ዐመታት በፊት ደሞ የሞምባሳ ሪፐብሊካን ካውንስል የተባለ ንቅናቄ ተቋቁሞ በህንድ ውቂያኖስ ዳርቻ ያሉ ግዛቶችን የመገንጠል ሃሳብ ማንሸራሸር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይጓዝ ተኮላሽቶ ቀርቷል፡፡

ባለፈው ነሐሴ የተካሄደውን አወዛጋቢ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ የመገንጠል ሃሳብ ብቅ ብሏል፡፡ የሃሳቡ አራማጆች በተደጋጋሚ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መጭበርበሩን፣ በርካታ ጎሳዎች ከኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተገለሉ መሆናቸውን እና መንግስታዊ ጭቆና መስፈኑን እንደ ምክንያት በመጥቀስ ለመገንጠል ሃሳቡ በበይነ መረብ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል፡፡ በምርጫው የታየውን ድምጽ አሰጣጥ መሠረት በማድረግ በደቡብ ምዕራብ እና በህንድ ውቂያኖስ ዳርቻ ያሉ አርባ ክፍለ ሀገሮችን በመገንጠል የኬንያ ህዝባዊት ሪፐብሊክን ለመመስረት ያለመ ነው፡፡

በራይላ ኦዲንጋ የሚመራው የተቃዋሚው ብሄራዊ ልዕለ ጥምረት እስካሁን ሃሳቡን በይፋ ባያቀነቅነውም አንዳንድ አመራሮቹ ግን በተናጥል የመጨረሻው መፍትሄ ይሄው መሆኑን በይፋ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በዳግም ምርጫው ማሸነፋቸውን ካጸደቀ ወዲህ ተቃዋሚው ሃይል የቀረው አማራጭ ለህገ መንግስታዊ ማሻሻያ መታገል ወይም መገንጠልን መስበክ ሆኗል፡፡ ሃሳቡ አራት ጊዜ በምርጫ የተሸነፉት የራይላ ኦዲንጋ የመጨረሻ ካርድ እንደሆነ እምነት ያላቸው ወገኖችም ቀላል አይደሉም፡፡ ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር በስምምነት ፍቺ መፈጸም ደሞ ይቻላል ተብሎ ስማይተበቅ ተገንጣዮች የሚከተሉት መጠነ ሰፊ የአደባባይ ህዝባዊ ተቃውሞ ወደተራዘመ ግጭት እንዳያመራ ስጋት አለ፡፡

እንግዲህ መገንጠል በሰላማዊ መንገድ ሊፈጸም የሚችለው በድርድር እና በስምምነት ወይም መገንጠልን የሚፈቅድ ህጋዊ ማዕቀፍ ሲኖር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም በጠቅላላው በአህጉሪቷ ከኢትዮጵያ በስተቀር የመገንጠል መብትን በህግ የፈቀደ አንድም ሀገር የለም፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም እኤአ በ1964 የጸደቀውን የቅኝ ግዛት ወሰን የማይገሰስ መሆኑን የሚደነግገውን መርህ ስለተቀበለ የሀገራቱን የግዛት አንድነት የሚሸረሽርን ጥያቄ አይደግፍም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ቻርተርም ያንድ ሀገር የግዛት አንድነት መሸርሸር ከቻርተሩ መርሆዎች ጋር ተጻራሪ መሆኑን ይገልጻል፡፡

የመገንጠል ሃሳብ አቀንቃኞች በፊናቸው በ1986 የጸደቀው የአፍሪካ ሰብዓዊ እና ህዝባዊ መብቶች ቻርተር አንቀጽ 20 “ሁሉም ህዝቦች የማይገሰስ የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው” በማለት ይደነግጋል፡፡ የኬንያዎቹ የመገንጠል ጥያቄ አንቀሳቃሾች እንግዲህ ይህንኑ ድንጋጌ በመተማመን ነው ጥያቂያቸውን ለአፍሪካ ሰብዓዊ እና ህዝባዊ መብቶች ኮሚሽን ለመምራት ያሰቡት፡፡ ዐለም ዐቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ድንጋጌም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ይቀበላል፡፡ የአፍሪካው ቻርተር አንቀጽ “ቅኝ የተገዙም ሆኖ የተጨቆኑ ህዝቦች ዐለም ዐቀፉ ህብረተሰብ በሚፈቅደው መንገድ ሁሉ ራሳቸውን ከጭቆና ቀንበር የማላቀቅ መብት አላቸው” ሲልም ጨምሮ ይደነግጋል፡፡ የኦሮሞ ብሄር ተገንጣዮች ይህንኑ አንቀጽ ነው ሊጠቅሱ የሚችሉት፡፡

