ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ሰፊ የመሬት ወረራ፣ ይፋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የመሬት ዕደላ፣ በህዝብ ገንዘብ የተሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግልፅ ባልሆነ መንገድ ዕጣ ላልደረሳቸው ሰዎች መስጠት ባለፉት ወራት በስፋት የታዩ ክስተቶች ናቸው። በጉዳዩ ላይ የከተማው አስተዳደርም ሆነ ያገባኛል የሚል የመንግስት አካል ማብራሪያና ምላሽ አልሰጠም። ችግሩን ለማቆም የሚያስችል እርምጃም አልወሰደም። የከተማው ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የችግሩ አካል እንጂ ችግሩን ለመፍታት ሙከራ እንኳን ሲያደርጉ አልታዩም። ከመሬት ቅርምትና ከጋራ መኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ነዋሪ ምላሽ ከሚፈልግባቸውን ጉዳዩች ዋዜማ ከዚህ በታች በግርድፉ ተመልክታለች።

ቤት ለተሰጣቸው ተፈናቃዩች ሌላ የተሻለ ቤት የመገንባት ዕቅድ

ከሁለት አመት በፊት በኦሮምያ እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ሳቢያ ከመኖርያ ቀዬአቸው ከተፈናቀሉት ውስጥ በአዲስ አበባ ለሰፈሩት ተፈናቃዮች የከተማ አስተዳደሩ ተለዋጭ አዲስ ቤት እንደሚሰራላቸው ራሳቸው ታከለ ኡማ ለተፈናቃዮቹ መናገራቸውን ለማረጋገጥ ችለናል። ይሄም የቤት ግንባታ በፍጥነት የሚተገበር እንደሆነ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል። ዋዜማ ራዲዮ ይህን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ኮዬ ፈጬ የጋራ መኖርያ ቤቶች አካባቢ ካሉት የተፈናቃዮች መኖርያ ውስጥ ከሚኖሩ ነዋሪዎችና ከከተማ አስተዳደሩ ምንጮቻችን ማረጋገጥ ችለናል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ለተፈናቃዩቹ የተሻለ ቤት ለመገንባት መጀመርያ ቃል የገቡት ይህን ቃል የገቡት የረመዳን ጾም ፍቺ በአል እለት የበአል ማክበሪያ ስጦታን በመኖሪያ ቤቶቹ ላሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለማበርከት ወደ ስፍራው በሄዱበት ወቅት ነው። በስፍራው ላሉ ተፈናቃይ የኦሮሞ ተወላጆች አሁን ከሚኖሩበት የተሻለ ቤት ተገንብቶላቸው ወደዚያው እንደሚገቡ ቃል ገብተውላቸዋል።

በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታ በተነሳ ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች እያንዳንዳቸው በ48 ካሬ ላይ ያረፉ በሺዎች የሚቆጠሩ የብሎኬት ቤቶች በብዙ ወጭ ከተገነባ በሁዋላ : በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃይ አባወራዎችም በዚያው ቤቶቹ ተረክበው መኖር ከጀመሩ በሁዋላ እንደገና ተለዋጭ ቤት ይገነባላችሁዋል በሚል ምክትል ከንቲባው መናገራቸው ግርታንና ጥያቄን የሚያስነሳ ሆኗል።


ዋዜማ ራዲዮ ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማችው ለተፈናቃዮቹ በተሰሩት ቤቶች ውስጥ በአባወራ ደረጃ ወደ ሰባት መቶ የሚጠጉ : በግለሰቦች ደረጃ ሲቆጠር ደግሞ 2, 700 አካባቢ ሰዎች ይኖራሉ። በጥቅሉ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ሲሆን በቀጣይም በአዲስ አበባ ዙርያ በጊዜያዊ የቆርቆሮ መጠለያዎች ውስጥ እየኖሩ ያሉ ተፈናቃዮችም ወደዚሁ ኮዬ ፈጬ ኮንደሚኒየም አካባቢ እየተሰሩ ባሉ ቤቶች ተዘዋውረው ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለተፈናቃዮቹ አዲስ የመኖሪያ ቤት የሚገነባ ከሆነ አሁን እየተገነቡ ያሉትና ከዚህ ቀደም የተገነቡት መኖሪያዎች ለምን ዓላማ እንደሚውሉ አልያም ላማን ተላልፈው ሊሰጡ እንደታሰበ የተገለፀ ነገር የለም።

