Mass Nightclubሙሔ ሐዘን ጨርቆስ (ለዋዜማ ሬዲዮ)

አትሌት ድሪባ መርጋ 22 ማዞርያ በተለምዶ ጤና ጣቢያ ከሚባለው ሰፈር ገባ ብሎ በቁመቱ ገዘፍ ያለ፣ በስፋቱ ከአንድ የሩጫ መም የማይተናነስ፣ (400 ካሬ ላይ ያረፈ) የእንግዳ ማረፊያ ገንብቷል፡፡ አክሊለማሪያም ክብሩ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል  ማኅበር ደግሞ የአትሌቱን እንግዳ ማረፊያ ጠቀም ባለ ዋጋ ተከራይቶታል፡፡ በሌላ አነጋገር አክሊለማርያም ሙሉ ሕንጻውን ከአትሌቱ በጅምላ ተከራይቶ ክፍሎቹን ለአረቦች በችርቻሮ ያከራያል፡፡ በዚህ የቢዝነስ የዱላ ቅብብሎሽ ሊያ- ገስት- ሀውስ ተወለደ፡፡

ሊያ ገስት-ሀውስን የማያውቅ ጥቁር አረብ በምድረ ኻርቱም የለም ብሎ ለመደምደም ትንሽ ሲቀረኝ ነው ይህን ማስታወሻ ያገባደድኩት፡፡ ያለ እረፍት ነው ቤቱን የሚመላለሱበት፡፡ “አልኹርፋቱ ነዚፋቱ ከማ ሰይደቱልሀበሺያ ….” ይላሉ የጥራቱን ነገር እርስበርሳቸው ሲያዳንቁ፡፡ “እንደሴቶቻቸው ጽድት ያለ መኝታ ቤት ነው…” እንደማለት፡፡

በሊያ የእንግዳ መረፊያ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ከመሰላችሁ በአረብኛ እስቅባችኋለሁ፡፡ ሁለት የጽዳት ሠራተኞች፣ አንዲት አንሶላ አጣቢና አንዲት አንሶላ አንጣፊ አረብኛውን ሲያቀላጥፉት ሰምቼ እኔ ራሴ ሀበሾች ስለመሆናቸው ማመን ከብዶኝ ነበር፡፡

እንዴት ቻላችሁት ብላቸው አንዷ ለ7 ዓመት ጅዳ የከረመች፣ አንዷ ከ3 ዓመት በኋላ ከኳታር የተጠረዘች፣ ሌላኛዋ ደግሞ ኻርቱምን እንደ ሰቆጣ የተመላለሰችበት ስለመሆኑ ተረዳሁ፡፡

የሰቆጣ ልጅ ናት ሁስና፡፡ እውነተኛ ስሟ እንኳ ሶስና ነው፡፡ ሁስና የሥራ ስሟ እንደሆነ ሳትነግረኝ ገና ማተቧን እንዳየሁ ጠርጥሪያለሁ፡፡ በእንግዳ ማረፊያው አንሶላ አንጣፊ ናት አላልኳችሁም?  አረብኛውንም ልክ እንደ ነጭ አንሶላ ነው የምታነጥፈው፡፡

ዘሀራ ደግሞ ኻዲማት ናት፡፡ የእንግዳ ማረፊያው ሆስተስ በሏት፡፡ የሱዳን አረብኛን በዜማ ተረክ ስታደርገው የማንኛውንም አረብ ልብ ትርክክ ታደርጋለች፡፡ “ያእኒ ሂያ ቲትከለም ሉጋ አረቢያ ሙምታዝ”

ብቻ ምን አለፋችሁ… በሊያ ገስት-ሀውስ ከዘበኛው ጀምሮ ቋንቋውን የማይሞክር ፈልጎ ማግኘት በኻርቱም ጥቁር ሱዳናዊ ፈልጎ እንደማጣት ነው፡፡

“ከይፍል ሃል፣ ከይፈ ኢንተ? ተማም? መዝቡጥ፣ ኮይስ?”