እዚህ ላይ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የተለያየ መንገድ እንደሚከተሉ ማየት እንችላለን፡፡ በህገ መንግስቷ መገንጠልን በፈቀደችው ኢትዮጵያ አጀንዳውን በይፋ መስበክ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያውን ኦሮሚያ ክልል በሚመራው ኦህዴድ ውስጥ ራሱ የመገንጠል ሃሳብ በግለሰብ ደረጃ እንኳ በይፋ ሲንሸራሸር ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት አሁንም ለመገንጠል መብት አፋዊ ድጋፉን ይስጥ እንጂ አጀንዳውን ግን በስጋት ነው የሚያየው፡፡ ባለፈው ዐመትም መንግስት “ኦሮሚያን ለመገንጠል ሲያሴሩ ያገኟቸው” ብሎ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የሽብር ክስ መመስረቱ ለዚሁ ስጋቱ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ለመገንጠል ጥያቄ ይቅርና ማለቂያ ለሌለው የብሄረሰቦች ማንነት እውቅና ጥያቄ ራሱ ምላሽ መስጠት ማቆሙን ታች አምና መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከመገንጠል በመለስ ያለው የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ባጠቃላይ ሲታይ ጠባብ አመለካከት ላላቸው ጎሰኛ ፖለቲከኞች የግል ፖለቲካ አላማ ማስፈጸሚያ እና የሃብት ማካበቻ ከመሆን አልፎ ለብሄሮችና ብሄረሰቦች ሁለገብ ፋይዳ አላስገኘላቸውም፡፡ እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብሄር ማንነትን ወደሚለይ መጠነ ሰፊ ግጭት እና ህገ መንግስቱ ከመደበላቸው ክልል ውጭ የሚኖሩ ዜጎችን በጅምላ ከቀያቸው ወደማፈናቀል ማደጉ ስርዓቱ በመርህ ደረጃም ይሁን በአፈጻጸሙ ሀገሪቱን በነውጥ ሊበታትናት እንደሚችል ማሳያ ነው፡፡

ባንጻሩ የመገንጠል መብት ባልፈቀደችው እና በህግ አሃዳዊ ቅርጽ ባላት ኬንያ ባሁኑ ጊዜ የመገንጠል አጀንዳ ሰላማዊ የአደባባይ መወያያ መሆን መቻሉን ስናይ ፌደራላዊ ስርዓትን የተከለው ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት በምን ያህል ስጋት ውስጥ እንዳለ መታዘብ እንችላለን፡፡ መንግስትም በእስካሁኑ አያያዙ መገንጠልን በሰላማዊ እና ህገ መንግስታዊ አካሄድ እንደሚፈቅድ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቀሰቀሰበት መጠነ ሰፊ ህዝባዊ አመጽ ሳቢያ ፖለቲካዊ ቀውስ ስለገጠመው የፖለቲካ ቅቡልነት ለማግኘት እና ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ቢያንስ ሊቆጣጠረው በሚችለው ደረጃ ጉዳዩ በአደባባይ እንዲቀነቀን ውስጣዊ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል ግምት ማሳደር ይቻላል፡፡ የሆነው ሆኖ መብቱ በህግ ተፈቅዶ ሳለ በመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ በውይይት አለመዳበሩ ደሞ ውሎ አድሮ አመለካከቱ እንዲከር ስለሚያደርግ የራሱ ጉዳት እንዳለው መናገር አይከብድም፡፡

በሌላ በኩል “ታሪካዊ በደል” የሚባለው አወዛጋቢ ትርክት ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር ያመሳስላታል፡፡ በኢትዮጵያ “በሀገረ መንግስቱ ምስረታ ሂደትም ሆነ ከዚያ በኋላ መንግስታት ባንዳንድ ብሄረሰቦች ላይ ያደረሷቸው ታሪካዊ በደሎች እንዴት ይካሱ?” የሚለው ጉዳይ ሁነኛ መፍትሄም ሆነ ብሄራዊ መግባባት ያላገኘ ጉዳይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስትም ለትርክቱ ህጋዊ እውቅና ከመስጠት እና ባደባባይም አፋዊ ድጋፉን ከመግለጽ ባሻገር በተለይ የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱትን “ተበዳይ ነን” ባዮች የሚያረካ ፖሊሲ ቀርጾ አልተገበረም፡፡

