ዋዜማ ራዲዮ- አዲስ አበባ ውስጥ ይገነባሉ ተብለው እቅድ ከተያዘላቸው የአውቶቡስ መናኽሪያ (ዴፖ) መካከል ሁለተኛው የቃሊቲ መናኽሪያ ነገ ቅዳሜ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል፡፡

ቃሊቲ አውቶቡስ ዴፖ 789.5 ሚሊየን ብር በጀት በቻይናው ሲኤስሲኢ(CSCE) በተባለ የቻይና የግንባታ ተቋራጭ የተገነባ ሲሆን የማማከር ስራው ኢቲጂ በተባለ የሀገር ውስጥ ዲዛይነርና ማማከር ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተከናውኖል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት መሰረተ ድንጋይ የተጣለው በቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ነበር የካቲት 3 2009 አመተምህረት ነበር፡፡

ስፍራው የገበሬዎች ይዞታ የነበረ ሲሆን አስፈላጊው የካሳ ክፍያ ተደርጎ ግንባታው ተከናውኗል፡፡

በአንድ ጊዜ ከ250እስከ300 አውቶቦሶችን ያለመጨናነቅ የማቆም አቅም ያለው አውቶቡስ ዴፖው ከመሬት በታች (Under ground) 89 አውቶብሶች መያዝ ይችላል፡፡ከዚህ ቀደም አውቶብሶቹ ማደሪያቸው ነዳጅ መቅጂያ አና የመጠገኛ ስፋራቸው የተለያየ ስፍራ በመሆኑ የተነሣ አስቸጋሪ ወጪውም ከፍተኛ ነበር፡፡

የቃሊቲ የአውቶቡስ ዴፖ በአንድጊዜ 9 አቶብሶችን መጠገን እንዲችል ተደርጎ ተሰርቶል ፡፡የአንበሳ እና የሸገር አውቶቢሶች የሚገለገሉበት ዴፖ በሁለት ደቂቃ መኪናን ማጠብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሲኖረው ቀለምም በግቢው ውስጥ እንዲቀቡ ይደረጋል፡፡

በከተማው አስተዳደር ስር የሚተዳደሩ አውቶቢሶች አሁን ከሸጎሌ እና ቃሊቲ የአውቶቡስ ዴፖውች ከአንድ ማዕከል የስራ ስምሪት እና ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡

ገርጂ አካባቢ በሚገኘው አንበሳ ገራጅ በቀጣይ የአውቶቢስ ዴፖ ለመግንባት ታቅዶ የመጀመሪያ ጨረታ ሂደቱ ተጠናቆ ወደስራ ለመግባት ታስቦ የነበረ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ትኩረቱን ወደሌሎች ጉዳዮች በማዛሩ ለጊዜ ቆሞል፡፡ በገርጂው የአንበሳ ገራዥ የሚሰራው ዴፖ 850 አውቶብሶችን የሚያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እንደሚሰራ እቅዱ ያሳያል ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በአስር አመታት ውስጥ 3ሺ አውቶብሶች ወደ ከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት የማስገባት እቅድ አለኝ ያለ ሲሆን የሚያስገነባቸው ዴፖችም ይህን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡

የቃሊቲ አውቶቡስ ዴፖ ግንባታውከተጠናቀቀ በኋላ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ነገ ቅዳሜ ግንቦት 8 በይፋ ይመረቃል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]