“አነ ተማም! አልሃምዱሊላህ” እያሉ እየተሳሳቁ መቀላቀል ነው፤ የአረብና የሴት እንግዳ የለውም፡፡

ሎቢው አካባቢ አረቦቹ በዋይፋይ ዙርያ ተቀምጠው ይሄን ፌስቡክ እንደ ፔፕሲ ይጠጡታል፡፡ አዲስ ሰው ሲመጣ ዝም ብሎ መቀላቀል ግን የለም፡፡ “ሰላም አለይኩም፣ ኬይፍ ኢንተ?” መባሉ አይቀርም፡፡ አረብ ፕራይቬሲ አያውቅልህም፣ እንደ ሐረር ሕዝብ ድርግም ነው፣ “አቦ ሰላም ነው?” ብሎ ጥልቅ፡፡ እየበሉማ ከሆነ ይብስባቸዋል…“ታኣል ታኣል ተፈደል”  ይሉሀል፤ (እንብላ እንጂ፣ አታካብድ!) እንደማለት፡፡

ይሄ ሩዝ የሚባል ምግብ ነብዩ ሙሐመድ ዉሻን ያረከሱ ዕለት እሱን ሳይባርኩት አልቀረም፡፡ እውነቴን እኮ ነው…ቢበላ ቢበላ እኮ ነው የማያልቀው፡፡

###

ለማንኛውም እነ ሊያ ገስት-ሀውስ አንድ ክፍል ለአንድ ምሽት ከስድስት መቶ እስከ ስምንት መቶ ይከራያል፡፡ አምስት ፎቅ ሙሉ ሽቅብ የሚራዩ ክፍሎች ቢኖሩም በመጡበት ምሽት አልጋ ማግኘት ግን ዘበት ነው፡፡ ዘለግ ላሉ ጊዜያት ነው ክፍሎቹ የሚያዙት፤ በታማኝ የሱዳኒ ደንበኞች፡፡

በሱዳኒ ባይያዙ በየመኒዎች ይያዛሉ፣ በየመኒ ባይያዝ በሱኡዲዎች ይያዛሉ፤ ክፍሎቹ፡፡ ብቻ እነ ሊያ ቤት ከአንድ የሐበሻ ደንበኛ በፊት አንድ የአረብ ደንበኛ አይጠፋም፡፡ እርግጥ ነው እነ ሊያ ቤት ደንበኛ ንጉሥ ነው፤ አረብ ደንበኛ ደግሞ ንጉሠ ነገሥት ነው፡፡ ዘሀራ ናት እንደዚያ ያለችኝ፡፡

ከማለዳዎች በአንዱ ሎቢው ዉስጥ ለጥቂት አበሾችና ለብ…ዙ አረቦች ቡና አፍልታልን ጀለቢያ የመሰሉ ሲኒዎችን ከበን በአማርኛ ስናማቸው ምን አለችኝ…?

“..ያአኺ…አረብ አይሰስትም፤ ያእኒ…ከወደደህ ምን ልበልህ….በአጭሩ ቲፑ ብቻ ደመወዝ ነው!”

###

ለካንስ ሊያ ብቻ አይደለም በሱዳኒ ሕዝብ የተጥለቀለቀ የእንግዳ ማረፊያ፡፡ ሃያ-ሁለት እና አካባቢው ግዛታቸው ኾኖ የለም እንዴ!! አቢሲኒያ የሚባል አለ፤ አስመሮም የሚባል አለ፣ ሰምሀር አለች፣ ትንሳኤ የሚባልም አለ፣ ኢኮ ገስትሀውስ አለ፣ ሳውዘርን-አዲስ የሚባልም አለ፤ ዘማማ የሚባልም አለ፤ የሓ የሚባልም አለ፣ አሪስተን አለ፣ አዲስቤይ አለ፣ ሜሪ ፔንስዮን አለች፣ ፓሪስ የሚባልም አለ፡፡ እዛ ሰፈር መዓት የሱዳኒ እንግዳ ማረፊያ እንዳለ ተነገረኝ፡፡

