Prof. Measfin Araya

ዋዜማ ራዲዮ- በየካቲት 2014 ዓ.ም አጋማሽ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ጀምሮ የሄደበትን የመጀመሪያ ምዕራፍ ርቀት የሚያሳይና በቀጣይ ሊያጋጥሙ ይችላሉ ያላቸውን ስጋቶች አካቶ የያዘ ባለአራት ምዕራፍ እቅድ ለፓርላማው አቀረበ፡፡

የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበው ኮሚሽኑ ከተመሰረተ አንስቶ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ-ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባዔ፣ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የፍትህ ሚንስትሩና የመንግስት ተጠሪ ሚንስትር በተገኑበት ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርአያ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት፤ የቅድመ ዝግጀት፣ የዝግጅት፣ የምክክር ወይንም የክንውን እንዲሁም የምክክር ውጤቶች መተግበሪያ በሚል  በአራት የተከፈሉ እቅዶችን አስተዋውቀዋል፡፡

በመጀመሪያው የዝግጅትና የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ከተከናወኑና እየተከናወኑ ካሉ የተወሰኑ ተግባራት መካከል በቀድሞው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እና የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች ይጠቀሙበት የነበረውን ቢሮና በጀት ወደ አዲሱ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማዛወር ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ኮሚሽኖች ይሰሩ 41 ሰራተኞች መካከል 40 የሚሆኑትን ወደ ኮሚሽኑ በማጠቃለል በጊዜዊነት በመመደብ በአዲስ መልክ ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአዋጁ ጽንሰ ሃሳብ ላይ ግልፅነት ለመፍጠር ከህግ ባለሙያዎች ጋር መወያየቱን፣ በአገራዊ ውይይት ዙሪያ ተሞክሮ ያለቸው የሲቪክ ማህበራትን፣ የሚዲያ ተቋማትና ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሃገር ሽማገሌዎችና እናቶች ጋር የትውውቅ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችን ሊመሩ የሚችሉ ገለልተኛ የሆኑ አወያዮችንና አመቻቾች 11 አባል ባለው የኮሚሽነሮች ምክርቤት አማካኝነት ተመርጠው ስልጠና እንደሚሰጡና የአጀንዳ ቀረጻ የሚሰራ መሆን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የክንውን ወይንም የምክክር ተብሎ በቀረበው ምዕራፍ  አገራዊ ምክክሩ የሚጀምርበት፣ በርካታ የሎጅስቲክ እንቅስቃሴና የሰው ሃይል በስፋት የሚያስፈልግበት ሂደት መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አንስተዋል፡፡

በዚህ ምዕራፍ  ከገዥው ፓርቲና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ሚዲያ ተቋማት ጋር ስለሚኖሩ ግንኙነቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተለያዩ ውይይቶች እንደሚኖሩ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የምክክር ውጤቶችን መተግበሪያ ምዕራፍ ላይ በውይይት ወቅት የተገኙ ግብዓቶችን መሰረት በማድረግ ዘላቂ መፍትሄዎች ተቀምረው ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንደሚቀርቡና ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ አስታቀውቀዋል፡፡

ይሁን እንጅ ዋና ኮሚሽነሩ እስካሁን ባለው ሂደትና በቀጣይ ኮሚሽኑ በሚኖረው የሶስት አመታት እድሜ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉና ለወደፊትም ሊያጋጥሙ ይችላሉ ያሏቸውን ተግዳቶሮች አቅርበዋል፡፡

ለአብነትም ከተጠቀሱ ተግዳሮቶች መካከል ስለኮሚሽኑ ያሉ አረዳዶች መለያየት፣ ከኮሚሽኑ ከመጠን በላይ መጠበቅ፣ ኮሚሽኑ ላይ ጥርጣሬ መፈጠር ፣ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችና በርካታ የተከማቹ አጀንዳዎች መኖር የሚሉትን ዋና ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በርካታ የኮሚሽኑ አባላት ለአገር ብለው የሞቀ ስራቸውን ለቀው ወደዚህ ስራ ሲገቡ ግዴታቸውና ሃላፊነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በመንግስት በኩል ሊሟሉላቸው የሚገቡ ጥቅማ ጥቀሞች እንዲታሰብበት ፓርላማውን ጠይቀዋል፡፡

ምንም እንኳ የኮሚሽነሮች ሹመቱ በሚንስትር ማዕረግ ቢሆንም የሚከፈላቸው አጠቃላይ ገንዘብ ተደማምሮ ከ28 ሽህ ብር እንደማይበልጥና ይህ ገንዘብም አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ምክያት በዚህ ገንዘብ ምን አይነት ቤት ተከራይተው መኖር እንደሚችሉ ለፓርላማው ማስረዳት አይጠበቅብኝም ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ‹‹ እንደዋና ኮሚሽነርም እንደዚህ አይነት  የመብት ጥያቄዎችን የመጠየቅ ግዴታ አለብኝ ››  ብለዋል፡፡

በቀጣይ የውይይት ሂደት ከተወያዮች ሊመጡና ሊነሱ ስለሚችሉ በርካታ አጀንዳዎች የተናገሩት የምክክር ኮሚሽነር አቶ ዘገየ አስፋው በበኩላቸው ‹‹ ክምር የሆኑ›› ረቂቅ አጀንዳዎች ቢመጡ አካተችነት አንዱ የኮሚሽኑ መርህ በመሆኑ የማንን ሃሳብ ጥሎ የማንን መውሰድ እንደሚቻል አዳጋችና ኮሚሽኑ ከተፈቀደለት ጊዜ በላይ ሊወሰድ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ መልስ ሲሰጡ የጥቅማጥቅም ጉዳይን ለመፍታት እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን አጀንዳ መለየትን በተመለከተ ሳይንሳዊና ወካይ በሆነ መንገድን በመጠቀም ልምድ ያላቸውን ምሁራንን በማሳተፍ ጉዳዩ ባልተገባ ሁኔታ እንዳይጓተት እንዲሁም ውይይትና ምክክሩ የታሰበለትን ዓላማ  ሊያውክ በሚችል መልኩ መፍጠን እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]