Yeka Sub City office
Yeka Sub City office

(በሙሔ ሐዘን ጨርቆስ-ለዋዜማ ሬዲዮ)

እንዴት ናችሁልኝ? እኔ ደኅና ነኝ፤ “እኔ ደኅና ነኝ” ማለት ግን ካድሬ ጓደኞቼ ደኅና ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ከሰሞኑ የግምገማ መጋኛ አጠናግሯቸዋል፡፡
ያዲሳባ የተሲያት ፀሐይ “የአበሻ አረቄ” የሚል ቅጽል ወጥቶለታል፡፡ ወዲያውኑ ያሰክራል፡፡ ካድሬ ጓደኞቼ በዚህ አስካሪ ንዳድ ላይ ሆነው እንኳ በረደን ይሉኛል፡፡ ፍርሃት አንዘፍዝፏቸዋል፡፡ ግምገማ አንፍዟቸዋል፡፡ የመሬት “ማሪዋና” አስክሯቸዋል፡፡ እስር አስግቷቸዋል፡፡
ካድሬ ጓደኞቼ በቁማቸው ይቃዣሉ፡፡ ከራስ ምታት ኪኒን ጋር ግለሂስ ይውጣሉ፡፡ ሁሉም ወጣቶች ናቸው፡፡ ሁሉም የከተማዋ መካከለኛ አመራሮች ናቸው፡፡ ሁሉም ኑሮን ለማሸነፍ ካድሬ የሆኑ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም “ሆዳደሮች” ናቸው፡፡ ለመሆኑ ኢህአዴግ ሆዳደር ያልሆነ አባል አለውን?
እንቆቅላችሁ…!
ምን አውቅላችሁ….!
በዓለም ላይ ብዙ ሆዳደር አባላት ያሉት ፓርቲ ማን ነው?

[እነሆ ጦማሩን በድምፅ ተሰናድቶ ያድምጡት፡ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

ካድሬ ጓደኞቼ ከፓርቲያቸው ጋር አይንና ናጫ እስኪሆኑ ድረስ በመዲናዋ ጉዳይ አዛዥ ናዛዥ ነበሩ፡፡ መሬት መትረው፣ ሸንሽንው፣ ከልለው ለጥብስ የሚያደርሱት እነርሱ ነበሩ፡፡ ቃላቸው መሬት ጠብ አትልም ነበር፡፡ ካሉ አሉ ነው- ይፈጸማል፣…”አንተ ፍረስ-አንተ ንገሥ”፣ “አንተ ከድንበርህ ትንሽ ግባ- አንተኛው ፎቅ ገንባ…”፣ “ላንተ አዲስ ካርታ-ላንቺ ደግሞ የሊዝ ቦታ” የሚሉ ያልተቀቡ ልጅ ነጋሲዎች ነበሩ፡፡
የሸገርን መሬት የሚዘለዝለውን ካራ ደረት ኪሳቸው ላይ ሻጥ አድርገው ማዘጋጃ ኮሪደር ላይ የሚሸልሉ፤ ያዲሳባን 45ሺ ጋሻ መሬት ልክ እንደ በሬ ስጋ ጎረድ ጎረድ፣ ዝልዝል፣ ጥብስ፣ ክትፎ፣እያደረጉ መበለት የሚያውቁ፤—ሸገርን በ10 ብልቶች የገነጣጠሉ ነበሩ፡፡ “ምን ዋጋ አለው!” አለ..አባዉቃው…! ምን ዋጋ አለው…! እንዲያ ጢባጢቢ የተጫወቱበት መሬት ድንገት ከዳቸው? ለካንስ መሬትም ይከዳል?!

ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማጋራችሁ ነገር ቢኖር በዚህን ሰዓት እስር፣ ምደባ፣ ሹመት ወይም ሽረት እየተጠባበቁ የሚገኙ ካድሬ ጓደኞቼ የነገሩኝን ይሆናል፡፡

የመጀመሪያው ቃል “ኑ በአምሳላችን ሙሰኞችን እንፍጠር!” ይላል

ባለ “መቶ ፐርሰንቱ” ፓርቲ በ10ኛው ጉባኤው “በስብሻለሁ-ከአናቴ ገምቻለሁ” የሚለውን ዝነኛ ሲንግሉን ሪሚክስ አድርጎ ከክሊፕ ጋራ በድጋሚ መልቀቁ አይዘነጋም። ሆኖም በለበጣ ከመሳቅ ሌላ ማንም “አልገማህም” ያለው አልነበረም፡፡ “ደቡቡ” ጠቅላይ ሚኒስትር በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው “በሰሜናዊ” ቁጣ፣ “ደ” የተባለችዋን ዕድለ ቢስ ፊደል እየደፈጠጡ “የደላላ መረባችሁን በጥሱ” ሲሉ አመል እንጂ ሌላ ጉድ ይከተላል ያለ ማንም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በኢህአዴግ ቤት ሂስ መዋጥ ምራቅ ከመዋጥ የቀለለ፣ ራስን ማዋረድ ዶሮ ከማረድ ያልከበደ ስለነበረ ነው፡፡ እንግዲህ በኃይለማርያም “ሰሜናዊ” ቁጣ ማግስት ነው አሳሪው-ታሳሪ፣ፈራጁ ወራጅ ለመሆን የበቃው፡፡

ሸገር በአስር ክፍለ ከተሞች የተበለተች መዲና ናት፡፡ ዋናው የከተማዋ ሥራ በመሬት ልማት ማኔጅመነት ቢሮ በኩል ያልፋል፡፡ ዋናው የጉቦ ቱቦ መስመር የሚያልፈውም በዚሁ ቢሮ ስር ነው፡፡ የነሴኮ ቱሬ ጥናት ነው እንዲያ የሚለው፡፡ ጥናቱን ለኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አቀረቡት፡፡ ይህን ተከትሎ አቶ አባተ ስጦታው “ዘመቻ መንጥር ወይም ወጥር”ን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዘዙ፡፡ በየክፍለ ከተማው ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲዋቀር ሆነ፡፡ በኮሚቴው የክፍለ ከተማው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ይብዙበት ተባለ፡፡ መቼም ያለነሱ የሚታመን የለም! የኮሚቴው አባላት ለሁለት ወራት ድምጽ አጥፍተው፣ በር ቆልፈው፣ ሰነድ መበርበር፣ ክስ መደርደር፣ ሾመኞችን ማስደንበር ያዙ፡፡ አሳ ጎርጓሪ ባዶ እጁን አይወጣም፡፡ መሠረቱ ሙስና ሆኖ “መሠረቴ ሕዝብ ነው” እያለ ራሱን የሚደልለው ፓርቲ የሙስና ዘንዶውን ይዞት ወጣ፡፡ ዘንዶ ቢሏችሁ ዘንዶ ነው እንዴ?