ለምሳሌ “አዲሲኒያ” የሚባል ጥቂት ኮከቦችን ግንባሩ ላይ የጣፈ ሆቴል አለ፡፡ ከድሮ ቦሌ ኬክ ቤት ማዶ የሚገኝ፡፡ 10 ፎቅ ወደ ሰማይ ይመዘዛል፡፡ 6ቱ ፎቆች በአረቦች ነው የሚያዙት፡፡ ሀበሻ ደንበኛ በአረብ ደንበኞች 6ለ4 እየተመራ ይገኛል፡፡

“ደንበኞቻችን ቢያንስ በዓመት አራት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ” ትላለች በሊያ የእንግዳ ተቀባይ የኾነችው ኻዲም ዘሀራ፡፡ “አንዳንዶቹ በጣም ከማዘውተራቸው የተነሳ አማርኛን ይሞካክራሉ፡፡ ከኛ ጋ ያእኒ ልክ እንደቤተሰብ ናቸው፡፡”

አስተውችሁ ከኾነ ዘሀራ በየንግግሯ “ያእኒ” የሚል የአረብኛ ቃል ትሰነቅራለች፡፡ ቃሏ ምን እንደሆነች በስንት መከራ ደረስኩባት፡፡ የንግግር አሰናኝ ናት፡፡ በእንግሊዝኛው…You know…it is like…እያሉ እንደሚቀናጡብን ዘመናይ ልጃገረዶች መሆኗ ነው፡፡ “ያእኒ” ማስቲካ እያኘኩ በየመሐሉ ጧ እንደማድረግ ያለች ናት፡፡ …አለ አይደል?! እንደማለት…

###

ከዕለታት በአንዱ ቀን ሱዳኖቹ ለምን አዲስ አበባን ክፉኛ እንደሚያዘውትሩ ዘሀራን ስጠይቃት ቆም-አሰብ አደረገችና…”ያው ያእኒ…ለቢዝነስ፣ እ… ለጉብኝት፣ እ…. ለሥራ… እ….ለእረፍት፣ በዛ ላይ ደግሞ ያእኒ….አየሩ ይመቻቸዋል….” እያለች ከዘረዘረችልኝ በኋላ ፈገግ አለች፡፡ አራት ነጥቧ ፈገግታ ሆነ፡፡ እኔም ፈገግ አልኩኝ፡፡ ተግባብተናል መሰለኝ፡፡

“…እሱማ ያእኒ ሁሉም አረቦች የኛን ሴቶች በጣም ይወዳሉ…!” ብላኝ እንደማፈር አለች፤ ኋላ እፍረቷን ወደ ፈገግታ፣ ፈገግታዋን ወደ ሳቅ አሳደገችው፡፡

###

ሊያ ገስት ሀውስን አልፌ ፍሪደም ሀውስን ተሻግሮ የሚገኘውን አቢሲኒያ ገስት ሀውስ ለመመልከት ስሄድ ገና ወደ ቅያሱ እግሬን ከማንሳቴ አረብኛ ጆሮዬ ዉስጥ ጥልቅ አለ፡፡ የኻርቱም ምናለሽ ተራ የገባሁ እስኪመስለኝ ጥቋቁር አረቦች ጮክ ብለው ያወራሉ፡፡ እኔን ገረመኝ እንጂ በዚያ ሰፈር ድሮም ወይ ትግርኛ ወይ አረብኛ መስማት የተለመደ ነው ተባልኩ፡፡

ለነገሩ አውራሪስና አካባቢውን ላገናዘበ አንዳች ነገር መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ በቅኝ ይዘውታል እኮ፡፡

ባለ ኮከብ ጫት ቤቶች፣ ባለ አረቢያን መጅሊስ ማስቃሚያ ቤቶች፣ ኮርኒሳቸው ላይ ጭስ ማውጫ ሊገጠምላቸው ግድ የሚሉ ሺሻ ቤቶች….ፓፓፓፓ…ቦቅቦቅቦቅቦቅ…

