Weregenu- PHOTO -Wazema Radio
Weregenu- PHOTO -Wazema Radio

ግንቦት፣ 2008

ተላከ-ለዋዜማ ራዲዮ

ከሙሄ ዘሐን ጨርቆስ

አዲስ አበባ

ውድ የዋዜማ ታዳሚዎች! በመላው ዓለም እንዳሸዋ የተዘራችሁ ኩሩ የኢትዮጵያ ልጆች ሆይ! እንዴት ናችሁ? እኔ ደህና ነኝ፡፡ ምንም የሌለው ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው?

ወይዘሮ ፎዚያ በሽርም እንደኔው ምንም አልነበራቸውም፡፡ ጨረቃ ቤት ግን ነበራቸው፡፡ በላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ ለፍቶ አዳሪ ነበሩ፣ በዚሁ ክፍለከተማ ልዩ ስሙ ለቡ ቀርሳ በሚባል ሰፈር ደሳሳ ጎጆ ቀልሰው፣ ገና ነፍስ ካላወቀች ልጃቸው ጋር በጥልቅ ድህነት ይኖሩ ነበር፡፡ ከሰሞኑ ደንብ አስከባሪ ካድሬዎች ቤታቸውን ሊያፈርሱባቸው ሆነ፡፡ በጄ አላሉም፡፡ የሰማይ ስባሪ ከሚያካክሉ ካድሬዎች ጋ የጨበጣ ትግል ገጠሙ፡፡ አራት ወር ያልሞላት ልጃቸውን በትከሻቸው አዝለው ነው ታዲያ፡፡

ይሄኔ ደንብ አስከባሪው ካድሬ ደሙ ተንተከተከ፡፡ የካድሬ ደም የፈላ ዘይት ማለት ነው፡፡ የካድሬ ደም የሽምብራ ሽሮ ማለት ነው፤ እንዲሁ ይንተከተካል፡፡ በሆነ ባልሆነው ይንተከተካል፡፡ ካድሬን ስሜት እንጂ ምክንያት አይገዛውም፡፡ ኢህአዴጎች ካድሬዎቻቸውን የሚሰሯቸው ከኮብል ስቶን ጠርበው ይመስለኛል፡፡ ባይሆንማ እንዴት አንድ ጥርብ ጎረምሳ ከአንድ ልጅ ካዘሉ እናት ጋር ለቡጢ ይጋበዛል? ይህ ካድሬ ፍፁም በለየለት እብሪትና ደም ፍላት ወይዘሮ ፎዚያን ገፈተራቸው፡፡ ወይዘሮዋ ለካንስ አቅም አልነበራቸውም፡፡  ድሀ ምን አቅም ይኖረዋል፡፡ ካድሬው ቢገፈትራቸው ወደ ኋላ ክንብል አሉበት፡፡ በዚህን ጊዜ አዝለዋት የነበረችው ልጃቸው አብራ ክንብል አለች፡፡ አንከብክበው ሆስፒታል ወሰዷት፡፡ አልተሳካም፡፡ ያንኑ ምሽት ለዘላለሙ አሸለበች፡፡

የማከብራችሁ አንባቢዎቼ!

ይህንን ልብ የሚነካ ዜና ለሕዝብ ያቀበለ አንድም ነጻ የአገር ቤት ሚዲያ እንደሌለ ስነግራችሁ ጫን ባለ ሐዘን ዉስጥ ተዘፍቄ ነው፤ ከሸገር ሬዲዮ በቀር፡፡ ሸገር ሬዲዮ ነገሩን አለሳልሶም ቢሆን ለህዝብ ጆሮ ለማቀበል መሞከሩን አደንቃለሁ፡፡ አሃ! ልክ ነዋ! ይህንንስ ማን አደረገና? ዛሚ የሚባለው ሬዲዮ እንደሁ አሁንም ክብ ጠሬጴዛ ላይ ቆመው የሚሸኑ ጋዜጠኞች የሚያፏጩበት ጣቢያ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኤቴቪ እንደሁ ልማት በማብሰር ተጠምዶ በግፍ ለተገደለች አንዲት ጨቅላ የሚሆን የባከነ ጊዜ ከየት አግኝቶ፡፡ ፋና እንደሁ የገዳይ እንጂ የሟች ቤተሰብ ስላልሆነ የሕጻኗ ጉዳይ ግድም አይሰጠው፡፡ ብስራት እንኳ ሕጻኗ በሌስተር ሲቲ ስቴዲየም ዉስጥ እስካልሞተች ድረስ ዜና ሆናም አትታየው፡፡ የሚዲያ ብዝኃነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ይህን ትመስላለች፡፡

Photo Wazema Radio
Photo Wazema Radio

ውድ የዋዜማ ታዳሚዎች!