በየክፍለከተማው የተዋቀረው መርማሪ ኮሚቴ የመረጃ አሰባሰብ ምን ይመስል ነበር? በሉኝ፡፡ ውስብስብና “ቃጢራ” የሚያሳድር ነበር እላለሁ፡፡ ተገልጋዮችን በመጥራት፣ ዕውቅ ጉዳይ አስፈጻሚዎችን በማባበል፣ የመሬት ደላሎችን ስልክ በመጥለፍ፣ አቧራ የለበሱ ዶሴዎችን በማገላበጥ፣ የመሬት ሹመኞችን ሚስት፣ የጭን ገረድ፣ ጓደኛና ቤተሰብ ሳይቀር እያስጠሩ፣ ሹመኞቹ የሚያዘወትሩበትን ዱለት ቤት፣ ቁርጥ ቤት፣ ግሮሰሪና ፔንስዮን ሳይቀር እየሰለሉ ቃል በመቀበል የተካሄደ ነበር ብለውኛል፡፡ ከዚህ ሁሉ ምርመራ በኋላ የሙሰኞች ሰንሰለት ይፋ ተደረገ፡፡ በውጤቱ ማግስት ምክትል ከንቲባና ባለ ብዙ ክለስተር አስተባባሪ አቶ አባተ 4ሺ መካከለኛ አመራሮቻችን “ማኖ ነክተዋል” አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 657ቱ ቀይና ቢጫ ካርድ ተመዘዘባቸው፡፡
አንድ መካከለኛ አመራር ሊመዘዝበት የሚችለው ካርድ በሦስት ይከፈላል፡፡ ከሙስና ክስ ጋር ወደ ወህኒ መወርወር፣ ከመሬት ጋር የተያያዘ ሥራ ለዘላለሙ እንዳይሠራ መታገድ፣ እና ከደረጃ ዝቅ ተደርጎ መመደብ ናቸው፡፡ ከሁሉም የከፋው ቅጣት የቱ ይመስላችኋል? መታሰር ካላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ የታሰረማ ይፈታል፡፡ ለመሬት ሹመኞች ከቅጣቶች ሁሉ ቅጣት ከመሬት ጋር የተያያዘ ሥራ ለዘላለሙ እንዳይሰሩ መታገድ ነው፡፡ እነዚህ ከመሬት ልማት የተነሱ ወጣት ሹመኞች ወህኒ ከተወረወሩት እኩል ሲያለቅሱ አስተውያለሁ፡፡ መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከመሬት ሌላ ነዳጅ የላትም፡፡ መሬት ልማት ላይ ሠራተኛ ሆኖ መመደብ የመንግሥት እቃ ግዢ፣ የጉምሩክ ዋና አስተላላፊ ሆኖ እንደመመደብ ያለ ሰማያዊ “ሪዝቅ” ነው፡፡ ከራስ አልፎ ዘርማንዘርን ማበልፀግ የሚቻለው ከዚህ ስፍራ ተኩኖ ነው፡፡ ድሮ በእኛ ጊዜ ጎበዝ የሂሳብ ተማሪ ሲገኝ “ማን ያውቃል ሲያድግ ፐርቼዘር ይሆናል” ይባል ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ‹ቀልጣፋ› ካድሬ ስትገኝ “ይቺ ምን አለ በሉኝ- የመሬት ባለሞያ ሆና ለዘርማንዘሯ ቀን ካላወጣች!!” ይባልላታል፡፡

በነገራችሁ ላይ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ከሦስት ወራት በፊት በቃል ለዩኒቨርስቲ የኢህአዴግ ኔትወርኮች ባስተላለፈው መመሪያ በከፍተኛ ማዕረግ የሚመረቁ አባላቱ ያለፓርቲው እውቅና ሌክቸረር እንዳይሆኑ ሲል አዟል፡፡ ዓላማው ሰቃይ ካድሬዎችን መሬትና ጉምሩክ አካባቢ መመደብ ነው፡፡ “ዩኒቨርስቲ መቅረት ነው የምፈልገው” የሚሉ አባላቱ ላይ ፓርቲው የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይችላል። በኢሕአዴግ ቤት “የማያዳግም” የሚባሉ እርምጃዎች ሁሉ የሚያዳግሙ እንደሆኑ የምታውቁት ነው።

ወደ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ በዚህ የመንጥር ወይም ወጥር ዘመቻ አስገራሚ ጉዶች ተዘክዝከዋል ብለውኛል ካድሬ ጓደኞቼ፡፡ ትርክታቸው አፍ ያስከፍታል፡፡ ለካስ “ቀይ ሽብር” በሚል የሚጠሩት ከተማችንን ያጨናነቁት ሲኖትራኮች ሲሶዎቹ ንብረትነታቸው የመሬት ባለሞያ ሠራተኞች ነበር፡፡ ለካስ “አይሱዙ” ለመሬት ባለሞያ ሰራተኛ ተራ ንብረት ነው፡፡ ለካስ አንድ ሙሉ ሰፈር በልማት ምክንያት የሚነሳው አንድ ጠብደል ሀብታም ቦታው አማረኝ ካለ በኋላ ነው፡፡
እስኪ ስለ አንዱ ሸበላ ኑዛዜ ላጫውታችሁ።

