ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወንድወስን አንዱዓለም ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን ዋዜማ ራዲዮ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ስምታለች። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት በፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ በአማካሪነት ከሰሩ በኋላ ነበር ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት።


አቶ ወንድወሰን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የቀረበ ግንኙነት ካላቸው ተሿሚዎች አንዱ ናቸው።


አንድ ወቅት ጋዜጠኛ ሆነው ለአጭር ጊዜ የሰሩት አቶ ወንድወሰን የብሮድካስት ባለስልጣን ከነበራቸው ሀላፊነት ተነስተው አሁን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል እንደተመደቡ ተረድተናል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሁለቱም ሀላፊዎችን በአዲስ ተሿሚዎች ለመተካተ ጠቅላይ ሚንስትሩ የቀረቡላቸውን ዕጩዎች እየገመገሙ መሆኑንም ስምተናል። [ዋዜማ ራዲዮ]