ከትናንት በስቲያ ሞዛዛ የሸገር ኤፍኤሞችን እየኮሞኮምኩ፣ ጠምዛዛ የሸገር ጎዳናዎች እያሳበርኩ፣ ደብዛዛ የድሀ ሰፈሮች እያቋረጥኩ፡፡ በስግብግብ መስሪያ ቤቶች ደጅ እያለፍኩ፡፡ ብዙ ፎዚያዎች ወደ ሚኖሩበት ወደ ምንዱባኑ ሰፈር ወረገኑ ጉዞ ጀመርኩ፡፡

ወረገኑ የሸገር እንጦሮጦስ!

መንገዶች ሁሉ በበዝባዦች መሞላታቸውን አላውቅም ነበር፡፡ ከተማዬን እንደነቀርሳ የሚበሏት ተቋማት በየአደባባዩ ተተክለው ጠበቁኝ፡፡ አነሳሴ ከአራት ኪሎ ነበር፡፡ በፓርላማው በር አለፍኩ፡፡ በሩ ላይ ጥርስ የሌለው አንበሳ በድንጋይ ተቀርጾ ተሰቅሏል፡፡ አባላቱን በትክክል ይወክላቸዋል፡፡

ቁልቁል ወደ አቧሬ ስወርድ አንድ አካዳሚ ለማስገንባት አንድ ቢሉዮን ተኩል ዮቴክ ለሚባል ተቋራጭ የከፈለው መለስ ፋውንዴሽንን አየሁት፡፡ ጥስር ነክሼ፣ እጅ ነስቼ አለፍኩት፡፡ በግራ በኩል ወደ አድዋ ድልድይ ተሻገርኩና የ22 ማዞርያን ጎዳናን ተቀላቀልኩ፡፡ የአገሪቱን የገቢ ብረት ሦስት አራተኛውን ገበያ በተቆጣጠረው ጎላጎል ሕንጻ አልፌ በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ሾልኬ ስፖርት ኮሚሽን ደረስኩ፡፡ ከዚያም ወደ ቶቶት የሚያስወጣ ድልድይ ተሻገርኩ፡፡ እዚያ ብር የማይጠግብ አንድ አጋሰስ መስሪያ ቤት አለ፡፡ ሜቴክ የሚባል፡፡ የ77 ድርቅን የሚያስንቅ ረሀብ በሚፈጃት አገር በ77 ቢሊየን ብር የሚጫወት ነብሰበላ፡፡ የርሱን ቢሮ ገላምጬ ፊቴን ወደ ገርጂ አዞርኩ፡፡፣ ራሱ ሜቴክ በገዛውና አሞራው ሕንጻ ብሎ በሰየመው የቀድሞው ኢምፔሪያል ሆቴል በኩል መንገዴን አሳብሬ ገርጂ ሮባ ደረስኩ፡፡

ገርጂ ሮባ ጋር ወደቀኝ መታጠፍ ‹‹ጊዮርጊስ›› ቤተክርስቲያን ያደርሳል፡፡ ካዲስኮ ሆስፒታል ማዶ እንደ በረሮ የሚሽሎኮሎኩ ባጃጆች ተኮልኩለዋል፡፡ ባጃጅ ከተማ መሐል ምን ይሰራል? ሙምባይ ነው እንዴ ያለሁት?

