EMI

Photo- from EMI website

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መርከበኞችን በተመለከተ ከሰሞኑ አስደንጋጭ የሆኑ መረጃዎች ሲሰሙ ቆይቷል ።
የሀገሪቱ መርከበኞች ከመርከብ ላይ እየኮበለሉ መጥፋት ለሀገሪቱ ከባድ ፈተና ሆኗል ፤ በሥራቸው ላይ የነበሩ ሠማንያ ያሕል ኢትዮጵያውያን መርከበኞች በመጥፋታቸው የተነሳ 10 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አዳዲስ መርከበኞችን መቅጠር አቁመዋልም ተብሏል ። ይህም ብቻ ሳይሆን 1050 መርከቦች ያሏቸው 30 ካምፓኒዎች የሥራ ግንኙነት ስለማቋረጣቸው ፤ 200 የኢትዮጵያ ባሕረኞች ከሥራ መባረራቸውም ጭምር ተሰምቷል ።

አመኔታ በማጣት 340 አዳዲስ ተመራቂዎች ሥራ ማግኘት አልቻሉም፤ ኢትዮጵያም ከባሕረኞቹ በየወሩ ታገኝ የነበረውን 450 ሺህ ዶላር የውጪ ምንዛሪ አጥታለች፡፡

አዲሱ የሀገሪቱ አስተዳደር ከኤርትራም መንግስት ጋር ተደራድረሮ ሀገሪቱን የተሻለ ወደብ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚሰራበትም በአሁን ጊዜ ለዘርፉ ተስፋ የሆኑ ሙያተኞች በዚህ ደረጃ እንዴት ስራቸውን ጥለው መጥፋትን ተያያዙት ? የዘርፉ ችግርስ ምንድነው የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም ።

ከመረጃ ምንጮቻችን እንዳገኘነው ኢትዮጵያ ውስጥ መርከበኝነትን ሰልጥኖ ስራ ውስጥ እስካለሁ ሁኔታ ድረስ እጅግ በችግር የተሞላ ነው ።

የመርከበኝነትን ሙያ በተለያዩ የምህንድስና መስኮች ላይ የተመረቁ በተለይም መካኒካል ምህንድስና የተማሩ ወጣቶች በብዛት የስድስት ወር ስልጠናን ወስደው የሚቀላቀሉት ነው ።

ስልጠናውን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠጠው የኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬኒንግ አካዳሚ የተባለ ተቋም ሲሆን ፤ በአሜሪካውያን ባለቤትነት የተያዘ እና እስራኤለውያንም የሚያንቀሳቅሱት ነው ።

ተቋሙ ቢሮውን በአዲስ አበባ አድርጎ በባህር ዳር ስልጠናውን ይሰጣል ፤ በሌላ በኩል በደብረዘይት ያለው በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት አገልግሎትና ሎጀስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ስር ያለውና አነስተኛ የመርከብ ስራዎች ላይ ግፋ ቢል ለሶስት ወራት ስልጠና የሚሰጠው ተቋም በተፈጠሩ ችግሮች ስልጠና አቁሟል ።

በባህር ዳር ያለውም የኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬኒንግ አካዳሚ እጅግ ብዙ ቅሬታ የሚበዛበት ነው ።

ጀማሪ መርከበኛ ወይንም ካዴት ለመሆን ወደዚህ ተቋም ለስልጠና የሚገቡት ወጣቶች ከቅጥር በፊት የሚሰጣቸው ውል ወደ አንድ ወገን ማለትም ለአሰልጣኙ ድርጅት ያደላ እና በምንም መልኩ የባህረኛውን መብትና ጥቅም የማያስከብር መሆኑ ይነሳል ።

ችግሩ ሰልጣኞች ስድስት ወር ሰልጥነው ስራ ሲገቡ ለሚከፍሉት የመሰልጠኛ ዋጋ ውል ሲገቡ ይጀምራል ።

መርከበኛ ለመሆን የሚሰለጥኑት ወጣቶች ለ6 ና 8 ወር ስልጠና ከ30 እስከ 34 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የእዳ ውል ይገባሉ ። እዳውን በስራ ላይ እንዲከፍሉ በማሰብ ማለት ነው ።

ሠልጥነው የወጡና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ወጣቶች የመሰለጠኛ ዋጋው በራሱ እጅግ ውድ እንደሆነ ይናገራሉ ።
የመርከብ ስልጠናው የተጀመረው በምህንደስና ዘርፍ የተመረቁ ወጣቶችን ስራ አጥነት ለመቀነስ ታስቦ ሲሆን የድህነት ቅነሳ አካልም ነው።ለዚህ አላማ የታሠበ ነገር በዚህ ደረጃ መወደዱ ጥያቄ ያስነሳል።

በዛ ላይ ሰልጣኞቹ ስራ ሲይዙ ኢንስትቲዩቱ ሰልጣኞች እዳቸውን እስኪጭርሱ ዶክመንታቸውን ይዞ ፤ ከወር ደሞዛቸው ላይ ሀምሳ በመቶውን በየወሩ ይወስዳል ።

ይህ እጅግ ውድ ከመሆኑም በላይ እጃቸውም ላይ የሚቀረው ገንዘብ ለኑሯቸው በቂ እንዳልሆነ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ።

ሁኔታው በተለይ ለአዲስ ተቀጣሪዎች ከባድ መሆኑ ይነሳል።

አዲስ መርከበኛ ወይንም ካዴት ስራ ካገኘ በወር አንድ ሺህ ዶላር ይከፈለዋል።

በኢትዮጰያ በባንክ ሲመነዘር 27 ሺህ ብር የሆነ ገንዘብ ግማሹ ለእዳ ቢከፈል ቀሪው ለመኖር በቂ አይደለም ወይ ? ብዬ ጠይቄያለሁ።

