ali suleimanየፌዴራሉ የሥነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን የመዘገበውን የመንግስት ባልስልጣናትና ኃላፊዎች የሀብት መጠን በድረገጽ ይፋ ሊያደርግ እንደኾነ አሳውቋል። ይህም ዜና ከዚህ በፊት ኮሚሽነሩ አቶ አሊ ሱሌይማን በተደጋጋሚ ተጠይቀው ይሰጡት ከነበረው ምላሽ የተለየ ነው ።

የኮሚሽነሩን ተደጋጋሚ መግለጫዎች እና ቃለ መጠይቆች ለሚከታተሉ ሁሉ ይህ አዲስ ርምጃ ለምን እንደተከሰተ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ገለልተኛ ተቋማትና መገናኛ ብዙኀን በተለያዩ ሰበቦች እንዳይኖሩ በተደረገባት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የኮሚሽኑ ሕልውናም በመንግስት በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ እንደኾነ በመገመት ገለልተኝነቱን የሚጠራጠሩ ብዙዎች ናቸው። (መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝሩን አዘጋጅቶታል እዚሁ ያድምጡት)


ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ከ1993 ዓም ጀምሮ ርምጃ የወሰደባቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥር ውሱን ናቸው። ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ በሙስና የተከሰሱ ባለስልጣናት ከገዢው ፓርቲ ጋር በአቋም ባለመስማማት ተቃውሞ ያሳዩ ሰዎች በመኾናቸው እንደፍርድ ቤቶቹ ሁሉ ይህም ተቋም የገዢው ፓርቲ መጠቀሚያ መሳርያ ተደርጎም ይታያል። ለዚህም በመጀመርያ ወቅት የነ ታምራት ላይኔ ቀጥሎም እነ የነስዬ አብረሃ ክሶች እንደማሳያ ዪጠቀሳሉ ፡፡

እስከዛሬ ድረስ እንደሚታየው ኮሚሽኑ በራሱ ስልጣን በሙስና የሚጠረጠሩ ባለስልጣናትን በመመርመር ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ ገዢው ፓርቲ ውስጥ ለውስጥ በሚያደርገው ሽኩቻ የሚወድቁለትን ቀን የጣላቸው ባለስልጣናት እስኪመጡለት የሚጠብቅ ይመስላል።
ይህንኑ የሰሞኑን የሀብት ምዝገባ ይፋ መኾንም በተመለከተ ይፋ የሚኾንበት አሰራር በእጅጉ የተገደበ እንደሚኾን ነበር የገለጹት። እንደኮሚሽነሩም አባባል የባለስልጣናቱን ሀብት በመገናኛ ብዙኀን ይፋ ማድረግ በአዋጅ የተከለከለ እንዲሁም በስነምግባርም መርህ ተቀባይነት የሌለው ነውር ነው ብለው ነበር።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አባዲ ደግሞ በቅርቡ ሌላ መግለጫ ሰጥተዋል። የአቶ ብርሃኑ መግለጫ የሚይዝላቸው ከኾነ ኮሚሽኑ የመዘገበውን የ 95,000 የመንግስት ተሿሚዎችና ተመራጮች ሀብት በድረ ገጽ ይፋ ያደርገዋል።
ኮሚሽነሩ አቶ አሊ በአንድ ወቅት ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ዛቻና ማስፈራርያ እየደረሰባቸው እንደኾንና በክልል ያሉ ጽሕፈት ቤቶቻቸው በባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ሥራቸውን መስራት እንደተቸገሩ የገለጹበትም ጊዜ ነበረ።

ብዙ ሙስና እንዳለ በሚነገርበት አገር ኮሚሽኑ በ15 ዓመት ሥራው አስመልሼዋለሁ ብሎ ከስኬት የሚቆጥረው ገንዘብና ንብረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። 127 ሚሊዮን ብርና ጥቂት ቤትና ንብረት ብቻ ናቸው እንደስኬት የተቆጠሩት።

ተጠያቂነት የሌለበትና ፓርቲው በውስጥ አሰራሩ ይቅር የሚላቸው አጥፊ ባለስልጣናት ጉዳይ ሳይመለስ እንዲሁም ነፃ ማኅበራት፣ ነፃ ፍርድ ቤት እና የመገናኛ ብዙኀን በሌሉባት አገር አሁንም ቢኾን የሐብት ምዝገባውና ይፋ የመኾኑ ጉዳይ የሚያመጣው ለውጥ ብዙም አይታይም። ያም ኾኖ ይህ የሀብት ምዝገባ ውጤት ይፋ መኾኑ ብዙዎች የሚጠብቁት ጉዳይ ነው።