FILE

ዋዜማ- ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ለሶስተኛ ጊዜ እየተከለሰ ነው።

በ2011 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1100 እና በ2013 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1232  በአንድ አድርጎ የቀረበው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 9/2015 ህዳር 13 ቀን 2015 ዓ.ም በምክር ቤቱ ውይይት ተደርጎበት ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ ማሻሻያ ያስፈለጋቸው የአዋጁ ፍሬ ሐሳቦች የሚከተሉት ናቸው

  • አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ በታሳስ 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ውጊያ ለመሩ ፣ ሀይል ለመሩ ፣ ድልና ውጤት ላስገኙ ከፍተኛ የጦሩ መኮንኖች በየደረጃው የማዕረግ ዕድገት ሲሰጥ በህግ ሳይደነገግ ለጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተሰጠውን የ “ፊልድ ማርሻል” ማዕረግ በአዲስ መልክ በአዋጁ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
  • ሌላው አዲስ ጉዳይ ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ለሁለት አመታት በሰራዊቱ ብሄራዊ አግልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ የከፍተኛ ሁለተኛ ደራጃ ወይም የዩንቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ አባላትን ተቋሙ ተቀብሎ ግልጋሎት እንዲሰጡ ሊደርግ እንደሚችልና አባለቱ ግልጋሎታቸውን ሲጨርሱ የብሄራዊ ተጠባባቂ ሃይል አባላት የሚሆኑ ከሆነ ተቋሙ በሚወጣው መመሪያ መሰረት ተያያዥ መብቶችና ጥቅሞች እንዲጠበቁላቸው እንደሚደረግና  ዝርዝሩ በህግ እንደሚወሰን ተደንግጓል፡፡ በዚህም ለተቋሙ ተልዕኮ አስፈላጊ ናቸው ተብለው በሚለዩ ሙያዎች ፈቃደኛ የሆኑ ሙያተኞችን መልምሎ በብሄራዊ ተጠባባቂ ሃይልነት ሊይዝ እንደሚችሉ አስቀምጧል፡፡
  • ረቂቅ አዋጁ ማንኛውም በክብር የተሰናበተ የሰራዊት አባል የአገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ  የሚጥል ሁኔታ ሲገጥም አደጋውን ለመመከት መንግስት ወይንም መከላከያ ሚኒስቴር ዳግም ጥሪ ሲያቀርብ  ለጥሪ ምላሽ የመስጠትና አገራዊ ግዴታ የመወጣት ሃላፊነት የሚጥል ሲሆን በጥሪው መሰረት ዳግም ወደ ሰራዊት የተቀላቀለ የሰራዊት አባል ሚንስቴሩ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው በቀጣይነት እንዲያለግል በነበረት ማዕረግ ደረጃ መልሶ ሊቀጥረው እንደሚችል አስቀምጧል፡፡
  • ከዚህ በፊት ከሰባት አመት በላይ ውትድርና ግልጋሎት ያለው ሆኖ በቀላሉ የማይተካ ልዩ ክህሎት ያለው እንዲሁም ሃያ አመትና ከዛ በላይ ያገለገለ ኮሎኔል፣ ጀኔራል መኮንንና ከዛ በላይ ለሆኑ ከቀረጥ ነጻ የቤት መኪና ከውጪ እንዲያስገቡ ይፈቅድ የነበረው መብት ተሻሽሎ በቀረበው አዋጅ የነበረው አሰራርና ማበረታቻ የአገርን አቅም ያላገናዘበ እንደሆነ በመግለጽ ወደ 30 አመት ከፍ እንዲልና ማንኛው ከ 30 አመት በላይ ያገለገለ የሰራዊት አባል ከቀረጥ ነጻ መኪና ማስገባት ቢፈልግ እንዲፈቅድ ተደንግጓል፡፡
  • ከዚህ ቀደም በሰራዊት አባል ላይ ክስ ሲቀርብ ተከሳሽ ከቀረቡበት ክሶች መካከል ከፊሉ በወታደራዊ ፍርድቤት ከፊሉ ደግሞ በመደበኛ ፍርድቤት ይታይ የነበረውን አሰራር አሰራሩ አመችነት ስለሌውና ለእንግልት የሚዳርግ በመሆኑ የተቀላጠፈ የፍርድ ሂደት እንዳይኖር ስለሚያደርግ በማሻሻያው ሁሉም ክሶች ተጠቃለው በአንድ በወታደራዊ ፍርድቤት እንዲታዩ ያደርጋል፡፡
  • የወታደራዊ ፍርድቤት ዳኞችን መሾምን በተመለከተ በመከላከያ ኢታማዦር ሹም አቅራቢነት በመከላከያ አዛዦች ካውንስል ይሾም የነበረውን አሰራር ፍትህ አሰጣጡ ፍትሃዊና ገለልተኛ እንዲሆን ለማድረግ በሚል ዳኞችን የመሾም ስልጣን ለአገር መከላከያ ሚንስትሩ ሰጥቷል፡፡
  • እስከ ሶስተኛ እርከን ድረስ የነበረው የውትድርና አገልግሎት ሜዴይ (ሽልማትና ዕውቅና) ተሸሽሎ በቀረበው ረቂቅ እስከ አምስት እርከን  ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡
  • በሌላ በኩል በመከላከያ ሚንስትሩና በጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አቅራቢነት ጠቅላይ ሚንስትሩ አገራዊ ጥቅምና ደህንነትን ለመከላል ሲባል እጅግ ጥብቅ ሚስጥር ብሎ የሚሰይማቸውን የጦር መሳሪያዎችና የውጊያ ቁሰቀቁሶች የግዥ ሂሳብ መዛግብት፣ ሰነዶችና  ለመረጃ የወጡ የክፍያ ማስረጃዎች እንዳይገለጹ ማድረግ እንደሚችልም ያብራራል፡፡ [ዋዜማ]