ዕድሜው ከ35 አይዘልም፡፡ ደፋር ካድሬ ነበር፡፡ በዘጠኝ ሺ ብር ወርሃዊ ደመወዝ አንድ የጭነት አይሱዙ፣ አንድ ሲኖትራክ፣ ሁለት ባለ ሦስት ፎቅ ቤቶች እንዳሉት ያመነ ሲሆን ይህ የመሬት ኃላፊ በካድሬነቱ ልደታ ክፍለ ከተማ ባለ ሦስት መኝታ ቤት እንዲሰጠው አደረገ፡፡ የመንግሥት ኃላፊ በመሆኑ ደግሞ ቦሌ ጣና ሬስቶራንት ላይ ሸክላዎቹ አፓርትመንቶች ላይ የኪራይ ቤት ይገባኛል አለ፡፡ ሰፋ ያለ ቤት ስለሌለና የኪራይ ቤት ለሌሎች ባለሥልጣናትም ማዳረስ አልተቻለም በሚል “ለጊዜው” ተብሎ ባለ አንድ መኝታ ቤት ተሰጠው፡፡ በጥቅሉ ይህ ኃላፊ ከሁሉም አይነት ቤቶች አንድ አንድ ነበረው፡፡ ከኮንዶሚንየም አንድ፣ ከኪራይ ቤት አንድ፣ ከግል ቪላ አንድ፣ ከፎቅ አንድ፣ ከቀበሌ ቤት አንድ…፡፡ በሌላ ቋንቋ ይህ ኮበሌ በሥልጣን ዘመኑ “የቤት ብፌ” ሲያነሳ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ኃላፊ ለመርማሪ ቡድኑ የሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ነገሩን ሁሉ ያጠቃልለዋል፡፡ “ለመጀመርያ ጊዜ ወደዚህ ቦታ ስመደብ አለቃዬ እንዲህ አለኝ- እኛን ካልመሰልክ አብረንህ ልንሠራ እንቸገራለን፡፡”

የመሬት ልማት ሠራተኞች ደመወዝ

በመሬት ላይ ለሚሰሩ ሠራተኞች ከሌላው መደበኛ ሠራተኛ ላቅ ያለ ደመወዝ እንዲሰጣቸው ሲወሰን ለሙስና እንዳይንበረከኩ ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት አንድ መካከለኛ የመሬት ልማት ጽሕፍት ቤት ኃላፊ የመኪናና የሞባይል ካርድ ጥቅማጥቅሞቹን ሳይጨምር እስከ 9,000 (ዘጠኝ ሺ) ብር ይከፈለዋል፡፡ ይህ የብር መጠን የመሬት ሠራተኞቹን ከልብ ያስቃቸዋል፡፡ “ሃሃሃሃሃ…ድሃሃሃሃሃ”ብለው የሙሰኛ ሳቅ ከሳቁ በኋላ “ይህ ገንዘብ እኮ እውነት ለመናገር ደንበኞቻችንን ይልማ ቁርጥ ቤት ወስዶ ለመጋበዝ እንኳን አስተማማኝ አይደለም” ይላሉ፡፡

የመርማሪዎች ውጤት ሪፖርት እንዳሳየው በሁሉም ክፍለ ከተሞች ያሉ አብዛኛዎቹ የግንባታ ፍቃድ ባለሞያዎች የቤት አውቶሞብል ባለቤት ናቸው፡፡ እንዲያውም የንፋስ ስልክ ላፍቶ የግንባታ ፍቃድ ሰራተኞች ለመኪኖቻቸው ቦታ ተይዞ ሌሎች ሠራተኞች እነርሱ ቦታ ላይ እንዳያቆሙ ይደረግ ነበር ይላሉ ምንጮች፡፡ የቦሌና የየካ የግንባታ ፍቃድ ሠራተኞች አብዛኛዎቹ የቪቲዝና ያሪስ አውቶሞብል ባለቤት ሲሆኑ የሰው አይን በመፍራት ይመስላል ብዙዎቹ ጎረቤት ከሚገኘው የዘፍመሽ ሞል ተሸከርካሪዎቻቸውን እንደሚያቆሙ ተወስቷል፡፡ አስገራሚው ደግሞ ስለምን ሁሉም ሠራተኞች በቪትዝ ያሪስ የመኪና ዓይነት እንደተለከፉ ነው፡፡

