Photo exihibition National Theatreዋዜማ ራዲዮ-

እኔ ደህና ነኝ፡፡ ድሮስ የመሐል አገር ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው!

ለምን እንደሆን አላውቅም…አንዳንድ ጊዜ የማይመስል ነገር አስባለሁ፡፡

እነ ሲራክ፣ ጭራ ቀረሽ፣ መራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያ፣ እነ ሃይማኖት ዓለሙ፣ እንግዳዘር ፣ ዓለሙ ገብረአብ፣  እነ በላይነሽ አመዴ፣ ሙናዬ መንበሩ… (ነፍሳቸውን ይማርና…)

…እንደው የአፀደ ገነቱ ፀጥታ ረብሿቸው፣ እንደው መድረክም ተርበው፣ እንደው ጭብጨባም ናፍቀው፣ ብቻ አንድ እሑድ እምር ብለው፣ የሰማይ ቤቱን መጋረጃ ቡጭቅጭቅጭቅ አድርገው፣ ዳግም ነፍስ ዘርተው በብሔራዊ ቴአትር በር ቢያልፉ…መሞታቸውን ክደው በተከራከሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በሕይወት ሳሉ ለመድረክ የበቁ አብዛኛዎቹ ቴአትሮች ዛሬም ከመድረክ አልወረዱማ፡፡

በዚህ ረገድ ባቢሎን በሳሎንን  የሚያህል የለም፡፡

እኔ አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፣ እኔ 2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁና፣ እኔ ኮሌጅ በጥሼ ቴአትሩ ከመድረክ አልወረደም፡፡ እኔ ሥራ ይዤ፣ ሚሽት ሳገባ፣ ቴአትሩ ከመድረክ ገባ፡፡ የመጀመርያ ልጄ ምድር ወደሚባል ሰፊ የቴአትር መድረክ ሲመጣ ባቢሎን በሳሎንም ወደ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ተመልሶ መጣ፡፡ አቤቱ! የጊዜው መርዘም!

እውነት ነው ይህን ቴአትር በተለያየ የሕይወት ዘመኔ አሰልሼ ተመልክቼዋለሁ፡፡ ጭብጡ በደንብ የገባኝ ግን ደም ግባት ያላት ሚስት አግብቼ መቅናት ስጀምር ነው፡፡ የኔ ገረማችሁ? ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው በተባለ መጽሔት ሰሞኑን የቀረበ አንድ የቴአትር ሱሰኛ ይህንኑ ተውኔት 46 ጊዜ ደጋግሞ መመልከቱን አምኗል፡፡ የዚህ ሰው ጤናው ሊጤን ቢገባውም አዲስ ነገር የማጣት ረሀብ ለአእምሮ ጤናም እንደሚዳርግ ይጠቁመናል፡፡

እውነት ለመናገር ድግግሞሹ አሰልቺ ነው፡፡ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለፀሐፊ ተውኔቱም፡፡ 16 የቴሌቪዥን ድራማ፣ 60 የሬዲዮ ድራማና ሌሎች በርካታ ቴአትሮችን ለመድረክ ያበቃው የቴአትሩ ፀሐፊ ዉድነህ ክፍሌ ‹‹ይሄ ቴአትር ለምን እንደተወደደ፣ ለምን እንደሚደጋገም ለኔም ምስጢር ነው›› ይላል፡፡ 

ብቻ የባቢሎን ታሪክ ረዥም ነው፡፡ በአጭሩ ለማስቀመጥ…ተስፋዬ ገብረሃና ብጽአትን ይዞ ከአውስራሊያ ዛሬ ቢመለስ ዛሬዉኑ ተሰልፎ ሊመለከተው የሚችል ቴአትር ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ተስፋዬ ቴአትሩን ጥሎ ከተሰደደ ስንት ሺ ዘመኑ፡፡ ባቢሎን በሳሎን ግን እንኳንስ ከአገር ከመድረክ አልወረደም፡፡ ምን የሚሉት የመድረክ መዥገር ነው ባካችሁ!

የአገሬ ሰዎች ሆይ!

