ዋዜማ ራዲዮ- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮምሽን እና የኣኢትዮጵያ ስብዓዊ መብት ኮምሽን ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈፀሙ የስብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ለወራት ያዘጋጁትን የምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

ሪፖርቱን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጥ የምርመራ ሪፖርቱን ልከውለታል። የሪፖርቱን ዋና ዋና ግኝቶችንና መንግስት ሪፖርቱን በተመለከተ የሰጠውን ምላሽ ዋዜማ ራዲዮ ተመልክታለች። የምላሹን ጨመቅ በዚህ ዘገባ አቅርበነዋል።

የህወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፣ ሪፖርቱ ከመውጣት አስቀድሞ ባሰራጩት ምላሽ፣ የምርመራውን ሂደትም ሆነ ውጤት እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። ኢሰመኮ በምርመራው መሳተፉ ተአማኒ ምርመራ እንዳይሆን አድርጎታል፣ ምርመራው ሁሉንም ጥፋት የተፈጸመባቸውን የትግራይ አካባቢዎች አላካተተም፣ እንዲሁም ድርጅታቸው ህወሃት በምርመራው ሂደት አልተሳተፈም በሚል ሪፖርቱን አጣጥለውታል።

መንግሥት ለሪፖርቱ በጽሑፍ ከሰጠው መልስ በተጨማሪ ጉዳዩን በቀጣይነት የሚመረመር ልዩ ዐቃቤ ሕግ እና ችሎቶችን ለማቋቋም የሚስትችል ሐሳብ ቀርቦ መምከሩን ሰምተናል። ሐሳቡ ለተጎጂዎች ልዩ የመልሶ ማቋቋም ስርዐት ለመዘርጋት እና ካሳ መክፈልንም እንደሚያጠቃልል ተነግሯል። ይሁንና ይህ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም እቅድ ስለመውጣቱ ለማረጋገጥ አልቻልንም።

መንግሥት በጽሁፍ ለመርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ መግቢያ ላይ፣ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ መርማሪ ቡድኑ በዚህ ውስብስብ ጉዳይ ላይ ሙያዊ ደረጃውን የጠበቀ እና ጥልቀት ያለው የምርመራ ሪፖርት በማዘጋጀቱ እና የምርመራ ሪፖርቱን ረቂቅ መንግሥት አስተያየት እንዲሰጥበት በማድረጉ ምስጋናውን ገልጧል።

በዚሁ ክፍል ስር የትግራዩ ጦርነት በጥቅምት 2013 ዓ.ም ከመቀስቀሱ በፊት፣ መንግሥት የወሰዳቸው አወንታዊ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና አያያዝ ማሻሻያዎች እና መንግሥት እና ሌሎች አካላት ሕወሃትን ወደ ሰላማዊ የውይይት መድረክ ለማምጣት ያደረጓቸው በርካታ ጥረቶች እና ሕወሃት የወሰዳቸው አደገኛ ርምጃዎች እንዲሁም ትንኮሳዎች ተዘርዝረዋል።

ሕወሃት በትግራይ ልዩ ኃይል አማካኝነት ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ድንገተኛ ወይም ተራ ጥቃት እንዳልነበር እና ይልቁንም ሀገሪቱን በማፍረስ ትናንሽ መንግሥታትን በመፍጠር “ታላቋ ትግራይን” ለማወጅ ያለመ እንደነበርም መንግሥት አብራርቷል።

አጣሪ ቡድኑ በሪፖርቱ ላነሳቸው ክስተቶች በየርዕሰ ጉዳዩ ስር መንግሥት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የሚቀበላቸውን እና የማይቀበላቸውን የሪፖርቱን ግኝቶች እና መደምደሚያዎች ያስቀመጠ ሲሆን፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ወይም ድጋሚ ቢፈተሹ ይሻላል ያላቸውን ነጥቦች እና የሪፖርቱ ክፍሎች ጠቃቅሷል።

የመንግሥት ምላሽ መደምደሚያ

በጠቅላላው መንግሥት በምርመራ ሪፖርቱ ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች ወይም ልዩነቶች እንዳሉት ይጠቅስና፣ የሪፖርቱን ግኝቶች በመርህ ደረጃ እንደሚቀበላቸው ገልጧል። አጣሪ ቡድኑ የመንግሥትን ምልከታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት አንዳንድ የሪፖርቱን ድምዳሜዎች እንደገና እንዲያጤናቸው ወይም እንዲፈትሻቸው፣ አንዳንድ የሪፖርቱ ጥቅል ድምዳሜዎች፣ አገላለጾች እና ምክረ ሃሳቦች ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚያስፈልጋቸውም መንግሥት ፍላጎቱን አስቀምጧል።

