ዋዜማ ራዲዮ- 350 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴን ለኢትዮጵያ የሸጠው የብሪታንያ ኩባንያ ሶስት የሀገሪቱ ተቋማት ላይ የ105 ሚሊየን ብር ክስ መሰረተ።


ክሱን በኢትዮጵያ ሶስት የመንግስት ተቋማት ላይ ያቀረበው የብሪታንያው ኢንትሬድ የተባለ ኩባንያ ሲሆን የክሱ መነሻም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2016 ለኢትዮጵያ ከሸጠው 350 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ጋር በተያያዘ ነው።በኩባንያው ክስ ያቀረበባቸው የኢትዮጵያ ሶስት የመንግስት ተቋማትም የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ; የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ናቸው።


ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ መረዳት እንደቻለችው የብሪታንያው ኢንትሬድ ኩባንያ የኢትዮጵያ መንግስት በአውሮፓውያኑ 2016 ለዋጋ ማረጋጊያ 350 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴን ለመግዛት አለማቀፍ ጨረታን ሲያወጣ ስንዴውን ለማቅረብ ጨረታውን አሸንፏል።ኢንትሬድ ጨረታውን ካሸነፈ በሁዋላም 350 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴውን በስምንት መርከብ አጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ ላይ ያደርሳል።ሆኖም ግዥውን የፈጸመው የመንግስት ግዥና የንብረት ማስወገድ አገልግሎት መርከብ ላይ የተጫነውን ስንዴ የጭነት መኪናዎችን በማቅረብ በወቅቱ መረከብ አልቻለም ነበር።በዚህም ምክንያት ስንዴውን አጓጉዘው ጅቡቲ ያደረሱት ስምንት መርከቦች የተወሰኑት ለሀምሳ ቀናት ; ሌሎቹ እስከ ስድስት ወራት ቀሪዎቹ ከዚህም ላነሰ ጊዜ ጅቡቲ ወደብ ላይ ለመቆም ከተገደዱ በሁዋላ ነው ጭነታቸው አራግፈው የተመለሱት።


መርከቦቹ ለረጅም ጊዜ ጅቡቲ ወደብ ላይ በመቆየታቸው ምክንያት የስንዴ አቅራቢው የብሪታንያው ኢንትሬድ ለጅቡቲ መንግስት መርከቦቹ የወደቡን ክፍል ለያዙበት ወይንም ዲሜሬጅ 4.7 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ; በወቅቱ በነበረ ምንዛሬም 105 ሚሊየን ብር መክፈሉን በክሱ ገልጿል።ክስ የመሰረተባቸው ሶስት የኢትዮጵያ የመንግስት ድርጅቶችም ማለትም ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ; የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ይህን ኪሳራውን እስከ ወለዱና ሌሎች ወጭዎች እንዲከፍሉት ነው ክሱን ያቀረበው።ክሱም ለሶስቱ ተቋማት በኩባንያው ጠበቃ በኩል እሮብ እለት እንደደረሳቸው ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።


በየተቋማቱ ሲታይም የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የተከሰሰው ተሽከርካሪ አቅርቦ ስንዴውን በወቅቱ ባለማንሳቱ ; የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ የግዥው አደራዳራ በመሆኑ እንዲሁም የኢትዮጵያ የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ደግሞ የወደብ ጉዳይ ማስተካከል ሲችል ባለማድረጉ ነው ኢንትሬድ ኩባንያ ላወጣው ወጭ የተጠየቁት።ክስ የቀረበባቸው ሶስቱ ተቋማት ምላሽ እንዲሰጡ 20 ቀን ተሰጥቷቸዋል።ጉዳዩ የሚታየውም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ፍትሀ ብሄር ችሎት መሆኑን ለማወቅ ችለናል።


ከምንጮቻችን እንደተረዳነው ዛሬም ድረስ የ105 ሚሊየን ብር ክስ ያመጣው ስንዴ ስካሁንም ተጠቃሎ ከጅቡቲ ተነስቶ ሀገር ውስጥ አልገባም።ጅቡቲ መጋዘኖች ውስጥ የተከማቸም አለ እስካሁን።

ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት በመነጋገር ሊፈታ ይችል እንደነበርና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በታየ ቸልተኝነት ምክንያትም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቷልም።እንደሰማነው ከሆነ የስንዴ አቅራቢው ኢንትሬድ ኩባንያ ነገሩን በአደራዳሪ ተቋማት እንፍታው ብሎ ጥያቄ አቅርቦ ነበሮ።ነገር ግን ከመንግስት በኩል ፈጣን ምላሽ ባለማግኘቱ ወደ ክስ አምርቷል።

ኢንትሬድ ኩባንያ ለኢትዮጵያ መንግስት በተለያየ ጊዜ ስንዴን አቅርቧል። ተጨማሪ ዘገባ ከታች በዩቲዩብ ያድምጡ

https://youtu.be/5IZHBgJUzj0