ባቢሎንን ጠቀስን እንጂ ሳሎኑ ባዶ ነው፡፡ አዲስ ነገር ተርበናል፡፡

የማንያዘዋል እንደሻው “እንግዳ” የተባለ ቴአትርም እንዲሁ ነው፡፡ ከአስርተ ዓመታት በኋላ ተመልሷል፡፡ የኃይሉ ፀጋዬ “ከራስ በላይ ራስ” ከ15 ዓመታት በኋላ መድረኩን ተቆናጧል፡፡ የዳዊት እንዚራ ለስምንት ዓመት ያህል ይወጣል ይወርዳል፡፡ “የጠለቀች ጀንበር” ለ16 ዓመታት ያህል ይመጣል፣ ይሄዳል፡፡ “አንቲገን” አዜብ መስፍን አምፊ ቴአትርን ባታፈርሰው ኖሮ ዛሬም መድረክ የሙጥኝ ይል እንደነበር አልጠራጠርም፡፡ ምን ተሻለን?

ሰሞኑን ደግሞ የጌትነት እንየው “የእግዜር ጣት” ለዳግም ዕይታ እየመጣላችሁ ነው፡፡ ተዋናዮቹ ከመድረክ ጀርባ በጥናት ተሰንገዋል፡፡ ዉበትን ፍለጋም መንገድ ጀምሯል፡፡

ድግግሞሹ አታክቶኝ አዲስ ነገር ፍለጋ ሽቅብ ወደ ቸርችል ወጣሁ፤ 

ማዘጋጃ ቤት ደረቱን ገልጦ ተቀበለኝ፡፡

ይህ የማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ድሮ ከቴአትር በተረፈ ጊዜው ለስብሰባ ያገለገግል ነበር፡፡ አሁን ከስብሰባ በተረፈ ጊዜው  ለቴአትር ክፍት ነው፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ እነ ከንቲባ ድሪባ ይተውኑበታል፡፡ ከእሑድ ከሰዓት ጀምሮ ደግሞ ጀማሪ አርቲስቶች የፖለቲካ አቧራውን ከመድረክ እፍ እፍ ብለው ካራገፉ በኋላ ፊጥ ይሉበታል፡፡

ከሰሞኑ እንግዳ የተሰኘ ቴአትርም ከዚሁ ማዘጋጃ ቤት መድረክ ላይ ወጥቷል፡፡ የጽዳት ሠራተኞች፣ ነጻ የቴአትር ካርድ ያላቸው የሥራ ሂደት ኃላፊዎች፣ ቴአትር ምን እንደኾነ ለማወቅ የጓጉ የሚመስሉ ባላገር ጥንዶች እየተሸኮረመሙም እያስካኩም ይመለከቱታል፡፡ ቴአትሩ እየታየ በግል ወሬ የሚጠመዱት ይበዛሉ፡፡ ሲጋራ ለማጤስ ከተመልካች ላይተር የሚለምኑም አልጠፉም፡፡

ፍቅር የተራበ የሚባል ተውኔትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዚሁ ‹‹ቴአትር በተራበው›› ማዘጋጃ ቤት እየታየ ነበር አሉኝ፡፡ ሰሞኑን ነው ወደ ዓለም ሲኒማ የሄደው፡፡ ዓለም ሲኒማ ደግሞ እንደባለቤቱ ቶሎ ቶሎ ማሊያ ይቀያይራል፡፡ ሲለው አቡጀዲውን እየዘረጋ፣ ሲለው ተዋናዮችን እያተጋ በሲኒማና በቴአትር መሐል ይዋልላል፡፡

  ዉድ የአገሬ ሰዎች!

ድግግሞሽ አታከተኝ፡፡ አዲስ ቴአትር ለምን ጠፋ ብዬ ራሴን ጠየቅሁ!? ከአንጀት ጠብ የሚል ምላሽ ግን አጣሁ፡፡

በአንድ በኩል፣ የድሮ ቴአትር ዛሬም ድረስ መደጋገም የቀድሞውን መድረክ ጥንካሬ፣ የዚያን ዘመን የምናብ ጥልቀት፣ የዚያን ዘመን የፈጠራ ምጥቀት፣ ከመጋረጃ በስተጀርባ የነበረን እውነተኛ የሞያ ፍቅር አመላከተኝ፡፡

በሌላ በኩል የድሮ ቴአትር በአሁን ዘመን እንዲህ መንገሥ፣ የዛሬን ደራሲና ተደራሲ ኪናዊ ትዳር መልፈስፈስ፣ የጥበብን መርከስ፣ የከያኒውን ሀሞት መፍሰስ ጠቆመኝ፡፡

