EPRDF logo(ዋዜማ ራዲዮ)–ገዥው ድርጅት ኢህአዴግም ሆነ የሚመራው መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀውስ ውስጥ እየገባ ነው፡፡ በተለይ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ባለበ በጥቂት ወራት ውስጥ በመጠነ-ሰፊ ችግሮች ተወጥሮ ከርሟል፡፡ መጠነ-ሰፊ ድርቅ፣ ህዝባዊ አመፅ፣ አስተዳደራዊ እና የማንነት ህዝባዊ ጥያቄዎች፣ ብሄረሰብ ግጭት፣ ወዘተ ሰንገው ይዘውት ከርመዋል፡፡ እንኳን ተራው ህዝብ እና ታዛቢዎች መንግስት ራሱ ሀገሪቱን ወዴት አቅጣጫ እየወሰዳት እንደሆነ ያውቃል ወይ? የሚለው ነገር አጠራጣሪ ከሆነ ከራርሟል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም የሚመሩት ፓርቲና መንግስት የሚሽከረከረው ከጀርባ በመሸገ አንጃ ሲሆን አሁን ፍጥጫው የፓርቲውንና የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተንበት ደረጃ ላይ መድረሱን ብሎም ወደ ለየለት ሽኩቻ መሸጋገሩን መመልከት ይቻላል። አርጋው አሽኔ በጉዳዩ ላይ ያሰናዳውን ዘገባ እዚህ በድምፅ ያገኙታል

ለመሆኑ የገዥው ድርጅት እና የሀገሪቱ ዋና ዋና ወቅታዊ ቀውሶች የትኞቹ ናቸው? ኢህአዴግ-መራሹ መንግስትስ ምን ዓይነት ምላሾች እየሰጠ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመርመር ይገባል፡፡

ቻላቸው ታደሰ ጉዳዩን ዘርዝሮ ያሰናዳው ዘገባ እነሆ በድምፅ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ  የአመራር ቀውስ እና አደጋን መጋፈጥ የጀመረው ከአቶ መለስ ህልፈት ማግስት ነው፡፡  ምንም እንኳ እዚህ ግባ የሚባል መሰንጠቅ ባያጋጥመውም ቡድናዊ አመራርን መልሶ መትከተሉ ግን የአመራር ቀውስ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በድህረ-መለስ ዘመን ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ከመጀመር ይልቅ ለጥብቅ ፖለቲካዊ ስልጣን ድልድል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡

ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉት ፕሮፌሰር ሬኒ ሌፎርት በተለይ ለጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪነት የተመደቡት የድርጅቱ አንጋፋ መሪዎች ከመጋረጃው በስተጀርባ ተሰግስገው ከሚንስትሮች ስልጣን በላይ እንደያዙ ያስረዳሉ፡፡ የተሰባሰቡበት የፖሊሲ ማዕከል ግን መንግስትን ከቀውስ አልታደገውም፡፡ በዚህም የተነሳ ፕሮፌሰር ሌፎርት ሀገሪቱን “አቅጣጫ የጠፋባት፣ ካፒቴን ያጣች መርከብ” አድርገው ይስሏታል፡፡ ብዙ ታዛቢዎችም በፕሮፌሰሩ አገላለፅ ይስማማሉ፡፡ አካሄዱ ለሀገሪቱ ውስብስብ ችግሮች የሚመጥን አዲስ አመራር በማፍለቅ ተስፋ ላይ በረዶ ቸልሶበታል፡፡  

ህወሃትም በትግራይ ያለው የቅቡልነት ክፍተት ቀስ በቀስ በግልፅ መታየት ጀምሯል፡፡ በተለይ ከዓመት በፊት የህወሃት አንጋፋ መሪዎች ዘለግ ላሉ ቀናት በትግራይ ወረዳዎች እየተዘዋወሩ የህዝቡን ምሬት ማዳመጣቸው ማህበራዊ መሰረታቸው እየተናጋ ለመሆኑ አመላካቺ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ አዲስ አበባ እና መቀሌ ባሉት የህወሃት አመራሮች መካከልም ወጥ አቋም እንደሌለ ውስጥ አዋቂቆች ይገልፃሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በትግራይ አንዳንድ ወረዳዎች አስተዳደራዊ እና የአከላለል ጥያቄዎች እየበረከቱ መምጣታቸው በመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡

 ገዥው ግንባር ማህራዊ መሰረቱን ለማስፋት በማሰብ ፈራ ተባ እያለ ወደ ውህድ ፓርቲ የመቀየር ፍላጎት እንዳለው ፍንጮችን ሲሰጥ ቢቆይም በተግባር ግን አንዳችም እርምጃ መራመድ አልቻለም፡፡ ባሁኑ ድርጅታዊ ቁመናው ግን ሀገሪቱን እየመራ መቀጠል እንዳልቻለ በግልፅ እየታየ ነው፡፡ ራሱም በይፋ ማመን ጀምሯል፡፡ ይህ ውልውልም ውስጣዊ ድርጅታዊ ቀውስ ውስጥ  እያስገባው እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡

 አውራ ማጣትና መዋለል

የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት በአንድ ፖለቲካ ድርጅት ውስጥ አወንታዊ ለውጥ የሚመነጨው ለውጥ አቀንቃኝ ልሂቃን ከውስጡ ሲፈጠሩ ብቻ ነው፡፡ በኢህአዴግ ሰፈር ግን ለውጥ ለውጥ የሚሸቱ እንቅስቀሴዎች ኮሽታቸውም አይሰማም፡፡ ለውጥን ለማስተናገድ ያለው መዋቅር የተኮላሸበት ይመስላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የትኞቹ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ለውጥን እንደሚሹ፤ የትኞቹ ነባራዊ ሁኔታውን ማስቀጠል እንደሚፈልጉ ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በድርጅቱ አሰራር መሰረት ከመጋረጃው ጀርባ ስልጣኑን እንደሚዘውሩት የሚገመቱት የህወሃት ቱባ ባለስልጣናት ለለውጥ ዝግጁ ከሆኑ ግን እምብዛም የሚያግዳቸው እንቅፋት እንደማይኖር በርካታ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ 

እንዲህ ዓይነት ድርጅታዊ ድብታ በድንገት ወደ ድርጅታዊ መሰንጠቅ ሊያመራም ይችላል፡፡ በድርጅቱ ላይ የሚከሰት ቀውስ ደሞ በሀገሪቱ መፃዒ ዕጣ ፋንታ ላይ ቀጥተኛ አንድምታ እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም፡፡ አንድ ገዥ ድርጅት በራሱ አነሳሽነት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ካልተገበረ ህዝባዊ አመፅ፣ ሽምቅ ውጊያ ወይም ጦርነት የመሳሰሉ ቀውሶችን ሊጋብዝ እንደሚችል የብዙ ሀገራት ልምዶች ያሳያሉ፡፡

ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በያዝነው ኣመት ከተጋፈጣቸው ቀውሶች ዋነኛው ግዙፍ የፖለቲካ እና የፀጥታ ቀውሶች ያስከተለው የኦሮሚያው ህዝባዊ አመፅ ነው፡፡ መንግስት አመፁን ለረዥም ወራት ማረጋጋት አለመቻሉን የቅርብ ታዛቢዎች የመንግስት እና ገዥው ፓርቲ መዋቅሮች ለመኮላሸታቸው አስረጂ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ምንም እንኳ አመፁ በሂደት ቢበርድም ከዚህ በኋላ የክልሉ ገዥ ድርጅት ኦህዴድ ክልሉን የሚመራበት ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ አመክንዮ እንደሌለው ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በድህረ-1997ቱ ምርጫ ማግስት ልማትን ለማፋጠን በሚል ሰበብ የተተከለው የአንድ-ለአምስት መዋቅርም ውጤታማ እንዳልሆነ ታይቷል፡፡