‹‹ፍሬንድ! የወረገኑ ታክሲ የቱ ጋ ነው የሚቆመው?››

‹‹ወረገኑ ታክሲ የለም፡፡›› ድህነት ያቀጠነውን ትከሻውን ሰበቀ፡፡

‹‹ታዲያ በምንድነው የሚኬደው?››

‹‹ካዛንቺስ ድረስ ባጃጅ ያዝና ሰላም ሰፈር ጋ ስትደርስ ጋሪ አለልህ››

የምን ካዛንቺስ ነው የሚያወራው ይሄ? ጋሪ? ምንድነው የሚዘባርቀው?

ለካስ እውነቱን ነው፡፡ የእውነተኛዋ ካዛንቺስ ተፈናቃዮች ለድህነታቸው የሚመጥናቸውን ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩበት ሰፈር እዚህ ነው፡፡ የሮም ቅኝ ገዢዎች ለቀድሞ ሰፈራቸው ያወጡላቸውን ስም ተሸክመው ነው የተሰደዱት፡፡ ምናለ ስሙን እንኳ ይዘውት ባይሄዱ፡፡ 20160221_113053

አንድ ብር ከሀምሳ ለባጃጅ ሾፌር ገብሬ አዲሷን ካዛንቺስ ረገጥኩ፡፡ የድህነት ቡሉኮ ደርባ ጠበቀችኝ፡፡

በእግሬ ወደ ሰላም ሰፈር ሸርተት አልኩኝ፡፡ ረዥም ሰልፍ ታየኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ የምር ደነገጥኩ፡፡ በዚህ ሰፈር ዉስጥ፣ በመኖርያ መንደር ዉስጥ እንዲህ ዓይት ሰልፍ ይኖራል ብዬ አልጠበቅኩም፡፡ ማለቴ እንዲህ ስፍር ቁጥር የሌለው ዜጋ በረዥሙ ተሰልፎ የሚገኝበት ሰፈር አዲስ አበባ ዉስጥ ይኖራል ብዬ አልጠበቅኩም፡፡ አውራ ጎዳና ላይ እሺ! ሰፈር ዉስጥ ሰልፍ? ደግሞም የታክሲ ሰልፍ አይደለም እኮ፣ የዳቦ ቤት ሰልፍም አይደለም፣ የተቃውሞ ሰልፍም አይደለም፣ የባጃጀጅም አይደለም- የጋሪ ሰልፍ ነው፡፡ ጋሪ ለመሳፈር ግማሽ ኪሎ ሜትር ሰልፍ፡፡ እግዚኦ መሐረነ!

እንዴት አዲስ አበባ ዉስጥ ያውም ከገርጂ በአጭር ኪሎ ሜትር ርቀት የጋሪ ሰልፍ ኖረ? ድህነት ለካስ አርቀው ቢጥሉትም እንደ ጭርት ነው፡፡ ተመልሶ ይወጣል፡፡

ወደ ወረገኑ ታክሲ ለመግባት የመሬቱ አቀማመጥ አይፈቅድም ተባልኩ፡፡ ለነገሩ ጋሪዎችም አይፈቅዱም፡፡ ሕዝቡም ሰፈር ዉስጥ ታክሲ ከገባ ባለሥልጣናት ዐይን ዉስጥ ይከተናል በሚል የሚሰጋ ይመስለኛል፡፡ እውነት ነው፤  ታክሲ ጣጣ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ታክሲ ከገባ-ኢህአዴግም ሰርጎ ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ከገባ ላፍርሳችሁ ይላል፡፡ የወረገኑ ሕዝብ ደግሞ በድጋሚ መፍረስ የሚፈልግ ሕዝብ አይደለም፡፡ ሲፈርስ ሲነሳ…ሲፈርስ ሲነሳ…የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ ከየጉራንጉሩ የተለቀመ የእስራኤል አይነት ሕዝብ ነው ወረገኑ፡፡