አዲስ ቴአትር ግን ለምን ጠፋ? ስል ደግሜ ደጋግሜ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ የልብ የሚያደርስ መልስ ግን ሳላገኝ ቀረሁ፡፡ ምላሽ ፍለጋ ኳተንኩ፡፡ ከነበርኩበት ማዘጋጃ ቁልቁል ወደ ራስ መኮንን ድልድይ ተንደረደርኩ፡፡

የቴአትር ጥበብ አድባር ብሔራዊ ቴአትር ይሁን እንጂ ቴአትር ከዚያ አልተጀመረም፤ ከማዘጋጃም አልተጀመረም፡፡ ለቴአትር ጥበባት አገር-ፍቅር ነው ምንጩ፡፡ እድሜ ለአክሊሉ ታላቅ ወንድም ለቢትወደድ መኮንን ሀብተወልድ፡፡

ምን ዋጋ አለው ታዲያ! እርሳቸው በአገር ፍቅር ማኅበር አማካኝነት አምጠው የወለዱት ቴአትር ቤት ዛሬ የአይጦች መራኮቻ ኾነ፡፡ የምሬን እኮ ነው፡፡ አገር ፍቅር አይጥ አስቸግሮ ቴአትር እየተቋረጠ ነው አሉኝ፡፡ በዚህ የተነሳ ሴት ተመልካቾች ጨርሱኑ መግባት ትተዋል ተባልኩ፡፡ ብዙ ድመቶችና ጥቂት ተመልካቾች ናቸው ቴአትር ቤቱን የሚታደሙት፡፡

ለቴአትር ጥበብ ፈር ቀዳጁ ያ ከጊዮርጊስ ዝቅ፣ ከራስ መኮንን ድልድይ ከፍ ብሎ የሚገኘው ቤት እንዳይሆኑት ኾኗል ቢሉኝ ከፋኝ፡፡ ከአይጦቹ ትርኢት ጎን ለጎን ለዘመናት ተመልካች ሲቀባበላቸው የከረሙት ያው የፈረደባቸው የዳዊት እንዚራ፣ ከራስ በላይ ራስ፣ የጠለቀች ጀንበር፣ እየተፈራረቀ ይቀርባሉ፡፡

ዉድ የአገሬ ሰዎች ሆይ!

እውነት እላችኋለው ድግግሞሹ እጅግ አታካች ነው፡፡ አዲስ ነገር ፍለጋ ኳተንኩ፡፡ ከአገር ፍቅር ወደ ብሔራዊ ቴአትር ተመለስኩ፡፡

ድሮም ጃ የባረኩት ነገር ግርማ ተለይቶት አያውቅም፡፡ ወርቃማው ባንክን፣ ማዘጋጃ ቤትን፣ ግዮንን፣ ሂልተንን ማየት ይቻላል፤ ከሁሉም ከሁሉም ብሔራዊ ቴአትርን መመልከት በቂ ነው፡፡ በተቃራኒው ኢህአዴግ የነካው ነገር ምንም ግዙፍ ቢኾን ቀትረ ቀላል የሚኾነው ስለምንድነው? በየወረዳው ከተገነቡ የወጣት ማዕከላት ጀምሮ እስከ ቀላሉ ባቡር ድረስ ነገራቸው ሁሉ ቀትረ ቀላል ይኾኑብኛል፡፡ ለምን እንደሁ እንጃ!

ቴአትር ጥበብ ግርማ ሞገሱ የተገፈፈውም በዚህ ሥርዓት ይመስለኛል፡፡ ነብሰ በላው ደርግ እንኳ እንዲህ አላንኳሰሰውም፡፡ በዚህ ፍዝ የኢህአዴግ አታካች የአመራር ዘመን ትልቁ የፈጠራ ስኬት የሚባለው ‹‹ብ-ሔ-ር ብሔረሰቦች፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች›› የሚል ኅብረ ዝማሬ ብቻ ነው፡፡ ሌላስ ከተባለ ‹‹አሽከርከር ረጋ ብለህ፣ አትቸኩል ትደርሳለህ›› የሚለው…ዝማሬ ይጠቀሳል፡፡

ዉድ የጦማሬ ታዳሚዎች!

ጃንሆይ ለኪነ ጥበብ የዋሉትን ዉለታ ቆጥረን እንዘልቀዋለን እንዴ?

ቴአትር ቤቶችን ከመገንባት ጀምሮ….

