ዋዜማ ራዲዮ- ከሰሞኑ የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመቀስቀስ ተሳትፈዋል የተባሉት ሁለት የትግራይ ክልል የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ስርጭት ኢዩቴል(EutelSat) ከተባለው የፈረንሳይ ሳተላይ ላይ እንዲወርድ መደረጉን ተረድተናል።


ድምፀ ወያነ እና ትግራይ ቴሌቭዥን ስርጭታቸው መቋረጡን ይፋ አድርገዋል።
ስርጭቱ ከሳተላይት እንዲወርድ የተደርገው በፈረንሳይና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት መሆኑን ጣቢያዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ግን የቴሌቭዥን ጣቢያዎቹ እንዲታገዱ አለመጠየቁን ይልቁንም የእርምት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ደብዳቤ መፃፉን ተናግሯል።
በተመሳሳይ መንግስት የጥላቻ ቅስቀሳ አድርገዋል ያላቸውን ሌሎች የመገናኛ ብዙሀን ለማሳገድ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንና በባህር ማዶ ባሉ የጥላቻ ቅስቀሳ በሚያደርጉ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችል ጥረት ማድረግ መጀመሩን ስምተናል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዳነች አቤቤ በባህር ማዶ ሆነው በሀገር ቤት ጥላቻ የሚነዙትንና የሚያስተባብሩትን ተጠያቂ ለማድረግ መስሪያ ቤታቸው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።