የታፈሩ፣ የተከበሩ መኖርያ ቤት እንደነበሩ የሚያስታውቁ ሙሉ ግቢ ቤቶች ሁሉ ጫት መቃሚያና ማስቃሚያ ኾነዋል፡፡ ማስቃሚያ ባይሆኑ እንኳ መታሻ ናቸው፡፡ ሳውና፣ ስቲም፣ ሞሮኮ፣ ማሳጅ ቤቶች በረድፍ ተደርድረዋል፡፡ ትውፊታዊ የቡና አፍይ ኮረዶችም ከነረከቦታቸው ተሰጥተው ለአረቦች ይቁለጨለጫሉ፡፡ ጉድ ነው ነው ያልኩት…ይሄ ሁሉ የሰፈርና የሰፈራ አብዮት ሲካሄድ የት ሄጄ ነበር ነው ያልኩት፡፡

ሚካኤል-አየር አምባ-ርዋንዳን የሶማሌ አውራጃ ካልን፣ 22-አውራሪስን የአረቦች አልጀዚራ (ደሴት) ማለታችን የግድ ነው፡፡ በተለይ ሱዳኖች ሃያ-ሁለትን ከጃንጃዊድ ሚሊሻ ነጻ ያወጡት ግዛታቸው አድርገው ነው የሚቆጥሩት…፡፡ ወንድ ሐበሻ ሰብሰብ ብሎ ሲያዩ ኤሊያን የመጣባቸው ያህል ነው የሚገላምጡ…፡፡Dagem Massage house

###

ያ አኺ!

እኛ ዐይን ብንሆን ሱዳኖች ቅንድብ ናቸው፡፡ ቅርበታችን ያን ያህል ነው፡፡ ሙዚቃም፣ ናይልም፣ ግድብም፣ ታሪክም አጎራብቶናል፡፡ አልበሽርና ሕወሓት ደግሞ ለልደት ሁሉ እየተጠራሩ አምባሻ ይቆርሳሉ፡፡ ያን ያህል ነው ፍቅራቸው፡፡

በመልክስ ቢባል፤ በጣም ነው እኮ የምንመሳሰል፡፡ እንደው ይቺ ከጥቁር መደብ አይደለንም የምንላት የሀበሻ እብሪታዊ ትርክት እያዘባነነችን እንጂ በአሶሳ በኩል እኮ ከሱዳን ሕዝቦች ጋር አንድ ነን፡፡ ፈካ ያሉት ሱዳኖች ደግሞ ቁ…ርጥ የኛን የመሐል አገር ሰው፡፡

ከነማቻር ጋር ደግሞ ጦርነትና ስደት አዋዶናል፡፡ በቀደም የዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ኢትዮጵያ ዉስጥ ለአንድ ሚሊዮን ጥቂት የጎደሉ ደቡብ ሱዳናዊያን ተጠልለው ይገኛሉ ሲል ሰምቼ ተገረምኩ፡፡ እንግዳ ተቀባይ የሚሉን ይሄን ይሄን እየቆጠሩ እንዳይሆን!?

###

22-አውራሪስ አካባቢ በኖርኩበት አጭር ዘመን አንድ ራሱን ‹‹ባሪያው›› ብሎ ከሚጠራ ሱዳናዊ ጋር ተዋወቅሁ፡፡ ሙዚቃቸው ነፍሴ እንደሆነ በእንግሊዝኛ ስነግረው አውቶማቲካሊ አፈቀረኝ፡፡ ወግ ጀመርን፡፡ ስለ ቴዲ አፍሮ ሁሉ ያውቃል፡፡ የነርሱን ቴዲ አፍሮ በሲዲ ጭኖ ሰጠኝ፡፡ መሐመድ አሚን ይባላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሱዳናዊያን እንደወርዲ የአድናቆት እስክስታ የሚወርዱለት እውቅ ቴዲ አፍሯቸው ነው ፣ መሐመድ አሚን ማለት፡፡