እርግጥ ነው ብሔራዊ ቴአትር ቤትን መገንባት የጀመሩት ጣሊያኖች ነበሩ፡፡ ጃ ግን ጅምሩን ሕንጻ በሩብ ዓመት ጨረሱት፡፡ 25ኛ ዓመት የዘውድ በዓላቸውን አስታከው ሕዳር 3፣1948 ዓ.ም መርቀው ከፈቱት፡፡ የፈረንሳይ ባሌት ተጫዋቾች ከፈረንሳይ መጥተው የቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ዳዊትና አሪዮን የተሰኘ ድንቅ ተውኔት ከመድረክ ቀርቦ ወዘናው ቸፍ ያለው ቴአትር ቤት ተመረቀ፡፡

በዚያ ዘመን ብሔራዊ ቴአትር እንኳን ለኢትዮጵያ ለአፍሪካም ፋና ወጊ ነበር እኮ፡፡ ንጉሡም ኪነቱን ይደግፉ የነበረው እንዳሁኖቹ ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ነበር፡፡ ለምሳሌ ደጉ ንጉሥ ለዚህ ዳዊትና አርዮን ለተባለ ተውኔት ለአልባሳት ብቻ 60ሺህ ብር ወጪ  አድርገዋል፡፡ የዚያ ዘመን 60ሺህ ከዛሬ ስድስት ሚሊዮን በምን ይለያል?

ከያኒስ ቢኾን! ዛሬ ከታፊ እንጂ ከያኒ አለ እንዴ? ምድረ ከር…..ም ሁላ!

ሲመስለኝ…በወዲህኛው ዘመን ከባድ የንዋይ ፍቅር እንዳለ ሁሉ በወዲያኛው ዘመን ከባድ የኪነት ጥሪ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያኔ በ1947 ከማዘጋጃ ቤት ወደ ብሔራዊ ቴአትር የተዛወሩት አርቲስት ታደለ ታምራት በ18ብር ደመወዝ ነበር በቴአትር ቤቱ የሚያገለግሉት፡፡ ትጋታቸው ታይቶ የቢሮ ሥራም ተጨምሮላቸው ደመወዛቸው ወደ 20 ብር ከፍ እንዲል የተደረገው ከአራት ዓመታት አገልግሎት በኋላ ነበር፡፡ ድንቅ ከያኒ ነበሩ ታዲያ፡፡

ደግሞም በዚያ ዘመን አንድም ሦስትም የነበሩት ሁለገብ አርቲስቶች ተውኔትን ብቻ ሳይኾን ዉዝዋዜን፣ ድምጽን፣ ኮሜዲን የሙዚቃ መሣሪያን ሁሉ ይጫወቱ ነበር፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ሳህሉ ለምሳሌ ሁሉኑም ከመሆን አልፈው የአስማት ጥበብን ደርበው ያቀርቡ ነበር፡፡

መርሃዊ ስጦታውን እንውሰድ፡፡ 60 ዓመት በብሔራዊ ቴአትር ቤት አገልግለዋል፡፡ ደመወዛቸው 27 ብር ነበር፡፡ ከረዥም አገልግሎት በኋላ መቶ ብር ደረሰ፡፡ እንግዲህ ያን ሁሉ ሙዚቃ ያስኮመኮሙን በ100 ብር ደመወዝ እንደሆነ ስናስብ ዘንድሮን እንረግማለን….!! እድሜ ይስጥልን አባባ መርሃዊ ከማለት ዉጭ ምን እንላለን!?

እንዴ! የአሁን ከያኒያን እኮ በደም አዝማሪያን ናቸው፡፡ እየተወኑ መቶ ብር ሸሚዝ ኪሱ ላይ የያዘ ተመልካች ከተመለከቱ መድረክ ላይ ፌንት ይሠራሉ፡፡ ቃለ ተውኔቱ ይምታታባቸዋል፡፡ ቴአትሩን የሚሠሩትም በትርፍ ሰዓታቸው፣ ለትርፍ ነው፡፡

ዉድ የአገሬ ሰዎች!