ኬንያም በተመሳሳይ እኤአ በ2010 በቀረጸችው አዲሱ ህገ መንግስቷ ያልተማከለ አወቃቀር ዘርግታ በተለይ ፖለቲካዊ ስልጣንን ወደ ክልላዊ ግዘቶቿ በተግባር በማውረድ ረገድ ባጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ ርቀት ሂዳለች፡፡ ያም ሆኖ በነጻነት ማግስት መንግስታቱ አንዳንድ ጎሳዎችን በማግለል ላደረሷቸው በደሎች “የተለየ ፖሊሲ አያስፈልግም” የሚለው አቋም ስላልተቀየረ ነው እንግዲህ ላሁኑ የመገንጠል አዝማሚያ እርሾ እየሆነ ያለው፡፡

የመገንጠል ጦስ

ተገንጥሎ ነጻ ሀገር መመስረት ብቻ እውነተኛ ነጻነትን፣ ሰላምን እና ብልጽግናን ያጎናጽል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለዚም ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳንን ጥሩ ማሳያዎች እንደሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ኤርትራ በዜጎቿ ጅምላ ስደት እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ስሟ በዐለም ቀዳሚ ተጠቃሽ በመሆኗ “አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ” የሚል ስያሜ እስከማትረፍ ደርሳለች፡፡ የደቡብ ሱዳኑ ነጻ አውጭው ድርጅትም በጎሳ ተከፋፍሎ የስልጣን ሽሚያ ውስጥ በመዘፈቁ ሳቢያ በተቀሰቀሰ የርስበርስ ጦርነት ከሀገርነት ተርታ እያወጣት ይገኛል፡፡ ዛሬም በዲንቃ ጎሳ የሚራው የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት እና በኑዌሩ ሬክ ማቻር የሚመራው ታጣቂው ቡድን እርቅ ማውረድ ስላልቻሉ ጦርነቱ እና ስደቱ ቀጥሏል፡፡ መንግስታዊ ሙስናውም ሀገሪቱ የተትረፈረፈ የነዳጅ ሃብቷን ለህዝቦቿ እድገት እንዳትጠቀምበት ከባድ ማነቆ ሆኗል፡፡

“በርግጥስ ለነጻነት ትግል ሲባል የሚከፈለው መስዕዋትነት እና የሚደርሰው ውድመት በመጨረሻ የሚገኘውን ነጻነት የሚመጥን ነው ወይ?” የሚለው ጥያቄም ተደጋግሞ የሚነሳው ለዚህ ነው፡፡ የኦሮሞ እና ኦጋዴን መገንጠል አቀንቃኞችም የዚህን እንቅስቃሴ ሂደት በትኩረት እንደሚከታተሉት እሙን ነው፡፡

ባጠቃላይ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የክፍለ አህጉሩ ሀገራት ዴሞክራሲያዊ እና ሁሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ማቆም እስካልቻሉ ድረስ ካንዣበበባቸው የመገነጣጠል አደጋ በቀላሉ የሚላቀቁ አይመስልም፡፡ የርስበርስ ጦርነት፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ ድርቅና ርሃብ ባልተለየው የአፍሪካ ቀንድ ክፍለ አህጉር ዛሬም ምስቅልቅሉ እየወጣ ነው፡፡ ለሀገረ መንግስታቱ የግዛት አንድነት ስጋት የሆኑ የመገንጠል ጥያቄዎችም ሁነኛ መፍትሄ ስላላገኙ ደረጃው ቢለያይም የመገንጠሉ ሃሳብ ዛሬም በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ ሱማሊያ እና ኬንያ አለ፡፡ የደቡብ ሱዳን የርስበር የጎሳ ጦርነትም ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልተበጀለት አዲሲቷ ሀገር ቢያንስ ከሁለት የመከፈል እድሏ ዝግ አይደለም፡፡

 

https://youtu.be/MCh8cjsiPaw