ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ መስተዳድር በፌደራል ቤቶች አስተዳድር በኩል ለአንበሳ ፋርማሲና ለኒዮን አዲስ ያከራየውን ታሪካዊ ሕንፃ ለቀው እንዲወጡ አዟል።


የፌደራል ቤቶች አስተዳድርም ትዕዛዙን በከተማ ደረጃ ባለው መዋቅር ለተከራዮቹ አድርሷል። የአዲስ አበባ መስተዳድር ሕንፃው የሚገኝበትን ቦታ ጀርመን አመንቴ ለተባሉ ባለሀብት እንዲያለሙት በሊዝ መስጠቱን አስታውቋል።


ጀርመን አመንቴ በቦታው ላይ የገበያ ማዕከል ለመገንባት ዕቅድ እንዳላቸውም ተረድተናል። ሕንፃው ካለው ታሪካዊ ፋይዳና በቅርስነት በመመዝገቡ ጥበቃ የሚያስፈልገው መሆኑን በመጥቀስ የሚነሳውን ቅሬታ በተመለከተ የአዲስ አበባ መስተዳድር ሕንፃውን የማፍረስ ዕቅድ እንደሌለው ይልቁንም አካባቢውን የሚያለሙት ጀርመን አመንቴ ቅርሱን ለመጠበቅ ሀላፊነት እንደሚወስዱ ይገልፃል።


የጀርመን አመንቴ የገበያ ማዕከል ሲገነባ የሚኖረውን ገፅታና ቅርሱ ሳይነካ ግንባታው እንዴት ሊካሄድ እንደታሰበ ለህዝብ የቀረበ መረጃ የለም።


ዋዜማ በወቅቱ እንደዘገበችው ፣ ባለፈው ዓመት በከተማዋ ካቢኔ ውሳኔ የተሰጠበት የልማትና የአምልኮ ቦታዎች የሊዝ ጨረታ ወቅት በባለሀብቱ የቀረበው የግንባታ ዕቅድ 7, 656 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ ለመኖሪያና ለንግድ ቅይጥ አገልግሎት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የካፒታል አቅም እንዳላቸው ገልፀው በመነሻ ዋጋ 2 ሚሊየን 213 ሺህ ብር ፀድቆላቸዋል።

ጀርመን አመንቴ የሊዝ ጨረታውን ማመልከቻ ያቀረቡት ከሶስት ዓመት በፊት ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]