በመርማሪዎቹ ሪፖርት መሠረት አብዛኞቹ የግንባታ ፍቃድ ሰራተኞች በሚስቶቻቸው አልያም በቤተሰባቸው ስም የግንባታ አማካሪና ተቆጣጣሪ ድርጅት ባለቤት ናቸው፤ ይህ ካልሆነ ደግሞ የሳኒተሪ፣ የኤሌክትሪካል፣ የአርክቴክቸራል ዲዛይን የሚሰራ ድርጅት ባለቤት ናቸው። የብሉፕሪንት ማተሚያ ማሽን አላቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጋራ በመደራጀት የአፈር ምርመራ የሚያካሄድ ግዙፍ ድርጅት ባለቤቶች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ጉቦ የሚቀበሉበት መንገድም እጅግ የረቀቀና አቅማቸውንም ያሳየ ነው ተብሎለታል፡፡ ይኸውም በሚስት ወይም በቤተሰብ ስም በከፈቱት ድርጅት በኩል ተገልጋዮች ሕጋዊ አገልግሎትና ህጋዊ ክፍያ እንዲከፍሉ በማድረግ ገንዘብ ሲሰበስቡ እንደነበር ተደርሶበታል፡፡ በእነርሱ ድርጅት በኩል ያላለፈ ተገልጋይ ግን አስቸጋሪ የመከራ ጊዜያትን ያሳልፋል፡፡

የሱሉልታው ጩሉሌ በፊንፊኔ
በአንድ ሌላ ክፍለ ከተማ ሠራተኛ ላይ የተገኘው የሙስና ውጤት ደግሞ ለየት ያለ ነው ይላሉ፣ ታማኝ ካድሬዎቼ፡፡ የብዙዎቹን ሙሰኛ ኃላፊዎች አድናቆት ጭምር ያገኘው፡፡ ይህ ሠራተኛ ቀድሞ በሱሉልታ የአንድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነበር፡፡ በሙስና ተገምግሞ ወደ አዲስ አበባ አንድ ክፍለከተማ ተራ የካሳ ኦፊሰር ሆኖ እንዲዛወር ተደረገ፡፡ ቅጣት መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም በቢሮው ለሁለት ዓመታት ሲቆይ ሁልጊዜም ይሰራ የነበረው የሱሉልታ መሬትን ጉዳይ ሲሆን ከመኖርያ ቤቱም ሆነ ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ቢሮው ሆኖ ሱሉልታ ላይ ለባለሀብቶች መሬት ያሰጥ ነበር፡፡ ቤቱ ውስጥ የሱሉልታ ልዩ ዞን መኅተምና በርከት ያሉ የካርታ ወረቀቶች ተገኝተውበታል፡፡ አንዳንዶች ይህ ሰው መታሰሩ ካልቀረ ቃሊቲ ከህወሃቱ ከአቶ ገብረዋህድ ጋር ቢጎራበት መልካም ነው ሲሉ ቀልደዋል፡፡ የከተማዋ ቀልደኞች አቶ ገብረዋህድ የያዙትን የቦታ ካርታ ብዛት በማየት በጊዜው የራስ ገዝ መብት እንዲጠይቁ አበረታተዋቸዋል ተብሎ መቀለዱ ይታወሳል፡፡ ይህ ከመድረክ ጀርባ የነበረ የሱሉልታ ስውር ከንቲባም ከአዲሳባ ቤቱ የሱሉልታ ካርታ ሲያድል ከርሟል። አቶ ገብረዋህድ ከታሰሩ በኋላ “ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?” ያሉት ወደው አይደለም ለካ፡፡