አንድ ቅሬታ አቅራቢ እንዳለኝ ታድያ ችግሩ ስራው ቋሚ አለመሆኑ ነው ብሏል።

ለምሳሌ ከአንድ ወደብ ሌላ ወደብ ድረስ ኮንትራት ስራ ካገኘሁ አንድ ሺህ ዶላር ከተከፈለኝ ግማሹን እዳ ከከፈልኩ በሁዋላ ከዚያ በሁዋላ ለስድስት ወርና ለአንድ አመት ላላገኝ እችላለሁ ።

ከእዳ በቀረኝ ገንዘብ ደግሞ ይህን ያክል ጊዜ ወጭ መሸፈን እንደማይችል ነግሮኛል።በወር ለስልጠናው የሚከፈለው እዳ ምጣኔ ቀንሶ በረጅም ጊዜ እንክፈል ወይንም የስልጠናው ወጭ ይቀንስ ብለው ከመቶ በላይ ወጣቶች ለኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን አቤቱታ ቢያቀርቡም አሠልጣኙን ተቋም የሚያስገድድ የመንግስት አለመገኘቱንም ይናገራለ።ተቋሙ ከመንግስት አካልት ጋር የጥቅም ግንኙነት መፍጠሩንም ይጠረጥራሉ።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬኒንግ ኢነስቲትዩት የተባለው ተቋም ደግሞ በተለያየ ሀገራት ካሉ መርከብ ድርጅቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላለው ከተቋሙ ጋር ፊት ለፊት መጋጨት ብዙ ጣጣ ያመጣብናል ብለው ይፈራሉ ፤ ቶሎ ቶሎ ስራ አለመገኘቱም ትልቅ ችግር ነው።

ሌላው ችግር ደግሞ መሀንዲሶቹ ሠልጥነው ሲጨርሱ ስራ የሚያስቀጥራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚመለከተው አካል ፍቃድ ያገኘ ህጋዊ ኤጀንሲ አለመኖሩ ነው።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሠልጣኞችን የሚየስቀጥር ኢትዮጵያን ማኒንግ ኤጀንሲ የሚባል ድርጅት አለ።ይሄ ኤጀንሲ የእስራኤል ኩባንያ ሲሆን ከአሰልጣን ተቋሙ ጋር በቅርበት የሚሰራ እንደሆነ መረጃ አለ ።

ግን ፍቃድ የሌለው ህገ ወጥ እንደሆነ ተረጋግጧል ።

ምክንያቱም ኤጀንሲው ስራ የማስቀጠር ፍቃዱን ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማግኘት ከኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት አለበት።ነገር ግን ኤጀንሲው ምንም አይነት ማረጋገጫ ከባለስልጣኑ አለማግኘቱን አረጋግጫለሁ።

ይሄ ደግሞ ስጋት ባለበት የመርከብ ስራ ላይ ኢትዮጵያውያን ችግር ቢገጥማቸው መንግስት ተጠያቂ የሚያደርገው አካል እንዳይኖር አድርጓል።

መርከበኞች ከሚሠሩበት መርከብ ላይ ሲጠፉ በተደደጋሚ የታየውም ይህው ነው ።ኢትዮጵያውያን መርከበኞች በሚደርስባቸው በደሎችና በሌሎች ምክንያቶች የሚሠሩበት መርከብ የሆነ ወደብ ላይ ሲደርስ ይጠፋሉ።

በዚህ ጊዜ ታድያ አንድ ኢትዮጵያዊ መርከበኛ ከጠፋ የመርከቧ ሀላፊዎች በስመ ኢትየጵያዊ መርከቡ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ወደ ሀገራቸው መመለሻ ትኬት ብቻ ቆርጠው በሙሉ እዛው ወደብ ላይ ይጥሏቸዋል ፤ ያለ ምንም ክፍያ ።ይህ ብዙ ጊዜ አጋጥሟል። ይህ ሁሉ ሲሆን ታድያ ተጠያቂ የለም።

በሌላ በኩል በትምህርትም በብቃትም የሚወዳደሩ ሀበሻዎች እያሉ በማሰለጠኛ ተቋማት የሚያሰተምሩት ህንዶች ናቸው ። ስለዚህም በቂ የሆነ የሀበሾችን ባህልና እሴት መሰረት ያደረገ ስልጠና ሳይሰጥ ወደ መርከብ መላካቸው ተጽእኖ እንዳመጣ ይነገራል ።

ወጣቶች ከሰለጠኑም በኃላ ወደ መርከብ ሲላኩ በሚያሳፍር መንገድ በሰለጠኑበት ሳይሆን ተራ ተላላኪና የ ቆሻሻ አፅጂ ሆነው እንዲሰሩ ሲገደዱም ይታያል ።

ባህረኞች የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ናቸው ። ሆኖም ደሞዝ በዶላር እየተከፈላቸው ፣ ነገር ግን ሀገር ውስጥ በዶላር ሂሳብ መክፈት እንዳይችሉ ተደረጎ እነሱ ያመጡት ምንዛሬ አግባብ ባለሆነ መልኩ ለሌላ አካል ጥቅም ላይ መዋሉ ተገቢ አለመሆኑም ይነሳል ።

ከዚህ በተቃራ ግን የቅሬታ አቅራቢዎቹን ችግር የሚሰማ አካል ካለመኖሩ ባሻገር ቅሬታ ያነሱ ልጆች በሆነ መንገድ ጥቅማቸው እንዲነካ ይደረጋል ። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/kCPibGbzRiQ