እና ከዚህ ራሱን ባሪያው እያለ ከሚጠራው ሱዳናዊ ጋር ያን ሰሞን እፍ አልን፣ በፍቅር፡፡ ልክ እንደ አልበሽርና እንደ አባይ ወልዱ፡፡

ባሪያው የአረብኛ ቅጽል ስሙ “አቡ አስወድ” ስለሚባል ነው ይህንኑ ወደ አማርኛ ተርጎሞ ራሱን ባሪያው እያለ የሚጠራው፡፡ ሰው ሲተዋወቅ My name is Abu Assuwad But You can call me Bariyaw ይላል፡፡ ድፍን አውራሪስና አካባቢው በዚህ ስሙ ነው የሚታወቅ፡፡

አጋጣሚ ኾኖ እኔና እሱ የተዋወቅነው በባለፈው አልበሽር ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባና ሀዋሳ ከኃይለማርያም ጋር ሽር ብትን በሚሉበት ሰሞን ነበር፡፡ ከአስወድ ጋር ወጋችን መቋጫ አጣ፡፡ እሱም እንደኔ ወሬ ይወዳል፡፡ እኔን ዛሚ ካላችሁኝ እሱን ኡምዱርማን በሉት፡፡ ስናወራ ነግቶ ስናወራ ይመሻል፡፡

ከነገረኝና ካስገረሙኝ ነገሮች ጥቂቱን እንሆ…

መለስንና ስዩም መስፍንን ከካርቱም ወደ ኢትዮጵያ በድል ማግስት ያመጣቸው ፓይለት አጎቱ እንደሆነ አጫወተኝ፡፡ “ወላሂ!” ብሎ ነው የማለልኝ፡፡ አጎቱ ፓይለት ብቻም ሳይሆን የዜናዊ ልዩ ረዳት ሆኖ በክፉው ጊዜ ካርቱም ዉስጥ ከሕወሓቶች ጋር አብሮ የኖረ ሰው እንደሆነም አጫወተኝ፡፡

ታዲያ መለስ በሕይወት በነበረ ጊዜ የአስወድ (ባሪያው) አጎት አዲስ አበባ እየተመላለሰ በቤተ መንግሥት ጥሩ ጊዜ ያሳልፍ እንደነበር አወጋኝ፡፡ ሜዳ ቴኒስ ሁሉ ይጋጠሙ ነበር አለኝ፡፡ “መለስ አጎቴን በጣም ስለሚወደው ለርሱ የሚሆን ጊዜ በፍጹም አያጣም ነበር” አለኝ፡፡ ከሚነግረኝ ምን ያህሉ እውነት እንደሆን ባላውቅም አመንኩት፡፡ ደግሞስ ለምን ብሎ ይዋሻል?

አስወድ (ባሪያው) የዋዛ ሱዳናዊ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከአውራሪስ ሆቴል ገባ ብሎ ወደ አቢሲኒያ እንግዳ ማረፊያ በምታቋርጠው ቂያስ አነስተኛ ፉል ቤት ከፍቷል፡፡ ራሱ ፉል እያበሰለ ይሸጣል፡፡ ፉል ብቻ ሳይሆን አሰድ (ምስር)ም አብስሎ ይሸጣል፡፡ ትንሽዬ የሱዳን ሬስቶራንት አለችው፡፡ በጣም ሚጢጢ እኮ ናት፡፡

አቡ-አስወድ (ባሪያው) ጥ…ቁ…ር ያለ ጥቁር ነው፡፡ ከሰል ራሱ አፍ አውጥቶ “ካንተ እንኳ ትንሽ እኔ እቀላለሁ” የሚለው ዓይነት፡፡ ፈገግ ሲል ታዲያ ነገሩ ሁሉ ይለወጣል፡፡ ድርድር፣ ችምችም ያሉት ጥርሶቹ የስታዲየም ፓውዛ ይሆናሉ፡፡ እንዴት እንደሚያምሩ፡፡ ፈገግታው ለ22ና አካባቢው የሚበቃ ዐይነት ሰው ነው፡፡