ወንጀልና ቅጣት
እርግጥ ነው የኢህአዴግ ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን ከዛፍ ወደ ሞዝቮልድ አልጋ ያዛውራል፡፡ ለምሳሌ በአራዳ ክፍለ ከተማ ከአንድ ዜጋ በወር 40 ሺ ብር የሚያተርፍ የአርከበ ሱቅ ቀምተው ለሚስታቸው የሰጡ ከፍተኛ የክፍለ ከተማ ኃላፊ በዚህኛው ዙር ግምገማ ከቦታቸው ተነስተው የሌላ ክፍለ ከተማ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ተደርገዋል፡፡ “ከዛፍ ወደ ሞዝቮልድ” ማለቴ ግልጽ የሆነላችሁ ይመስለኛል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢ ጋብቻ
ከአስሩ ክፍለከተሞች በአንዱ ይህ ሆነ፡፡ የክፍለ ከተማዋ ሠራተኛ አብዝቶ ወደ ቢሮዋ ከሚመላለስ የአንድ ባለሀበት ጉዳይ አስፈፃሚ ጋር በአይን ፍቅር ወደቀች፡፡ ፍቅራቸው የጥቅም ሳይሆን የምር ነበር፡፡ ተዋደው ብቻ አላበቁም፣ ተጋቡ፣ ወለዱ፣ከበዱ፡፡ የሰሞኑ የመንጥር ዘመቻ ግምገማ ግን ጉድ አፈላ፡፡ ኮሚቴው የዚህችን ሴት ትዳር “የኪራይ ሰብሳቢ ትዳር” በሚል ፈረጀውና በጥቅም የተሳሰረ ትዳር ሊሆን ስለሚችል ሠራተኛዋ ላልተወሰነ ጊዜ ከሥራዋ እንድትታገድ ሆነ፡፡

“የትኩስ ድንች አስተዳደር”
በአዲስ አበባ አስተዳደር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ አቶ ቃሲም ፊጤን የሚያህል አቅምና ክህሎት ከልበሙሉነት ጋር የተላበሰ መሪ አልተፈጠረም ይላሉ ውስጥ አዋቂዎች፡፡ ሰውየውን “ኦሮሞው አርከበ” የሚሏቸው ሁሉ አልጠፉም፡፡ አሁንም ድረስ በመተግበር ላይ ያሉና የሚሰራባቸውን የመሬት ደንቦችና መመሪያዎችን በመቅረጽ፣ በወረራ የተያዙ መሬቶችን እንዴት ሕጋዊ ማድረግ እንደሚቻል መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ ለ52ሺ ሰነድ አልባ ዜጎች እንዴት ካርታ መሰጠት እንዳለበት፣ ሊዝ ላይ የተጣለው ዓመታዊ ድርብ የወለድ ክፍያ ተቀባይነት የሌለውና ሕጋዊም እንዳልሆነ በመከራከር፣ በሂደት ሙሉ በሙሉ መቅረት እንዳለበት ለደነዘዙ የከተማዋ አመራሮች ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡

እርሳቸው የከተማዋ የመሬት ልማት ማኔጅመነት ቢሮ ኃላፊ ሳሉ ታዲያ የትኛውም የክፍለ ከተማ ሹም ለውሳኔ ሲቸገር ቃሲም ይጠራ ይባላል፡፡ ወደ እርሳቸው ስልክ የመታ ኃላፊ “እፎይ” ማለቱ አይቀርም ነበር፡፡ ውስብስብ የመሬት ነክ ጉዳዮችን የማያዳግም መፍትሄ በመስጠት ይታወቃሉ፣ ለመካከለኛ አመራሮች አቅጣጫ ያስቀምጣሉ፡፡ “መለስ-የሕዳሴው መሐንዲስ” እንደሚባሉት ሁሉ “ቃሲም ፊጤ- የመሬት ቀላጤ” የሚሏቸው ሽማግሌ ጉዳይ አስፈጻሚ ሁሉ ነበሩ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ለሥራ ቻይና ተሳፍረው ሳለ ዜና ተሰማ፡፡ ሰውየው በፖሊስ እየታደኑ ነው የሚል፡፡ ለብዙዎች ግርምትን ፈጠረ፡፡ እርሳቸው ደግሞ ይባስ ብለው ከቻይና መጡና ከቦሌ በፍቃዳቸው ወደ ወህኒ ተሳፈሩ፡፡ ነገሩ የፀረ ሙስና ጉዳይ ነበረና አይጥ ዝሆን እንዳልሆነች እስኪጣራ አንድ አመት ተንገላቱ፡፡ በሙሉ አዲስ አበባ መሬት እንዳሻቸው የሚያዙት ሰው በአንዲት የ5መቶ ካሬ መሬት ጉዳይ መከራቸውን በሉ፡፡ መጨረሻ ላይ ፍርድ ቤት ነጻ አላቸው፡፡ ይህን ጊዜ ኦሮሚያና ሸገር በኚህ ሰው የይገባኛል ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ደረሱ፡፡ ኦሮሚያ አሸነፈና ሰውየው የኦሮሚያ ክልል የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጅንሲ ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ፡፡

ከቃሲም በኋላ ከተማዋ ውስጥ ሰው የለም ይላሉ፡፡ ሰው ስላችሁ ውሳኔ የሚወስን ሰው ማለቴ ነው፡፡ ከቃሲም መታሰር በኋላ መካከለኛ አመራሮች ፈሪ ሆኑ፡፡ ለትንሽ ውሳኔ ይርበደበዳሉ፡፡ ወትሮ በወረዳ ደረጃ ይወሰኑ የነበሩ ጉዳዮች ወደ ክፍለ ከተማ ይመራሉ፡፡ ክፍለ ከተሞችም በተራቸው “ለውሳኔ ተቸገርን” እያሉ ቀላሉን ጉዳይ ወደ ማዕከል ይልኩታል፡፡ ማዕከል “እኛ የከተማዋን ጥቃቅን ጉዳይ ሁሉ ልንፈታ አንችልም” ብሎ ወደ ክፍለ ከተማ መልሶ ይሰደዋል፡፡ ክፍለ ከተሞች ወደ ወረዳዎ፣ አዙሪቱ ይቀጥላል፣ ትኩሱ ድንች ሲሽከረከር ይውላል፡፡ በዚህ መሐል ባለጉዳይ ይነዳል- ያለቅሳል፡፡
ለዚህም ነው ከቃሲም ፊጤ እስር በኋላ ያለው የመሬት ማኔጅመንት በሠራተኞች ዘንድ “የትኩስ ድንች አስተዳደር” በሚል ይበልጥ የሚታወቀው፡፡ እላይ ያሉት ትኩስ ድንቹን ወደ ታች ይወረውሩታል፣ ታች ያሉት ወደ ላይ ይመልሱታል፡፡ አንድም ሰው ድንቹን ስለማብረድ የሚያስብ የለም፡፡

የአቶ ሰለሞን ኃይሌ መብጠልጠል

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ግምገማ በየደረጃው ሲጀመር እንደ አቶ ሰለሞን የተብጠለጠለ የአስተዳደሩ ኃላፊ የለም፡፡ ሰውየው በማዕከል የመሬት ማኔጅመንቱን የሚዘውሩ ናቸው፡፡ ከወራት በፊት በተከፈተ ግምገማ አቶ ሰለሞን ዘብጥያ ወረዱ፣ አበቃላቸው ተባለ፡፡ ሰውየውም ራሳቸውን ለእስር እያዘጋጁ ነበር አሉ፡፡ የአቅም ችግር የለባቸውም፡፡ እንዲያውም ካሉት ከፍተኛ አመራሮች የተሻለ ውሳኔ በመስጠት የተሸሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በግምገማ አፈር ድሜ በሉ፡፡ በቃ ለአቶ ሰለሞን በልካቸው ካቴና እስኪሠራ ሌላ ሰው ይፈለግ ተባለ፡፡
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎትን የሚመሩት አቶ አወቀ ኃይለማርያም ለቦታዉ ታጩ ተባለ፡፡ ከዛሬ ነገር ቦታውን ተረከቡት ሲባል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጣልቃ ገቡ፡፡ “አወቀን ከቦታው እንዳትነኩት፣ ውኃና ፍሳሽን ጥሩ ይዞልኛል” ብለው በግልጽ ተናገሩ፡፡ የአዲስ አበባ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮን ማን ይምራው? ሰው ጠፋ! በቃ አቶ ሰለሞን ከሚታሰሩ ቢሰሩ ይሻላል ተብሎ ዘብጥያ ሊወርዱ አንድ ሐሙስ የቀራቸው ሰው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተደረገ፡፡ “ከቂሊንጦ ማዘጋጃ ቤት ይሻላል” ብለው ነው እንጂ ሰውየው አሁንም ቢለቋቸው ደስተኛ ናቸው ይላሉ ለእርሳቸው ቅርበት ያላቸው አካላት፡፡

