HT

የኢትዮዽያ የብየነ መረብ ደህንነት ተቋም ወይም በፈረንጁ ቃል INSA ገልቱ መስሪያቤት ነው ሲል የራሱ የስለላ ሸሪክ ወነጀለው። ኢንሳ የኢሳት (ESAT) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነዐምን ዘለቀን ለማጥመድ ብዙ መድከሙን የሚጠቁም መረጃ ይፋ ሆኗል።

“ሌባን ሌባ ቢሰርቀው ምን ይደንቀው” ይሚለው ብሒል በጣልያኑ የኢንተርኔት የስለላ ቡድን (ሃኪንግ ቲም)ላይ ደርሶ የሰሞኑ ዋና ዜና ኾኖ ሰንብቷል። ሃኪንግ ቲም ባላሰበው ኹኔታ የመረጃ ቋቱ ለመበርበርና በሰበቡም ከቡድኑ ጋር ደምበኝነት የነበራቸው አምባገነን መንግስታት እና የስለላ ድርጅቶቻቸው ምስጢር የባቄላ ወፍጮ ለመኾን በቅቷል።
ከዚህ የስለላ ቡድን ጋር ውል የነበረውም የኢትዮጵያው “የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ” ሚስጥራቸው ከተጋለጠባቸው ድርጅቶች አንዱ ነው። የዚህን የስለላ ቡድን መጋለጥ ዜና የተከታተለው መዝገቡ ኃይሉ በጉዳዩ ዙሪያ የሚከተለውን አዘጋጅቷል።አድምጡት