ሁለት ቀያይ ሚስቶቹ በዛች ጠባብ የሬስቶራንት ኪችን ዉስጥ ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ አንዷ ሚስቱ የጠይም ቆንጆ ሀበሻ፣ ሌላኛው ደግሞ የደስ ደስ ያላት ሱዳናዊት ናት፡፡ ከሁለቱም በድምሩ 6 ልጆችን ወልዷል፡፡ 2 ከሀበሻዋ፣ 4 ከሱዳናዊቷ፡፡ በነ አስወድ ሃይማኖት በሚስቶች መካከል ፍትሀዊነት የግድ ስለሆነ 2 ልጆችን ከሐበሻዋ የመድገም ሐሳብ አለው፡፡ 4 እኩል እንዲሆኑ፡፡

የሁሉንም ልጆቹን ፎቶ በአይፎን ስልኩ ስክሪን እያጎላ አንድ ባንድ አሳየኝ፡፡ እንዴት እንደሚያማምሩ….

ሁለቱም ሚስቶቹ እየተሳሳቁ በፍቅር አብረው ይኖራሉ፡፡ ደግሞ መመሳሰላቸው፤ …ነገሩ እጅግ አስገረመኝ፡፡ በአስወድ ሚጢጢ የሱዳኒ ሬስቶራንት ዉስጥ ባላንጣዎቹ ኪችን ዉስጥ ቀኑን ሙሉ እየተሳሳቁ ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ መቼ መቼ ነው ታዲያ የሚቀናኑት?

###

አስወድ (ባሪያው) ጋር እያዘወተርን መገናኘት ጀመርን፡፡ እሱ ቤት ቁርስ አልጠፋም ነበር፡፡ ብዙ ሱዳናዊያን ይመጣሉ፡፡

ለካንስ እኛ የአባይ ምንጭ እንደሆንነው ሁሉ ፉል ከሱዳን ነው ምንጩ፡፡ አንድ ጧት ሠርቶ ያበላኝ ፉል ኤርትራዊያን ከሚሠሩት የተለየ፣ እኛም ከምናውቀው ጣፈጥ ያለ እንቁላል አልባ የባቄላ አይስክሬም ነው፡፡ ከትንሿ ባልዲ በማይተናነሰ ብርጭቆ ሻይ ቀዳልኝና ‹‹ ተፈደል!›› አለኝ፡፡ ቅርጥፍጥፍ አድርጌ በላሁት፣ ጭልጥ አድርጌ ጠጣሁ፡፡

ፉል ለነርሱ የቁርስ ምግብ ብቻ አይደለም፡፡ ምሳም እራትም ይደግሙታል፡፡ እንጀራቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለነገሩ ከእንጀራ ሳሳ ያለ “ኪስራ” የሚባል ጠፍጣፋ ዳቦ አዘውትረው ሲመገቡም ዐይቻለሁ፡፡

ታዲያ ከማለዳዎች አንድ ቀን አስወድን “እስቲ ፉጡር (ቁርስ) ምን አለ?” ስለው የፉል ቤት ጠበብት ብቻ አድርጌ እንደቆጠርኩት ገመተ መሰለኝ ሕይወቱን እንደ ዋይት ናይል ረዘም አድርጎ ይተርክልኝ ገባ፡፡

እኔ ታሪኩን በአጭሩ ወደናንተ ሳደርሰው የዋዛ ሰው እንዳልሆነ ነገረኝ ብዬ ማጠቃለል እችላለሁ፡፡ ግን ለምን ቤሳ አድርጌ አልነግራችሁም፡፡

ከአረብኛ ሌላ ጀርመንኛና እንግሊዝኛን አቀላጥፎ ይናገራል፡፡ 2ኛ ዲግሪውን በሙንሽ ዩኒቨርስቲ በጀርመንኛ ነው የተማረው፡፡ አንድ በኢኮኖሚክስ፣ አንድ በፐብሊክ አድምኒስትሬሽን ማስተርስ ዲግሪ አለው፡፡ ብሉ-ናይል (አልኒሉል አዝረቅ) በምትባለው ግዛት የአውራጃው አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ፣ በኋላም ዳይሬክተር አንደነበር ተረከልኝ፡፡ ይህቺ አውራጃ ከአሶሳ የምትዋሰን ናት ያለኝ መሰለኝ፡፡