ይሄን ይሄን እያዩ እየሰሙ፣ አንዳንድ ጨለምተኞች “ቴአትር እኮ ሞተ” ይሉኛል፡፡ ቴአትር አይሞትም እላቸዋለሁ፡፡ 2ሺህ 500 ዓመት እድሜ ያለው የቴአትር ጥበብ ለምን ብሎ ነው ዛሬ የሚሞት፡፡ 

“የሚሞተውማ ዘመናዊ ፊልም አቆስሎ ስለገደለው ነው” ይሉኛል፡፡

አይዋጥልኝም፡፡ እንዲያማ ቢኾን ኑሮ ኪነ ጥበባት እርስበርስ ተታኩሰው በተላለቁ ነበር፡፡

የራዲዮ መፈብረክ ጋዜጣን መች ገደለ? የቴሌቪዥን መብለጭለጭ ራዲዮንን መች አጠፋ? የፎቶግራፍ መፈልሰፍ ሥዕልን መች አከሰመ?

እመኑኝ ቴአትር አይሞትም፡፡

ባይሆን ቴአትር የጽኑ ሕመምተኛ ማገገሚያ ክፍል (አይሲዩ) ገብቷል በሉኝ፡፡ ለምን ነው ብትሉ ፈጣሪ ጠፍቶ፡፡ ጥልቀት ያለው ሐሳብ የሚጽፍ ፈጣሪ ጠፍቶ፣ ለንዋይ የማይብሰከሰክ ፈጣሪ ጠፍቶ፡፡

እውነት ይነገር ከተባለ….አሁን እኮ አገሪቱን የዶላር እጥረት ብቻ አይደለም እያሰቃያት ያለ፡፡ የፈጠራም ነው፡፡ ሁሉ ጥበብ እየቸከ፣ ጥበበኛም የታኘከን መልሶ እያኘከ፣ ኪነት ቀረፋ ማስቲካ ኾነች፡፡ የነበረከት እያዩ ፈንገስ፣ የነ አዜብ ወርቁ ሰላምታ ባይኖር የዚህ ትውልድ አሻራ ምን ይሆን ነበር?

ብቻ ቴአትር ሞተ እያላችሁ አታሟርቱ፡፡ ተገቢም አይደለም ጸሎተ ፍትሐቱ፡፡

ቴአትር አይሞትም፡፡ ፊልም ቴአትርን ተኩሶ የሚገድል ጥይት ጨርሶ የለውም፡፡ ልጅ ይሮጣል እንጂ አባቱን አይቀድምም፡፡

2500 ዓመት የኖረን ጥበብ ቻራና ዛንድራ ተኩሰው ይገድሉታል ብሎ ማሰብ በራሱ የጥበብ ማነስን ነው የሚያሳይ፡፡

ይልቅ እንዲያ ስንል እንዳይሰሙን፤ እነ ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ እነ አውላቸው ደጀኔ፣ እነ ጌታቸው ደባልቄ፣ እነ አስናቀች ወርቁ፣ እነ ሙሴ ነርሲስ፣ እነ ተስፋዬ ሳህሉ፣ እነ ወጋየሁ ንጋቱ… እንዳይሰሙን፡፡

ዉድ የአገሬ ሰዎች!

ነገር ባጭር አይኾንልኝም፡፡ ጥበብ ርቆኛል ማለት ነው፡፡

እኔን የደነቀኝ ግን ሌላ ነው፡፡ ቴአትር ሲታመም የቴአትር ትምህርት ቤቶች መፈልፈላቸው ደንቆኛል፡፡ ነገሩ ስላቅም፣ ፌዝም፣ ፋርስም ይመስላል፡፡ የጅግጅጋ፣ የዋቻሞ፣ የመደወላቡ ዩኒቨርስቲዎች የቴአትርን ዲግሪን ለዜጎች ይጭናሉ፤ ያስጭናሉ፤ ሲሉኝ ሳቅ አመለጠኝ፡፡ በትምህርተ ሥርዓታቸው ዉስጥ ‹‹ለተመልካች ጀርባ አይሰጥም›› የሚባል ባለ 6 ክሬዲት ኮርስ አላቸው ሲሉኝ ሳቄ ረዘመ፡፡

ቴአትርን በዲግሪ የማስተማሩን ነገር ወልቂጤም ጀምሮታል ሲሉኝ ነገሩ አንዳች ዓይነት ብሔራዊ ፋርስ ኾኖ ተሰማኝ፡፡ “የኾነው ኾኖ የ60 ዓመቱን ቴአትራችንን የ6 ዓመቱ ወልቂጤ ይታደገው ይሆን?” ብዬ ጦማሬን በከንቱ አንቀጽ ልሠረው፡፡

አውግቻው ቶላ (ለዋዜማ ራዲዮ)