ጋሪ ያቀናው ሰፈር

የተትረፈረፈ ኮብልስቶን በሞላባት ሸገር አንድ ጥርብ ድንጋይ እንኳን ያልደረሰው ቅርቃር ነው ወረገኑ፡፡ ሰፈሩ የመንገድ ልማት የራቀው ሰፈር ቢሆንም ኢህአዴግ ጥሎ አልጣለውም፡፡ የፈረስ ጋሪ አበጀለት፡፡ ለነገሩ ጋሪውን መንግሥት ሳይሆን ሕዝብ ነው ያበጀው፡፡ የአካባቢው ዋነኛ የመጓጓዣ ዘዴም ይኸው ነው፡፡ የፈረስ ጋሪ፡፡ ‹‹ቀን ቀንስ እሺ ይሁን፤ ማታስ?›› ብዬ ጠየቅኩ፣ አካባቢው የመንገድ መብራት ብሎ ቅንጦት እንደማይከነካው ከመረዳቴ የተነሳ፡፡ ማታ ማታ አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ ትመጣለች፡፡ የዚች ቅጥቅጥ አይሱዙ አዉቶቡስ ሾፌሩ ቤቱ ወረገኑ ነው፡፡  እሱ የአካባቢውን ሕዝብ 5-5 ብር እያስከፈለ ይጭናል፡፡ ሌላስ አልኩ፡፡ ሌላ ደግሞ ከፍት የጭነት መኪኖች አሉ፡፡ ልክ የቀን ሰራተኛ ወደ አንድ የግንባታ ማዕከል ሲወሰድ እንደሚደረገው አይነት ፣ ልክ ወዶ ዘማች ወታደር ወደ ግንባር ሲወሰድ እንደሚኾነው አይነት፣ የወረገኑ ሕዝብም እንደ አሸዋና ጠጠር ይጫናል፡፡ ተጭኖ ወደ ቀዬው ይገባል፤ በክፍት አይሱዙ-በክፍት ሲኖ… ተባልኩ፡፡

ሌላስ አልኩ፤ ሌላ አልፎ አልፎ ማታ ማታ ዉልቅልቅ ያሉ የዛጉና ጋራዥ መቆም ይገባቸው የነበሩ አንድ ሁለት ታክሲዎች በራስ ተነሳሽነት ሰው ያመላልሳሉ ተባልኩ፡፡ ቀን ቀን ግን ሁሉም ነገር በጋሪ ነው፡፡ ሰርግ በጋሪ ነው፡፡ ንግስ በጋሪ ነው፡፡ ዘመድ ጥየቃ በጋሪ ነው፡፡ የታመመ ሰው ሲኖር እንኳን በ55 ብር የጋሪ ኮንትራት ነው ገርጂ የሚደርሰው፡፡ ለዚያውም ሶምሶማ እየተጋለበ፡፡

ወረገኑ ጠባብና ገደላማ የምንዱባን ሰፈር ይሁን እንጂ ነዋሪው ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት የሕዝብ ቆጠራ ወደ ወረገኑ ከዘለቀ በማሽን እንጂ በሰው ኃይል የሚሞከረው አይሆንም፡፡ እኔ ከሰሞኑ ባየሁት 50-60ሺ እገምተዋለሁ፡፡ ዜጎች ተጠባብቀውና ተጠጋግተው ስለሚኖሩ ሁለት ሰው እንደ አንድ ደርቤ ቆጥሬም ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ቅዳሜና ዕሁድ የጎብኚው ብዛት ለጉድ ነው፡፡ ከሥራ መግቢያ ማታ ለዐይን ያዝ ሲያደርግ በወረገኑ ትከሻ ለትከሻ ሳይጋፉ ማለፍ አይሞከርም፡፡

‹‹የአካባቢው ወጣት ተደራጅቷል?›› አልኩ፡፡ አዎ ተደራጅቷል ተባልኩ፡፡ ገቢ እንዲያገኝ መላ ተዘይዶለታል ተባልኩ፡፡ እንዴት ብዬ ጠየቅኩ፡፡ የወረገኑ ኢኮኖሚ የተመሰረተው ወፍና አሞራን ‹‹እሽ!.› ብሎ በማባረር ነው አሉኝ፡፡ አልገባኝም፡፡ 20160221_112821