 ምክትል ከንቲባ ታከለ በዚሁ የረመዳን ጾም ፍቺ በአል ላይ በስፍራው ተገኝተው በኦሮምኛ ቋንቋ የእንኳን አደረሳችሁና ንግግር ካደረጉ በሁዋላ ቀጥሎ በአማርኛ ባሰሙት ንግግር ነው ለነዋሪዎቹ ተለዋጭ ቤት እንደሚሰሩላቸው የገለጹላቸው።
ምክትል ከንቲባው በዚሁ ንግግራቸው ; ተፈናቃዮቹ በነዚያ ቤቶች የሚኖሩት ጸሀይ ላይ ከሚሆኑ ለጊዜው በተገነቡት ቤቶች ቢሆኑ የተሻለ እንደሆነ በማሰብ : አሁን የሚኖሩበት ቤት የሚገባቸው እንዳልሆነና በጊዜያዊነት የሚኖሩበት እንደሆነ ገልጸውላቸዋል።
ምክትል ከንቲባው አክለውም ተፈናቅለው በስፍራው ላሉት ነዋሪዎች የተሻለ ቤት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመርና ወደዛም እንደሚዘዋወሩ ; አሁን ያሉበትን ቤትም እንደ ጊዜያዊ መኖርያ እንዲወስዱትም ገልጸውላቸዋል። ታከለ ኡማ ይህን ሲናገሩ የከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የመንግስታዊ አገልግሎቶች አስተባባሪ እንዳወቅ አብጤ እና የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ተስፋዬ በልጅጌ በስፍራው ነበሩ።

ምክትል ከንቲባ ታከለ በንግግራቸው አዲሶቹ ቤቶች የት እንደሚገነቡ አልገለጹም።
አሁን ላይ ኮዬ ፈጬ ኮንደሚኒየም አካባቢ ከኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተሰሩት ቤቶች አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከሚኖርባቸው ቤቶች አንጻር ጸሀይ ለመከላከል የሚባሉ እንዳይደሉ የቤቶቹን ቁመና ያየ ሊመሰክረው የሚችለው ሀቅ ነው።

በሌላ በኩል ግጭት የነበረባቸው ቦታዎች አሁን ላይ ሰላም ያለ እንደመሆኑ ተፈናቃዮቹም ወደዚያ ተመልሰው የቀድሞ ኑሯቸውን እና ስራቸውን መቀጠል ሲችሉ በተለያዩ መጠለያዎች አቆይቶ ቋሚ ተረጂ የማድረጉ ነገር ተገቢ እንዳልሆነ ይነሳል። ይህም ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ኮዬ ፈጬ ኮንደሚኒየም አካባቢ የተሰሩት “ሰርቪስ ቤቶች” ሲሆኑ አሰራራቸውም ቦታና ወጪ ቆጣቢ ያልሆነ በደፈናው የቦታ ብክነት የታየበት እንደሆነ በመሀንዲሶች ይተቻል። በዚህ ቦታ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዙርያ እና በብዙ የኦሮምያ ከተሞች በመጠለያ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ያለ ስራ ተረጅ ሆነው እንዲቆዩ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑ ይነሳል።

የጋራ መኖርያ ቤቶች እደላው ነገር

በአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመኖርያ ቤት እጦት እንግልት እየደረሰባቸውና እየቆጠቡና እጣም ወጥቶላቸው ቤቶችን መረከብ ሳይችሉ በቆዩበት በአሁኑ ጊዜ የከተማ አስተዳደሩ የጋራ መኖርያ ቤቶችን በተመለከተ እየተከተለ ያለው አካሄድ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬ አሳድሯል።

 ከ18 ሺህ በላይ የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች ለባለ እድለኞች ባለፈው አመት እጣ ወጥቶላቸው የቤቱን 40 በመቶ ዋጋ በመክፈል ውል ገብተው ቀሪውን 60 በመቶ ብድር መክፈል ጀምረውም ብዙዎቹ ቤቶች ተጠናቀው እስካሁን አልተሰጣቸውም። በጎን ግን መገናኛ ገቢዎች ሚኒስቴር አጠገብ ያሉ የተወሰኑ ብሎኮች ገቢዎች ሚኒስቴር ራሱ ለሰራተኞቹ ገዝቷቸው ነው ተብሎ እየተኖረባቸው ነው። በጋራ መኖርያ ቤት መርሀ ግብር ተሰርተው በዚህ መልኩ መሸጣቸውም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

በሌላ በኩል ካለፈው አመት ወዲህ በተለያዩ ሳይቶች ያሉ ባዶ የጋራ መኖርያ ብሎኮች ግልጽ ባልሆነ መልኩ ለግለሰቦች እየተሰጡ ነው።ዋዜማ ራዲዮ የኦሮምያ ክልል ሰራተኞች የቤቶቹ ባለቤቶች ውስጥ እንዳሉበት አረጋግጣለች። እጣ ወጥቶላቸው እስካሁን መረከብ ባለመቻላቸው ችግር ውስጥ ላሉ ባለ እድለኞች በፍጥነት መፍትሄ ሳይቀመጥ የከተማ አስተዳደሩ ለሌላ የጋራ መኖርያ ቤት እደላ መጣደፉም አጠያያቂ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ከሀያ ሺህ በላይ የጋራ መኖርያ ቤቶች መሰጠቱ ይታወሳል።በጋራ መኖርያ ቤቶች ስር ያሉ የንግድ ቤቶችም የካሳው አካል ናቸው።

ባለፉት ወራት በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ትእዛዝ የጋራ መኖርያ ቤቶችን : ቤቶቹን ለማግኘት ላልቆጠቡ የኦሮምያ ክልል ሰራተኞች እንዲሰጥ መደረጉን ዋዜማ ከራሳቸው ከዕድሉ ተጠቃሚዎች አረጋግጣለች።

መንግስታዊ ድጋፍ ያለው የመሬት ቅርምት

 በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የመሬት ወረራ መንግስታዊ መደበኛ ስራ የሚመስል ገጽታ አለው። ድርጊቱ ከከተማ አስተዳደሩ ዋና መስሪያ ቤት እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ በመናበብ እየተከወነ ያለ ነው። ቦሌ : አቃቂ ቃሊቲ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች አሁን ላይ በዋናነት የመሬት ወረራው የሚከናወንባቸው ናቸው። በነዚህ ክፍለ ከተሞች በተለያየ ምክንያት ሰፋፊ ባዶ ቦታዎች ያሉ በመሆኑ ወረራው ተጧጡፎባቸዋል። በዚህ ውስጥ በአንድ ይዞታ ብቻ በቦታ አጣሪዎችና በክፍለ ከተማ የመሬት ባንክ ሀላፊዎች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናት መካከል ሚሊየን ብሮች ይንቀሳቀሳሉ።ዋዜማ ራዲዮም ይሄን አረጋግጣለች።

 ለአብነት ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አማካይ ከሆነው በተለምዶ ስሙ ሀይሌ ጋርመንት ከሚባለው ሰፈር ጀምሮ በገላን ኮንደሚኒየም ጀርባ አልፎ አቃቂ ኬላ እስከሚባለው አካባቢ ብዙ ቦታዎች አስፓልት ዳርም ሆነ ውስጥ ለውስጥ ታጥረው ይታያሉ።በጀሞ : ለቡ እንዲሁም በሰሚት ሰፊ የመሬት ወረራዎች ተካሂደዋል : እየተካሄደም ነው። እነዚህ ወረራዎች በተለያዩ መንገዶች እንደሚካሄዱ ዋዜማ ራዲዮ ተረድታለች።