የአቶ ሰለሞን ኃይሌን ጉዳይ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ መስተዳደሩ በአቅም ማነስ ሽባ መሆኑን፣ በሙስና እስከ አፍንጫው መዘፈቁን፣ ቦርጭ ያወጣ ሙሰኛ እያሰረ በምትኩ ከሲታ ሙሰኛ እየቀጠረ መሆኑን ለማስገንዘብ እንጂ፡፡ አቅም ማነስን ሳነሳ ምን ትዝ አለህ አትሉኝም? አዲሳባ ሰሞኑን አይናችሁን ላፈር ብላ ያባረረቻቸው የመሬት ባለሞያዎቿ ከመሬት ጋር በተያያዘ ያላቸውን ንቃትና ብቃት ከፍ ለማድረግ በሚል ከዓመት በፊት ለወራት በሥልጠና ጠምዳ ይዛቸው ነበር፡፡ እነርሱን ለማሰልጠን ስንት ብር ወጣ አትሉም? 125 ሚሊዮን ብር ሆጭ ተደርጓል፡፡ ያኔ ሥልጠናው የከበዳቸውና የትምህርት ደረጃቸው ዝቅ ያሉት ካድሬዎች “ምን ይደረግላችሁ” ተብለው ተጠየቁ፡፡ ከሚከተሉት አንዱን ምረጡ ተባሉ፤ እኛ ሙሉ ደመወዝ እየከፈልናችሁ እናንት ጥቂት ዓመታትን ሲቪል ሰርቪስ ግቢ ቆዩና ዲግሪ እንግዛላችሁ? ወይንስ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታችሁ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም 5 ሚሊዮን ብር እናበድራችሁ? ወይንስ ተደራጅታችሁ እኛ ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ያለ ጨረታ እየሰጠናችሁ እናበልፀጋችሁ?
ዲግሪ ይገዛልን ያሉ ወደ ሲቪልሰርቪስ ተላኩ፤ አደራጁን ያሉ ወደ ብልጽግና ማማ ተፈናጠጡ፡፡ ያኔ ሥልጠናውን በብቃት ያለፉት ግን ለዛሬው ፈታኝ ግምገማ ተዳረጉ፡፡
ዛሬ ወሬዬን እንደ ክፍለከተማ የመሬት ጉዳይ እንዳይሆን እንዳይሆን አድርጌ ተበተብኩት መሰለኝ፡፡ እንዲህ ላጠቃለዋ፡፡ እውነት እላችኋለሁ…የሸገር ጉዳይ ተወሳስቧል፣ እንኳን ድሪባ፣ እቴጌዋም ከሞት ቢነሱ የአዲስ አበባን ችግር የሚፈቱት አይመስልም፡፡ መሠረቱ ሙስና የሆነ ፓርቲ “መሠረቴ ሕዝብ ነው” እያለ በሥልጣን ላይ እስከቆየ ድረስ አዲሳባ መድማቷን ትቀጥላለች፡፡

ሙሔ ሐዘን ጨርቆስ፣ ለዋዜማ ሬዲዮ