የሪፖርቱ አንዳንድ ክፍሎች በድጋሚ ቢታዩ ወይም ቢፈተሹ ሪፖርቱ ሚዛኑን የጠበቀ እና ትክክለኛውን ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ሪፖርት ይሆናል የሚል እምነት እንዳለው መንግሥት በምላሹ አክሎ አብራርቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመ እና ሆን ብሎ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለትግራይ ክልል እንዳይደርስ በማድረግ ርሃብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል ሲባል ለቆየው “ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው” ውንጀላ፣ የምርመራ ሪፖርቱ ተጨባጭ ማስረጃ አለማግኘቱን እና ሪፖርቱ መንግሥትን ከወንጀሉ ነጻ ማድረጉን መንግሥት በደስታ እንደተቀበለው በምላሹ ላይ ገልጧል።

በምላሹ መግቢያ እና መደምደሚያው ላይ መንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ፣ ሕወሃት የፈጸማቸው ወንጀሎችን ሪፖርቱ ማካተት አለመቻሉ እና የቡድኑ ምርመራ የጊዜ እና ቦታ ውስንነት ያጋጠመው መሆኑ እንደሚያስቆጭ ገልጧል።

መንግሥት በዚህ ውስንነት ሳቢያ ሳይካተቱ ቀሩ ያላቸው የሕወሃት የመብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች ሕጻናትን፣ ሴቶችን እና አረጋዊያንን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸማቸውን ግድያዎች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን እና ዕድሜያቸው ለተዋጊነት ያልደረሱ ታዳጊዎችን ለጦርነት ማሰለፉን የመሳሰሉ ወንጀሎችን እንደሆነ ጠቅሷል። ሆኖም ምርመራ ሪፖርቱ በሚሸፍነው ጊዜ ውስጥ ሕወሃት ትግራይ ውስጥ የፈጸማቸውን ከባድ ወንጀሎች ሪፖርቱ ማጋለጡ እንዳስደሰተው መንግሥት ሳይጠቅስ አላለፈም።

መንግሥት የምርመራ ሪፖርቱን ግኝቶች መሠረት አድርጎ የመፍትሄ ርምጃዎችን እንደሚወስድ፣ ለተጎጅዎች ማካካሻዎችን እንደሚያመቻች እና የመልሶ ማቋቋም ርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን፣ በተላይ ለጾታዊ ጥቃት ተጎጅዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ እና የጾታ ጥቃት ወንጀል ወደፊት እንዳይፈጸም የሚያስችሉ አሠራሮችን እንደሚዘረጋ እና ለሁሉም ወንጀሎች የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን ቃል የገባ ሲሆን፣ ካሁን ቀደምም ለተጠቀሱት አንዳንድ ወንጀሎች ተጠያቂነትን ማስፈን እንደጀመረ ጭምር አብራርቷል