መንግስት ቀውሱን በኃይል ለመፍታት ሞክሮ ብዙ ህይወት ማጥፋቱ ደሞ የገጠመውን ቀውስ ከማባባስ ያለፈ የፈየደለት ነገር የለም፡፡ የጭፍለቃ እርምጃው በምዕራባዊያን አጋሮቹ ፊት ሳይቀር ውዥንብር ውስጥ የገባ መንግስት መሆኑን አጋልጧል፡፡ በዓለም ዓቀፍ ሜዲያ ሽፋንም የበላይነቱን አሳጥቶታል፡፡ በሌላ በኩል “ፖሊሲዎቼ የሚቀየሩት በመቃብሬ ላይ ነው” በሚል አባዜው የሚታወቀው መንግስት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአመፁ መነሻ ሰበብ የሆነውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለጊዜውም ቢሆን ለማጠፍ መገደዱ ያሳየው እውነታ ቢኖር ለህዝባዊ ተቃውሞ ያለው ተጋላጭነት መጨመሩን ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ መጋቢት ላይ ፓርላማ ቀርበው በኦሮሚያው አመፅ ለጠፋው ህይወት ይቅርታ መጠየቃቸው ቀውሱን ለማርገብ አንድ አወንታዊ እርምጃ ተደርጎ ተወስዶላቸው ነበር፡፡ ኦህዴድም በበኩሉ ለቀውሱ ተጠያቂ ያደረጋቸውን በሺህ የሚገመቱ ካድሬዎቹን አባርሪያለሁ ብሎ ነበር፡፡ መንግስት ግን አስከትሎ እስረኞችን ከመፍታት ይልቅ እንዲያውም አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ ታዛቢዎችም ሁለት ልብ ሆኖ እየዋለለ ያለው መንግስት ጊዜ ከመግዛት ያለፈ ቀውሱን ከስረ-መሰረቱ የመፍታት ዓላማ የለውም የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ በጠቅላላው ከመንግስት ሲሰጡ የነበሩት እርስበርስ የሚጋጩ መልዕክቶች መንግስት የጋራ መግባባት እንደሌለው ጠቋሚ ሆነው አልፈዋል፡፡

 የመለዮ ለባሹ ማገንገን

ሌላኛው መንግስት የገባበት ቀውስ የመልካም አስተዳደር መንኮታኮት እንደሆነ ራሱ አምኗል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ ከምሁራን ጋር ያደረጉት ውይይትም አንዳችም የለውጥ ጭላንጭል አልፈነጠቀም፡፡ ገዥው ድርጅት የመልካም አስተዳደር ዕጦቱ አረንቋ ውስጥ እንደሆነ ተረድቶ ራሱን ተጠያቂ ማድረጉን ከአጭር ጊዜ ግብ እንደሆነ አድርገው የሚያዩት ታዛቢዎች ቀላል አይደሉም፡፡ 

የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስልጣን በተጋራበት እና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ ፖለቲካዊና ፖሊሲ ማሻሻያዎች ሲደረጉ እንጂ በአስተዳደራዊ ለውጦች ብቻ እንደማይፈታ የዘርፉ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ ታዲያ ኢህአዴግ ለምን ዘላቂ መፍትሄ አይሻም? ለሚለው ጥያቄ የምናገኘው ምላሽ ግን ከመዋቅር መኮላሸት ወይም አመራር ብቃት ማነስ በላይ፡ ዋናው ችግር የህወሃት ልሂቃን ከነባሩ የፍርሃት ቆፈናቸው መውጣት አለመቻላቸው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በህወሃት ዘንድ እያንዳንዷ መሰረታዊ ለውጥ ያልታሰበ ማዕበል ታስነሳለች የሚል ስጋት የሰፈነ ይመስላል፡፡ 

ፖለቲካዊ ስልጣን ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር በቀጥታ ተቆራኝቶ መቀጠሉ ሌላኛው ቀውስ-አባባሽ ክስተት ነው፡፡ ገዥው ድርጅት ስልጣኑን የሚያስጠብቁለትን የፀጥታና ወታደራዊ መዋቅሮችን የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተጋሪ ማድረጉም ህገመንግስታዊ ተቋማትን የመጠቅለል አዝማሚያ ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ገዥው ድርጅት በሚሊዮኖች የሚገመቱትን ካድሬዎቹን እና የጦር ሰራዊቱን ጥቅም ቢሸራርፍ ውስጣዊ አመፅ ይቀጣጠልብኛል ብሎ ይሰጋል፡፡ የአስተማማኝ ገለልተኛ መረጃዎች ዕጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ሙስናም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትም በመጠንም እየሰፋ መሄዱ ሌላ የፖለቲካ እና ፀጥታ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል አመላካቺ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግስት በግዙፍ የልማት ፕሮጄክቶች የህዝቡን ልቦና ለማማለል ቢያስብም አለመሳካታቸው ግን ሌላ ግዙፍ ቀውስ እያመጣበት ነው፡፡