በዚያች አውራጃ SPLM-N መሽጓል፡፡ ጦርነት ከተከፈተ አራት ዓመት ሞላው፡፡ ሰላም ጠፋ፡፡ እሱም ሚስቶቹንና ልጆቹን ይዞ ወደ አዲስ አበባ ጠፋ፡፡ ሱዳን ደቡብ ኮርዶፋን በሚባለው ግዛት ዉስጥ 6 ቤቶች አሉት፡፡ ብዙም እንዲነዱ አይፈቅድላቸውም እንጂ ለሁለቱም ሚስቶቹ መኪና ገዝቶላቸዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ሁሉንም ነገሩን አጣ፡፡

አልበሽር በሦስት ግንባር ዉጊያ ላይ እንደሆነ ወረቀትና እስክሪብቶ አውጥቶ አስረዳኝ፡፡ በኮርዶፋና ብሉናይል፣ በአብዬ፣ እንዲሁም በዳርፉር፡፡ በምዕራብ ሱዳን የአፍሪካ ደም ያላቸው ጥቁሮች ከአረብ ጥቁሮች ጋር ሲጋደሉ ስንት ዓመታቸው፡፡ በሦስቱም ግንባር በድምሩ 3 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሎ፣ አንድ አምስት መቶ ሺ ሕዝብ ተገድሏል አለኝ፡፡

“በሽር የጦርነት ሱስ አለበት፤ ይኸው 28 ዓመት በጦርነት ማገደን፡፡ ዋላሂ ለአልበሽር ጦርነት መለኮስ ሲጋራ እንደመለኮስ ቀላል ነው፡፡ አላህ ሱባሀነ ወተኣላ ለምን ያንባገነኖችን እድሜ እንደሚያረዝም አላውቅም፡፡” አለኝ…ምርር ብሎት፡፡ ፊቱ ከሰል መሰለ፡፡ ለካንስ ሐዘን ጥቁር ሰውንም ያጠቁራል፡፡

በአገር ሰላም ከሌለ ክብርና ኩራት በመስኮት ብን ብላ እንደምትጠፋ የፉሉ ኤክስፐርት ኢብን አስወድን ዐይቶ ብቻ መመስከር ይቻላል፡፡ አቦ አገራችንን ሰላም ያርግልን!!

ከዚያን ቀን ጀምሮ የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲክስ ቁርስ ላይ ከእንቁላል ፍርፍር ጋር ይፈረፍርልኝ ገባ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አጅሬ ፖለቲካዋን በፉል ለውሶ ያቀርብልኛል፡፡ ኢትዮጵያ በሁለቱ ሱዳኖች ጉዳይ፣ በደቡብ ሱዳን አንጃዎች ጉዳይ፣ በግብጽ ጉዳይ ከመለስ ወዲህ ትክክለኛ አሰላለፍ እንደጠፋባት ተነተነልኝ፡፡

“ይኸው 10 ዓመት ጀርመን የኖርኩ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሊቅ በአዲስ አባባ ፉል አብሳይ ሆንኩልህ፤ እድሜ ለአልበሽር…” አለና በረዥሙ ተነፈሰ፡፡ ፊቱ በድጋሚ ከሰለ፡፡ በድጋሚ አሳዘነኝ፡፡

###

ያ አኺ! አስወድን ለጊዜው እርሳው….