ወረገኑ በስተሰሜን የምትዋሰነው ከቦሌ አየር ማኮብኮቢያ ነው፡፡ በአካባቢው ራዳሮችና ከአየር በረራ ጋር ተያይዘው የተሰሩ ምሶሶዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ታዲያ አየር መንገዱ ለወረገኑ ወጣቶች ሥራ ፈጠረላቸው፡፡ የወፍ አባራሪነት ሥራ፡፡ እንደመታደል ሆኖ ማንኛውም ከቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የሚነሳ አውሮፕላን አፍንጫውን ወደ ወረገኑ ቀስሮ ነው ወደ ሰማይ የሚንደረደረው፡፡ በዚህ ወቅት አሞራና ወፍ የአውሮፕላኑ ሞተር ዉስጥ ገብተው ጉዞውን እንዳያስተጓጉሉ የወረገኑ ወጣቶች ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ቅን ተግባራቸው በቀን 20 ብር ይከፈላቸዋል፡፡ ቀኑን ሙሉ ‹‹እሽሽሽ›› እንዳሉ ነው የሚዉሉት፡፡ ሕልማቸውም በበራሪ አእዋፋት የተሞላ እንደሚሆን መጠርጠር አይከብድም፡፡

ወረገኑን መንግሥት ያውቀዋል?

አዎን ያውቀዋል! በስሱ፡፡ የንብ ምልክት ለጥፎ ለምክር ቤት የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄዶ ያውቃል፡፡ ተመራጩ ግን መጥቶ አያውቅም፡፡ ወረዳ 12 ብሎ ሰይሞታል፡፡ ቦሌ ቡልቡላም ወረዳ 12 ነው የሚባለው፡፡ በቦሌ ክፍለከተማ ስንት ወረዳ 12 እንዳለ ኢህአዴግ ይወቀው፡፡

‹‹ወረገኑ›› ከላሊበላ ዉቅር ቤተክርስቲያን ቀጥሎ ከወጥ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራ የሚመስል አስገራሚ ሰፈር ነው፡፡ በነፍሴ አሲዛለሁ ይህንን ሰፈር ድሪባ ኩማ አያውቁትም፡፡ በድህነቴ አሲዛለሁ ይህንን ሰፈር 99.9 የሚሆነው አዲስ አበቤ አይቶትም ሰምቶትም አያውቅም፡፡ በድህነቴ አሲዛለሁ ኢህአዴግ ለአዲስ አበባ መቀመጫ የወከለው እጩ ተወዳዳሪዉ ይህንን ሰፈር በአይኑ ሳያይ ቦሌ አፓርታማ ተቀምጦ ሰፈሩን ወክሎ እንደተመረጠ፡፡ እውነቴን ነው፡፡

በድህነቴ አሲዛለሁ ይህንን ሰፈር አንድም የከተማዋ የካቢኔ አባል አያውቀውም፡፡ ደግሞም ሰፈሩ ሩቅ ሆኖ እኮ አይደለም የማይታወቀው፡፡ እንዲያውም ከቦሌ አየር ጤና ከመሄድ፣ ከቦሌ ወረገኑ መሄድ በኪሎሜትር ደረጃ የትናየት፡፡ በስነልቦና ደረጃ ግን ወረገኑ ለቦሌ ሩቅ ምስራቅ ማለት ነው፡፡

ለአንድ መቀመጫውን ቦሌ ላደረገ የኢህአዴግ አስተዳዳሪ ወደ ወረገኑ መሄድ ወደ ጥልቁ ገሀነም የመወርወር ያህል ሊሰማው ይችላል፡፡

እንዴ! ወረገኑ እኮ የምንዱባን ደሴት ነው፡፡ መሐል አዲሳባ ሆኖ ሰማያዊ ታክሲን አይቶ የማያውቅ ሰፈር ነው፡፡ በሸገር  ይገኛል ተብሎ የማይታሰብ የምንዱባን ዞሮ መግቢያ ነው፤ ወረገኑ፡፡20160221_111540

የወረገኑ ትንቢት

‹‹ከሰሞኑ ኢትዮጵያን የሚጎበኝ ባለሥልጣን ይኖር ይሆን?›› ብለው ጠየቁ እንበል፡፡

ለዚህ ጥያቄ ከሁለት ቦታዎች መልስ ያገኛሉ፡፡ ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ከወረገኑ፡፡ እውነቴን ነው፡፡ ከዉጭ ጉዳይ ሌላ ይህንን መተንበይ የሚችሉት የወረገኑ ነዋሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ወረገኑዎች ፈረንጅ ባለስልጣን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል አይመጣም የሚለውን መተንበይ ይችላሉ፡፡ እንዴት ማለት ጥሩ ነው፡፡

