Ms. Frehiwot Tamiru, CEO of EthioTelecom , Photo – Fortune Addis

ዋዜማ ራዲዮ- አርባ በመቶ የባለቤትነት ድርሻውን ለውጪ ኩባንያዎች ለመሸጥ በሂደት ላይ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም ተጫራቾቹ እያሳዩት ባለው የኩባንያውን የአመራር ሰጪነት የመቆጣጠር ፍላጎት ጨረታውን ለማራዘም ሳይገደድ እንደማይቀር ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ሰምታለች።

ከ120 አመታት በላይ በኢትዮጵያ መንግስት እጅ ሲተዳደር የቆየው የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለዓለማቀፍ ባለሀብት ድርጅቶች በጨረታ ሽያጭ ለማስተላለፍ በተጀመረው እንቅስቃሴ ውስጥ በኩባንያው ጨረታ ላይ ለመሳተፍ የፈለጉ ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻን ከገዙ በኋላ በኩባንያው አመራር ውስጥ የወሳኝነት ሚና እንዲኖራቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

ይህም የኢትዮጵያ መንግስት የኩባንያውን ድርሻ ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ ከፈለገበት አላማ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ምናልባትም ጥር ወር ላይ ሊወጣ የታሰበው የኢትዮ ቴሌኮም ጨረታ ሊዘገይ እንደሚችል ከከፍተኛ የመንግስት ሹማምንት ሰምተናል።

የገንዘብ ማኒስቴር እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ኤጀንሲ በጋራ እየሰሩት ባለው የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ድርሻ ሽያጭ ሂደትን ለማከናወን መስከረም ወር ላይ የኩባንያውን ድርሻ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው አለማቀፍ ኩባንያዎች እቅዳቸውን እንዲያስገቡ ማስታወቂያ በመንግስት መውጣቱ ይታወሳል።

ጥር ወር ላይም የኩባንያው ሽያጭ ጨረታ እንደሚወጣ መዘገቡ የሚታወስ ነው። ሆኖም በኢትዮ ቴሌኮም የ40 በመቶ ድርሻ ሽያጭ ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አለን ያሉት ኩባንያዎች በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ የሚኖራቸው የወሳኝነት  ደረጃ ላይ ያቀረቡት ሀሳብ መንግስት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለግል ለማዞር ካለው አላማ ጋር የሚጻረር መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዋዜማ ራድዮ ምንጮች ነገረውናል።

ጨረታውን ለመካፈል የፈለጉት ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ብንገዛ በኩባንያው የስራ አመራር ውስጥ የዋና ስራ አስፈጻሚነት ቦታን ጨምሮ መሰል የስልጣን እርከኖችን ይካተትልን ማለታቸውን ምንጫችን ነግረውናል።

ታዲያ ይህን ጥያቄ መንግስት እንዴት ያየዋል? ብለን ለመንግስት ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ሐላፊ ላቀረብነው ጥያቄ ያገኘነው ምላሽ “እኛ ይህን የምናየው ኢትዮጵያውያን ኩባንያን መምራት አትችሉም እንደማለት ነው ። ወሳኝ የቴሌኮም ኩባንያ አመራር ቦታዎችን ለውጭ ኩባንያ መስጠት ማለት የሉአላዊነት ጥያቄም ነው።  መንግስት ይህ ፍላጎት ቢኖረው ቀድሞም በሆን አብላጫውን ድርሻ ለራሱ አስቀርቶ የሚሸጠውን ድርሻ ማሳነስ ባለስፈለገው ነበር ”  ብለውናል።

“በጨረታው ለመሳተፍ የሚፈልጉት ኩባንያዎች ፍላጎት የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ አንጡራ ሀብት ላይ ያለው ወሳኝነት ዝቅ እንዲልና ብዙ ተያያዥ ችግሮችን ሊያመጣ የሚችል ነው” ይላሉ ሐላፊው። ይህ አቋም በመንግስት በኩል መግባባት የተደረሰበት ስለመሆኑ ግን ባለስልጣኑ ማረጋገጫ አልሰጡንም።

ጨረታ የማውጣት ሂደቱ ያለበት ደረጃም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ለውይይት የሚቀርብ እንደሆነም አንስተውልናል።

የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመግዛት ከፈለጉት ኩባንያዎች መካከል ግን የትኛው ኩባንያ ይህን ሀሳብ እንዳቀረበና ፍላጎት ያሳዩት ኩባንያዎች ስምና ብዛታቸውን ከጨረታው ስነምግባር አንፃር መግለፅ እንደማይቻል የመረጃ ምንጫችን ገልጸውልናል።

ሆኖም የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመግዛት ይፈልጋሉ በሚል ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አለማቀፍ ኩባንያዎች መካከል የፈረንሳዩ ኦሬንጅ ይገኝበታል። ይኸው ድርጅት ከዚህ ቀደም የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመግዛት እንደሚፈልግ ገልጾ ያውቃል።  የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና የቱርክ ኩባንያዎችም ተመሳሳይ ፍላጎት ማሳየታቸው ተሰምቷል። 

ኢትዮጵያ መንግስት 55 በመቶ የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻን በራሱ ይዞ 5 በመቶውን ፍላጎት ላላቸው ኢትዮጵያውያን አክስዮን ሽጦ ቀሪ 40 በመቶውን ደግሞ ለውጭ ገበያ ለመክፈት ዕቅድ አለው። 

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ለሁለተኛ የግል የቴሌኮም አንቀሳቃሽ ኩባንያ ፍቃድ ለመስጠት ያወጣውን ጨረታ መሰረዙ የሚታወቅ ነው።ከዚህ ቀደም ሳፋሪ ኮም የሚመራው ጥምረት በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሳተፍ በ850 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ፍቃድ ማግኘቱ የሚታወስ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]