ለኢትዮጵያው የኢንተርኔት የስለላ ድርጅት (INSA)የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርገው ኢጣሊያዊው ኩባንያ (Hacking Team) መጋለጡ ለብዙ የመብት ተሟጋች ቡድኖች አስደሳች ዜና ነበር።
ይህ “Hacking Team” የተባለ ድጅት የመረጃ ቋቱ በመከፈቱ ምክንያት 400 ጊጋ ባይት የሚያህል መጠን ያላቸው ሰነዶቹ ይፋ ኾነውበውታል። ይፋ ከወጡትም መረጃዎቹ መካከል፤ በቡድኑ አባላት መካከል ውስጥ ለውስጥ ይደረጉ የነበሩ የኢሜይል መልእክቶች፣ ከደምበኞቻቸው ጋር ያደረጓቸው የመልእክት ልውውጦች እና ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የክፍያ ሰነዶች ይገኙባቸዋል። በደምበኝነት ወግ መሠረት በከፍተኛ ምስጢርነት ሲጠበቁ የቆዩትም የደምበኞቹ ዝርዝር እና ከቡድኑ ያገኙትም የነበረው የስለላ ድጋፍ ፀሐይ ሞቋቸዋል።
ኢትዮጵያን ከመሰሉ አምባ ገነን መንግስታት ጋር ደምበኝነት የለኝም እያለ ሲገዘት የነበረው ሃኪንግ ቲም፤ አሁን ይፋ በኾነው መረጃ መሰረት ከደምበኞቹ መካከል አብዛኞቹ የሰብአዊ መብት ረገጣን በተመለከተ በሚወጡ ሪፖርቶች ላይ ተጠቃሽ የኾኑ አፋኝ መንግስታት እንደኾኑ ተጋልጦበታል።
የኢትዮጵያውን የበይነ መረብ ስለላ ድርጅት (INSA)በተመለከተም የፋ የኾኑት መረጃዎችም ጉዳዩን ይዘገቡትን መገናኛ ብዙኀን ትኩረት የሳቡ ነበሩ። ኢንሳ የ ሃኪንግ ቲም ቋሚ ደምበኛ መኾኑ ከመጋለጡም በተጨማሪ በአንድ ወቅት ለተቀበለው አገልግሎት የከፈለው የ 1 ሚሊዮን ዶላር የክፍያ ሰነድም ይፋ ከኾኑት ሰነዶች መካከል ይገኝበታል። የኢሳት ማኔጂንግ ኤዲተር የኾነውን ነአምን ዘለቀን ለማጥመድ ያደረጓቸውም ተደጋጋሚ ሙከራዎች የዚሁ የ ሃኪንግ ቲም አፍራሽ ሥራ ዋነኛ ምሳሌም ኾኖ ቀርቧል።
ከዚህ ቀደም ኢሳትን በተመለከተ ተመሳሳይ መጋለጥ ካጋጠመው በኋላ ቡድኑ ጉዳዩን እንደሚያጣራ እና እንዲህ አይነት ደምበኝነት ከኢትዮጵያም ኾነ ከሌሎች በሰብአዊ መብት ረገጣ ከሚታወቁ አገራት ጋር እንደማያደርግ ቃል ቢገባም፤ ይህ ቡድን እስከ አሁን ድረስ ለአምባ ገነን መንግሥታቱ ድጋፍ ማድረግ መቀጠሉንም ይፋ የኾኑት መረጃዎች ያሳያሉ። ከደምበኞቹ ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ኢንሳም እስከ ኦክቶበር 31፣ 2015 ድረስ የታደሰ ደምበኝነት እንዳለውም የታያል።
የከዚህ በፊቱ መጋለጥ ባስከተለው ውዝግብም ምክንያት በኢንሳው ተወካይ በ አቶ ቢንያም ተወልደ እና በቡድኑ ተወካይ በ ዳኤል ሚላን መካከል የተደረገ የኢሜይል ልውውጥ እንደሚያሳየው አቶ ቢንያም የነአምንን የጥቃቱ ኢላማ መኾን ከጋዜጠኝነቱ ጋር የማይገናኝ እንደኾን ለማሳመን ጥረት ሲያደርጉም እንደነበረ ለማየት የቻላል።
በቡድኑ መካከል ከተደረጉትም የኢሜይል ልውውጦች ለመረዳት እንደሚቻለው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሥራ ግንኙነት ለመቀጠል ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ እና ቅድመ ኹኔታም የዘረዘሩበት መልእክታቸው በአፕሪል 16፤ 2015 የተጻፈ በመኾኑ ግንኙነቱ እስካሁን ቀጥሎ እንደነበረም የሚያሳይ መረጃ ኾኖ ቀርቧል።
የትኛውን ኢላማቸውን ለማጥመድ እንደቻሉ ለማወቅ ባይቻልም፤ አቶ ቢንያም ተወልደ በአንድ ኢሜላቸው ላይ ስኬታማ እንደነበሩ በመግልጽ ምስጋናቸውን ለቡድኑ ሲያቀርቡም ይታያል። ይኹንና ብሃኪንግ ቲም አባላት መካከል በነበረው የኢሜይል ልውውጥ ውስጥ ለቡድኑ ሥራ መጋለጥ እንደምክንያት ሲቀርብ የሚታየው የ ኢንሳ አላዋቂ አጠቃቀም እንደነበረም ለመረዳት ይቻላል። “የደምበኛችን ጭፍን እና ገልቱ አጠቃቀም” ችግር ፈጥሮብናል ሲሉም ይነበባል። ያም ኾኖ በዚህ ቡድን የሚሰሩት ሶፍት ዌሮች ለአጠቃቀም ቀላል እና የተክኒክ እውቀት በሌለው በማንኛውም ሰው ሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉም እንደነበሩ በድረ ገጻቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ራሱን አይነኬ እና ቁጥር አንድ አድርጎ ይቆጥር የነበረው ይኽው “ሃኪንግ ቲም” የተባለ በድን ለደምበኞቹ መንግሥታት እና የስለላ መዋቅሮቻቸው የሚሰጠው የቴክኒክ ድጋፍ፤ መንግሥታቱ ሊያጠቋቸው የሚፈልጓቸውን ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በሩቅ ርቀት ለመከታተል የሚያስችላቸው ደጋፍ ነው።
እነኚህ ሶፍት ዌሮች በቀላሉ በኢሜይል አማካኝነት ወደ ኢላማቸው ተልከው በስፓይዌርነት ከበከሉት በኋላ በዒላማቸው ኮምፒውተሮች ወይም ስልኮች ላይ በመኾን ማንኛውንም በኮምፒውተሩ ወይም ብስልኩ ላይ ያለውን መረጃ የመስረቅ ችሎታ አላቸው። በኮምፒውተሩ ወይም በስልኩ ላይ ያሉ ካሜራዎች በመጠቀምም ዒላማቸውን ለመከታተል የሚስችል ተግባርም አላቸው። በኢሜይል ሲላኩም የወዳጅ ወይም የሥራ ጉዳይ በመሰሉ ኢሜይሎች ላይ አባሪ ወይም (attach)ተደርገው የሚላኩ ናቸው። ዒላማው እነኚህን አባሪዎች ከከፈታቸው በቀላሉ በኮምፒውተሩ ወይም በስልኩ ላይ ለመጫን ይችላሉ። በተለመዱት አንቲቫይረሶች እንዳይገኙ የሚያደርግ አሠራር ስላላቸው ብዙውን ጊዘ በቀላሉ የማይታወቁ ስፓይዌሮች ናቸው።
ሃኪንግ ቲም ከተጋለጠ በኋላ በላከው መረጃ መሠረት፤ ሃክ መደረጉን አምኖ ደምበኞቹ ከዚህ በኋላ በቡድኑ የተሰጧቸውን ሶፍትዌሮች እንዳይጠቀሙ ተማጽኗል። የቡድኑ የኢሜይልና የቲውተር አካውንት ማንነታቸው እስካሁን ባልተገለጸው አጋላጮቹ እጅ በመውደቁ ከዚህ ብኋላ ይህ ቡድን እነኚህን መገናኛዎቹንም ኾነ መረጃዎቹን ሊያገኛቸው እንዳልቻለ ባስተላለፈው ጥሪ ላይ አስታውቋል።