አሁን ኢህአዴግ በተለይ ከተሞችን የሚያስተዳድረው ከውይይትና ህዝባዊ ተሳትፎ ይልቅ ወታደራዊ እና የፀጥታ ኃይሎቹን በመጠቀም እንደሆነ ታዛቢዎች ይስማሙበታል፡፡ በኮንሶ እና ወልቃይት እስካሁን ለቀጠሉት የመብት ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚችሉ ህገ መንግስታዊ ተቋማት ቢኖሩም አንዳቸውም ምላሽ መስጠት አልቻሉም፡፡ ምላሹ አፈና እና እስራት ሆኗል፡፡ በኦሮሚያ አመፅም ሲቪል አስተዳደራዊ መዋቅሮች በፍጥነት በወታደራዊ ቁጥጥር ስር መውደቃቸው ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ሆኖም በኃይል ፍርሃትን ለማንገስ በተሞከረ ቁጥር ህዝባዊ ተቃውሞም እየጨመረ መሄዱ ቀውሱን እንደሚያባብስበት መገመት ከባድ አይደለም፡፡ ከእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ጋር የገባበት ውጥረትም ሳይፈታ እየተንከባለለ ሲሆን በሃይማኖቱ መሪዎች ላይም በቅርቡ ያስወሰነው የረዥም ዓመታት እስር ከአጣብቂኝ መውጫ አዲስ መንገድ እንደሌለው አሳይቷል፡፡

ኢህአዴግ በሀገር ውስጥ የጠመንጃ ድምፅ አለመሰማቱን እና ጠንካራ ተቃዋሚ ድርጅት አለመኖሩን እንደ አወንታዊ ስኬት ያየው ይመስላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ግን ህዝቡ ከፍርሃት ቆፈን መውጣቱን አመላካቺ ሆነዋል፡፡ ይህም ፍርሃትን ያነግሱልኛል ብሎ የተማመነባቸውን የፀጥታ መዋቅሮች ውጤታማነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እያስገባው ነው፡፡ በቅርቡም መንግስት የፀጥታ ተቋማቱንና አቃቤ ህጉን እንደገና በማዋቀር የተማከለ አወቃቀር መከተሉ ቀውሶችን ለመፍታት ወደፊት የሚከተለውን መንገድ ኃይል መጠቀም ብቻ እንደሆነ ጠቋሚ ነው፡፡ መጠነ-ሰፊ ፖለቲካዊ ቀውስ ከተከሰተ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ጦር ሰራዊቱ የፖለቲካ ዘዋሪ እንዲሆን ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ይጠበቃል፡፡  

 መድሀኒቱ ከወዴት አለ?

ምሁራን እና ፖለቲካ ተንታኞች ሀገሪቱ ለገጠሟት ችግሮች የሚያቀርቧቸው መፍትሄዎች ቢለያዩም አብዛኛዎቹ ግን ሀገሪቱ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡ እርስ በርስ ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል የሚያስጠነቅቁም በርክተዋል፡፡ 

በጥቅሉ መንግስት ብዝሃነትንም ሆነ ተቃውሞን ማስተናገድ አለመቻሉ ዋነኛ ፈተናዎቹ ሆነው እየቀጠሉ ነው፡፡ የሚወስዳቸው ብዙዎቹ እርምጃዎችም የአጭር ጊዜ ማስታገሻዎች እንጂ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ዘላቂ መፍትሄዎች እንዳልሆኑ ታይቷል፡፡ የቀውሶች መደራረብ እና የዘላቂ መፍትሄዎች አለመኖር የሀገሪቱ ዕጣ ፋንታ ምን ይሆን? የሚለውን ለመገመት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ በዚህም አለ በዚያ ግን አሁንም ኳሷ በገዥው ኢህአዴግ እግር ስር እንዳለች በሰፊው ይታመናል፡፡