ወረገኑ ለአየር መንገዱ ማኮብኮቢያ ቅርብ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ማንኛውምን አውሮፕላን በቀላል መሳሪያ መትቶ ለመጣል ስትራቴጂክ ሰፈር ያደርጋታል፡፡ በመሆኑም እንደ ባራክ ሁሴን ኦባማ አይነት የኢህአዴግ ጌታ ወደ አዲስ አበባ ሊመጣ ሲል ወረገኑ በፌዴራል ትወረራለች፡፡ ጆሮ ጠቢዎች በምንዱባኑ ሰፈር ጆሯቸውን ያቆማሉ፡፡ ፍተሻው ይጠናከራል፡፡ ባለሥልጣኑ ወደ አገሩ ሲሄድ ወረገኑ እፎይ ትላለች፡፡

ወረገኑ የብራዚሏ ፋቬላን የምታስንቅ ሰፈር ናት፡፡ ቤቶችም እንደሰው የተሰለፉና የተዛዘሉ ናቸው፡፡ በወረገኑ የግንብ ቤት አየሁ የሚል ዳፍንታም መሆን አለበት፡፡ የግንብ አጥር እምብዛም ነው፡፡ ከገዢያቸው ባሕሪ በመነሳት ወደፊት መፍረሳችን አይቀርም ብለው ይሆን ግንብ የማይደፍሩት? በቆርቆሮ ጥፍንግ ተደርገው የተሰፉ ቤቶች ስብስብ ነው ወረገኑ፡፡ ጠባብ መንገዶች፣ ብዙ ሺ ቆርቆሮዎች፣ አጠናዎች፣ ጭቃ ቤቶች፡፡ ደግሞ እንደነገሩ የክር ካሴት የሚሸጡ ሙዚቃ ቤቶች፣ ከሰል ቤቶች፣ ሙዝ ቤቶች፣ አጠና ቤቶች ይታያሉ፡፡ ሸምሱ ሱቅ መክፈት ግዴታ የሆነ ይመስል እያንዳንዱ ቤት ደጁ ኪዮስክ አለው፡፡ አጠና ቤትና ሳምቡሳ ቤት ብዛቱ፡፡ በወረገኑ ከዳቦ ይልቅ ሳምቡሳ ተመራጭ ነው፡፡ ሳምቡሳ አንድ ከበሉት ሆድ ይነፋል፡፡ ለረሀብ ጥሩ ስንቅ ነው ይላሉ፡፡

ልክ እንደቤቶቹ ሰዎቹም በጥምዝ ተሰልፈው ይታያሉ፡፡ ሰልፉ ከቦታው አቀማመጥ የተነሳ ‹‹ሰለሜ›› ሆኗል፡፡ ከፊት ጋሪዎች ተሰልፈው ተመለከትኩ፡፡ ወግ ነውና ጋሪዎቹ ታርጋ አላቸው፡፡ ‹‹ወረገኑ›› የሚል፡፡ ይህ ሰፈር ራስ ገዝ ይሆን እንዴ? ከገርጂ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት እንዴት እንዲህ አይነት አስገራሚ ጉድ ሊኖር ይችላል፡፡ የምጸቶች ምጸት ደግሞ ወረገኑ በቦሌ ክፍለ ከተማ ሥር መመደቡ ነው፡፡

የወረገኑ ጋሪ ትርፍ ይጭናል፡፡ ከፈረሱ ኋላ የምትበነውን ምናምን እየማጉ የሚሄዱ ጋቢና የሚቀመጡት ናቸው ትርፍ የሚባሉት፡፡ ከነጂው ጋ! ሾፌር ትርፍ የሚሆንበት መጓጓዣ፡፡