መንግሥት ምላሹን እና ምልከታውን የሰጠባቸው ግኝቶች

  • በሰላማዊ ሰዎች እና ለሰላማዊ አገልግሎት በሚውሉ ወይም በጦርነት ጊዜ ጥበቃ ሊደረግላቸው በሚገባቸው ተቋማት፣ መሠረተ ልማቶች ወይም አካላት ላይ የደረሱ ጥቃቶችን በሚመለከት፤
    (በዚህ ርዕስ ስር መንግሥት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በገለልተኛነት ለመመርመር ልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም እንደወሰነና፣ የሀገሪቱ ፍርድ ቤትም ለእዚሁ ጉዳይ ራሱን የቻለ ችሎት እንደሚያደራጅ፣ መንግሥት የሽግግር ፍትህ ሥርዓት ለመዘርጋት የጀመረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ የሰላም፣ የዕርቅ እና የፈውስ ሂደት ለማስጀመር ማቀዱን እና ለመብት ጥሰት ተጎጅዎች ካሳ ለመክፈል ማሰቡን ጠቅሷል።)
  • ኅዳር 19፣ 2013 ዓ.ም በመቀሌ የተከሰተውን ክስተት ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በከተማዋ በሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ አካባቢ መድፍ እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ስለመተኮሱ የቀረቡ ግኝቶችን በተመለከተ፤
  • በውቅሮ ከተማ ከኅዳር 16-18፣ 2013 ዓ.ም የተፈጠረውን ክስተት ማለትም በከተማዋ ላይ የተፈጸሙ የመድፍ እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ጥቃቶችን በተመለከተ
  • ሑመራ ላይ ከጥቅምት 30 እስከ ኅዳር 2፣ 2013 ዓ.ም የተፈጠረውን ክስተት በተመለከተ ማለትን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የትግራይ ልዩ ኃይል እና የኤርትራ ወታደሮች ግድያዎችን ፈጽመዋል መባሉን በተመለከተ፤
    (በዚህ ርዕስ ስር መንግሥት በሪፖርቱ የተጠቀሱ ግኝቶችን እንደሚመረምር፣ ወደ ክስተቱ ያመሩ ሁኔታዎችን፣ ድርጊቱ እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ እና የሠራዊቱ እና የትግራይ ልዩ ኃይል ሚና ምን ድረስ እንደሆነ እንደሚያጣራ ጠቅሷል።)
  • በጎንደር፣ ባሕርዳር እና ደባርቅ ከተሞች ከኅዳር 4-5፣ 2013 ዓ.ም የተፈጸሙ የሮኬት ጥቃቶችን እና መንግሥት የባሕርዳር እና ጎንደር አውሮፕላን ማረፊያዎችን በጦርነቱ መጀመሪያ ሰሞን ለወታደራዊ አገልግሎት ተጠቅሞባቸዋል የሚለውን ግኝት በተመለከተ፤
  • በትግራይ ክልል ጊጀት ከተማ እና አካባቢዋ ከታኅሳስ እስከ መጋቢት 2013 ዓ.ም ድረስ መከላከያ ሠራዊት እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባደረሱት ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ሞተዋል መባሉን በተመለከተ፤
  • በማይካድራ ከጥቅምት27-30፣ 2013 ዓ.ም የተፈጠሩ ክስተቶችን ማለትም ሕወሃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸማቸውን ግድያዎች በተመለከተ፤
  • ከጥቅምት 24 እስከ ሰኔ 21፣ 2013 ዓ.ም ሕወሃት በመቀሌ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የፈጸማቸውን በማንነት የመለየት፣ ማስፈራራቶች፣ ጥቃቶች እና ግድያዎችን በተመለከተ፤
  • የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሳምረ እና መቀሌ ከተሞች ትምህርት ቤቶችን እና የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽሕፈት ቤትን ለወታደራዊ ካምፕነት መጠቀሙን በተመለከተ፤
  • በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጦርነቱ ተዋናዮች ከሕግ ውጭ ፈጽመዋቸዋል ስለተባሉት የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎች ሪፖርቱ ያካተታቸውን ግኝቶች በተመለከተ፤
    (በዚህ ርዕስ ስር የኤርትራ ወታደሮች አክሱም ከተማ ውስጥ 100 ያህል ሰዎችን ሲገድሉ፣ በአካባቢው የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግድያውን ለማስቆም ጣልቃ አልገባም መባሉን በተመለከተ መንግሥት የሰጠው ምላሽ ተካቷል።)
  • በደቡባዊ ትግራይ በቦራ አመድዋ፣ ቦራ ጨመላ፣ ማይ ሊሃኒ በተባሉ ቦታዎች 70 ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል መባሉን እንዲሁም በአዲግራት፣ አዲ አውሳ፣ አዲ ጊባይ፣ አዲ ሐውሱን፣ በርዝባህ፣ ሑመራ፣ ውቅሮ እና መቀሌ ሌሎች ግድያዎችን ፈጽሟል መባሉን በተመለከተ
  • የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ አበባ እና ትግራይ ክልል የትግራይ ተወላጅ በሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የዘፈቀደ እስር ፈጽሟል መባሉን በተመለከተ፤
  • የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ክልል ፈጽሟቸዋል የተባሉ የንብረት ዝርፊያ እና ውድመቶችን በተመለከተ፤
  • የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጾታዊ ጥቃት ወንጀሎችን ፈጽሟል መባሉን በተመለከተ፤
  • የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የስቅየት ግርፋት ስለመፈጸሙ እና ሰዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል የሚሉትን የሪፖርቱን ግኝቶች በተመለከተ፤
  • በትግራይ ክልል ሰላማዊውን ሕዝብ በግዳጅ የማፈናቀል ውንጀላን በተመለከተ፤
  • በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና የጦርነት ወንጀሎችን እና የወንጀሉ ፈጻሚዎችን ማንነት በተመለከተ ናቸው።