አዲስ አበባ አንዳንድ ሰፈሮቿ በቅኝ ተይዘዋል፡፡ የአረብ ኢምፔሪያሊዝም ነግሶባቸዋል፡፡ በጦርነትም በቱሪዝምም፡፡

ነገሩን ለማስረዳት አራት የወሰን ችካል እናስቀምጥ፡፡

አንድ ጎላጎል ጋ፣ አንዱን አትላስ ጋ፣ አንዱን ትሪኒቲ ሆቴል ጋ፣ የመጨረሻውን ጌታሁን በሻህ ሕንጻ ላይ፡፡ በነዚህ የወሰን ክልል የሚገኘው ሰፈር መኖርያነቱ አብቅቷል፡፡ ወይም እያበቃለት ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህ ሰፈር በአንድ ዘመን የሞጃ ሰፈር ነበር፡፡ ጸጥታው የሚያስቀና፣ ወፎች የሚንጫጩበት፡፡

አሁን ግን ያ ታሪክ ሆኗል፡፡ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ቤታቸውን ለማስቃሚያነት፣ ለፔኒሲዮንነት፣ ለማሳጅ ቤትነት፣ ለዊስኪ ቤትነት እያከራዩ በጥድፊያ ዉልቅ፡፡ ሀበሾቹ ሲወጡ አረቦቹ ይገባሉ፡፡ ለመዝናናት ገንዘብ አይሰስቱም፡፡ አገራቸው የተከለከሏትን በለስ 22 ሰፈር 24 ሰዓት ፈክታ ያገኟታላ፡፡

ይህ ሰፈር አሁን ልጅ የሚያድግበት አልሆነም፡፡ ድሮ ቀበሌ 05 እና ቀበሌ 03 ይባል ነበር፡፡ በአዲሱ የኢህአዴግ ካርታ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ተብሏል፡፡ ሻላ መናፈሻና ዙርያውን ያጠቃልላል፡፡

በዚህ የአዲስ አበባ የምድር ወገብ እያልኩ በምጠራው ሰፈር ዉስጥ ከመቶ የሚልቁ እንግዳ መረፊያዎች አልቆጠርኩም ብላችሁ ነው? ባለ አረቢያን መጅሊስ ሺሻ-ወ-ማስቃሚያ ቤቶች እንኳ የአባልነት መታወቂያ ስለሚጠይቁ ለመቁጠር አይመቹም፡፡ ሌሊት ላይ ቤሊ ዳንስ የሚያስኮመኩሙ አንድ አራት ቤቶች ተዘርዝረውልኛል፡፡

ገላቸው ላይ ስስ ጨርቅ ያጣፉ፣ ጠፍጣፋ ሆዳቸው የተራቆተ ኮረዶች በዚህ ሰፈር -ሽው-እልም የሚሉት እንዲሁ አይደለም፡፡ የአረቦቹ ኻዳሚና ቤሊዳንሰር ሆነው ኑሮን በሪያልና በዲናር እየገፉት ስለሆነ ነው፡፡

###

ያ አኺ!!

በዚህ ዘመን ከአዲስ አበባ አስመራ ከመብረር፣ ከአዲስ አበባ ኻርቱም መብረር ይቀርባል፡፡ በምናብም በጠያራም፡፡ 900 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው እኮ በአየር፡፡ ኻርቱም አፍንጫችን ሥር ናት፡፡ የአንድ ሰዓት በረራ ምናላት፡፡

አውሮፕላኑ በቀን በቀን ሱዳኒዎችን ጭኖ ማምጣት ቢሰለቸው አውቶብሶቹ ተጨምረውለታል፡፡ እነ ስካይ ባስ፣ እነ ሰላም ባስ፣ እነ አባይ ባስ….በመተማ ይሾልካሉ፡፡

ከመስቀል አደባባይ ኻርቱም ሰተት ለማለት 60 ዶላር በቂ ነው፡፡ እንዴ! 22-ለገስት ሀውስ ከአንድ ስስ አንሶላና ከአንዲት ስስ ልጅ ጋር ስንት ነው? ለዚህ ነው አውቶብሶቹ ትርፍ ጭነው ከኻርቱም የሚመጡት፡፡ ችግሩ ካዲሳባ ኻርቱም ተሳፋሪ የለም፡፡

ሙሔ ሐዘን ጨርቆስ (ለዋዜማ ሬዲዮ)