ለመጨረሻ ጊዜ ወረገኑን የጎበኘኋት ከትናንት በስቲያ ከሰፈሩ ሬሳ ከወጣ በኋላ ነበር፡፡ ከሰላም አምባ ሰፈር ወደ ወረገኑ የምታሻግር ቀጭን ድልድይ ጋ ስንደርስ በቁጥር ሃያ የሚሆኑ ፖሊሶች አስወርደው ፈተሹን፡፡ ሰፈሩ ሞት ሞት ይሸታል፡፡ እናቶች በየደጁ ቆመው አፋቸውን በተቀዳደደ ሻሻቸው አፍነው በጥላቻ ወጪ ወራጆቹን ፖሊሶች ይገላምጣሉ፡፡ ቡልዶዘር አስገብተው ቤት ያፈርሳሉ፡፡ የስንቶች የዓመታት ላብ በደቂቃዎች በቡልዶዘር አፈር ድሜ ሲበላ በዐይኔ በብረቱ አየሁ፡፡

በ97 የመሬት ወረራን ፊሽካ ነፍቶ ያስጀመረ መንግሥት ዛሬ ሕገወጥነትን ለመቆጣጠር ሲንፈራገጥ ማየት ያሳፍራል፡፡ የሕገወጥነቶች ሁሉ ራስ የሆነው መንግሥት ዛሬ በሕዝብ እንባ ሐጥያቱን ለማጠብ ሲሞክር ያሸማቅቃል፡፡

አዲስ አበባ እየኖሩ መሸሽ20160221_110233

ሸገር ድሀ ገፊ እየሆነች መምጣቷን ተከትሎ ነው ወረገኑ የተፀነሰችው፡፡ የቤት ኪራይ ጀሞ ድረስ ተኪዶም ሺ ፓውንድ ሆነ፡፡ ድሆች የራቁትን ቢርቁ ቤት ኪራይ ካራ እየሆነ አረዳቸው፡፡ መላ ዘየዱ፡፡ አዲስ አበባ እየኖሩ በምሽት የሚሸሸጉበት ምሽግ ፈለጉ፡፡ ይህ ጥይት እየጨረሰ ያለ ወታደር መሆን ማለት ነው፡፡ አንድ ተኩሶ ሮጦ ምሽግ ዉስጥ መደበቅ፡፡

የሸገር ምንዱባን የኑሮ ዉድነት ላይ ቀን ቀን አንድ ጥይት ይተኩሱና ምሽት ወደ ወረገኑ ምሽጋቸው ይንደረደራሉ፡፡

የአዲሳባ ወያላ የቀን ገቢ መቶ ሃያ ብር ነው፡፡ የአዲሳባ ጉልበት ሰራተኛ የቀን ገቢ 80 ብር ነው፡፡ አናጢው፣ አሸዋ አቡኪው፣ ለሳኙ፣ ቀጥቃጩ፣ ሊስትሮው፣ ወዛደሩ፣ ላባደሩ፣ ጮኾ-አደሩ….ወላ ፖሊሱ…ገቢያቸው አያፈናፍንም፡፡ ባይበሉ ባይጠጡ እንኳን በሸገር አንዲት ክፍል ቤት ለመከራየት አትበቃም፡፡ ስለዚህ ወረገኑን ፈጠሩ፡፡ ወረገኑ የምንዱባኑ የአእምሮ ዉጤት ናት፡፡

አንድ ክፍታፍ ካድሬ ወደጌቶቹ ነገር ለማድረስ በቀን የሚሞላት የመቶ ብር የሞባይል ካርድ ለአንድ የወረገኑ ነዋሪ የወር የቤት ኪራይ ትሸፍናለች፡፡ ይህ ግነት የመሰለው ሰው ከገርጂ ሮባ ዳቦ ባጃጅ ይዞ፣ ከሰላም ሰፈር ጋሪ ይዞ፣ በሰላም አምባ አቆራርጦ ወረገኑ ገብቶ ማየት የሚችለው ሀቅ ነው ፡፡ እውነት መሆኑን አረጋግጦ ይመለሳል፡፡ በመቶ ሀምሳ ብር አንድ ከፍል ቤት መከራየት በአዲሳባ ዉስጥ በወረገኑ ብቻ ያለ ቸርነት ነው፡፡ ደግሞም ሌላ ዘዴ አለ፡፡ 13 ሊስትሮዎች ይሰበሰቡና አንድ ተለቅ ያለ ክፍል፣ ሰርቪስ ያለው ከነሽንትቤቱ ይከራያሉ፡፡ በስምንት መቶ ብር…በአንድ ሺ ብር፣ በአንድ ሺ ሁለት መቶ ብር ወይም ከዚያ ባነሰ፡፡ ተደራርበው ይተኛሉ፡፡ ማልደው ወደ አዲሳባ ይሻገራሉ፡፡ የአዲስ አበቤን የጫማ ጭቅቅት አስለቅቀው ሳንቲም ይለቅማሉ፡፡ አምሽተው ወደ ወረገኑ ምሽግ ይገባሉ፡፡ የዛለ ክንዳቸውን ለማሳረፍ፡፡

የወረገኑ የቤት አከራዮች ከድህነት አብራክ ፈልቅቀው ለውጣት እየታተሩ የነበሩ ዜጎች ናቸው፡፡ ከገበሬ መሬት በአስር ሺ ብር እየገዙ ያጠሩ፡፡ ከአመታት በፊት 50 ካሬ በአስራ አምስትና በ20ሺ ብር የገዙ ዜጎች፡፡ ከድህነት የማምለጥ ትልቅ ተስፋን ሰንቀው፣ ከአገር ቤት ሚስት አግብተው፣ በአዲሳባ የምንዱባን ሰፈር ኑሮ የጀመሩ ናቸው፡፡ ከድህነት በቅርብ ስለወጡ ድህነትን አልረሱም፡፡ ስለዚህ አንድ ክፍል ቤት ለድሀ ሲያከራዩ በሐዘኔታም ጭምር ነው፡፡

የወረዳ 12 እና 13 ነዋሪዎች፣ የወረገኑ፣ የሰላም ሰፈር፣ የሰላም አምባ ሰፈር ነዋሪዎች በዚህ ሁኔታ ሲኖሩ አምስትና ስድስት አመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ቀበሌዎች ለስብሰባ ይጠሯቸዋል- እንደነዋሪ፡፡ የቀበሌ መታወቂያ ሰጥተዋቸዋል- እንደነዋሪ፡፡ ዉሃ በቦኖም ቢሆን አዳርሰዋቸዋል- እንደነዋሪ፡፡

ከትናንት በስቲያ ማለዳ ጀምሮ ግን ተቀየሩባቸው፡፡ ጠላት ሆኑባቸው፡፡ ድንገት መጡና በዶዘር አፈረሷቸው፡፡ አንድ ሰው የሕይወቱን ሲሶ ጥሮ ግሮ ያፈራውና አለኝ የሚለው ተስፋውን በአንድ ደቂቃ ዉስጥ ወደ ትቢያ ሲመነዘርበት ምን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ወረገኑዎች ተዋደቁ፡፡ ተናነቁ፡፡ 3 ገድለው፣ አስሩ መስዋእት ሆኑ፡፡

ሰፈሩን ለቅቄ ስወጣ ሐዘን ከእፎይታ ጋር ቦረሸኝ፡፡ ከወረገኑ ወደ ገርጂ መሻገር ከሊቢያ ሲሲሊ እንደመግባት ያለ ነው፡፡

ወደ ሰፈሬ ለመድረስ ከገርጂ መገናኛ ታክሲ ተሳፈርኩ፡፡ አንዱ ኤፍኤም ያላዝናል፡፡ ‹‹በአፍሪካ ከድህነት ወለል በታች ትታወቅ የነበረችዋ አገራችን ዛሬ በዓለም ኢኮኖሚያያቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየተምዘገዘጉ ካሉ ጥቂት አገሮች ተርታ መመደብ የቻለቸው ግንቦት 20 ባመጣው ሰላምና ብልጽግና ነው፡፡ ቱቱቱቱቱ››

ጋዜጠኛው ከተናገረው ሁሉ ‹‹ከድህነት ወለል በታች›› የሚለው ቃል ከህሊናዬ ታተመ፡፡ ከድህነት ወለል በታች ሲሉ ወረገኑን ማለታቸው ነው? ከእንግዲህ ለኔ የድህነት ጠለልም ወለልም ወረገኑ ሆናለች፡፡