ግለሰቦች የልማት ተነሽ አርሶ አደር መሆናቸውን የሚያሳይ የተጭበረበረ ሰነድ በጉቦ እንዲሰራላቸው ማድረግ አንዱ መሬት መቸብቸቢያ መንገድ ነው። ይህ የተደረገለት ግለሰብ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለክፍለ ከተሞች መሬት ነክ ሰራተኞች እንደሚከፍል አረጋግጠናል። ሰነድ የሚዘጋጅለት ግለሰብም ለራሱ 500 ካሬ ሜትር : በልጆቹ ስም ደግሞ ከ70 ካሬ ሜትር ጀምሮ እንዲገዛ ሊመቻችለት ይችላል። የመሬቱ ባለቤት የሚሆነው ግለሰብም ለከፈለው በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የልማት ተነሽ አርሶ አደር እንደሆነ የሚያሳይ ሙሉ ሰነድ ተዘጋጅቶ ይሰጠዋል ይዞታውንም ያጥራል። በዚህ ሂደት ውስጥ የመሬት ባንክ ሰራተኞች ይዞታን የተመለከቱ ቁልፍ ሚናን ይወጣሉ። በመሀል ባለ ገንዘብ ግለሰብንና የመንግስት ሰራተኞችን የሚያገናኙ ደላሎች አሉ።
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከአርሶ አደሮች ከ400 ሺህ ካሬ መሬት በላይ በአቶ ለሚ ታዬ ተጭበርብሮ ከተወሰደ በሁዋላ በተቀናጀ ስራ አስመልሰናል ካሉ በሁዋላ መሬቱ ባልታወቀ ሁኔታ እየተሸነሸነ መታጠር መጀመሩን ተመልክተናል። 

 ሌላው የመሬት ቅርምት መንገድ መሬት ባንክ ውስጥ የሌሉ መሬቶችን እየለዩ ማጠር ነው። ይህ በብዙ የከተማው አካባቢዎች የታየ ግልጽ የመሬት ችብቸባ ነው። ቆይቶ ተጠያቂነት እንዳይመጣ ይዞታዎችን ከመሬት ባንክ የማውጣት ስራዎችም ይሰራሉ። ነገሩ ተራ ህገወጦች ብቻ በየስፍራው የሚያጥሩት የመሬት ጉዳይ ሳይሆን በርካታ ሚሊየን ብሮች በየእርከኑ ያሉ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች ኪስ የሚያስገባ የመሬት ወረራ ሂደት ነው። በየጊዜው መሬት ተወረረ በተባለ ማግስት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የክፍለ ከተማ አመራሮችና የጸጥታ ሀይሎችን ሰብስበው እርምጃ እንዲወሰድ ግብረ ሀይል አቋቁሜያለሁ ይሉና : ለይስሙላ የተወሰኑ መሬት ወራሪዎች ሰለባ ይሆኑና ቀሪው እንደተወረረ መቆየቱ ነው።

አድሏዊ አሰራር

 ታከለ ኡማ በምክትል ከንቲባነት በሚመሯት ከተማ ብዙ አድሏዊ ስራዎች እንደሚሰሩ ቅሬታዎች ይቀርባሉ። በተለይ ከስራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያሉ አሰራሮች ብዙ ጉድለት ያለባቸው ናቸው ።በርካታ ወጣቶች አዲስ ብድርና ቁጠባ ያበደራቹኋል ተደራጅታችሁ የንግድ ፍቃድ አውጡ : ለስድስት ወራት የመስሪያ ቦታ ተከራዩ ተብለው የስድስት ወር ክራይ ከከፈሉ በሁዋላ ብድር ተሰጥቶ አልቋል : የምንሰጣቹ ገንዘብ የለም መባላቸውን ለዋዜማ ራዲዮ ቅሬታ ያቀረቡ አሉ። ዋዜማ ራዲዮ ብድሩ አይሰጣችሁም መባላቸውን ከአዲስ ብድርና ቁጠባም አረጋግጧል። የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ያለ ምንም በቂ ተያዥ ሲሰጥ እንደነበርም ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የጋራ መኖርያ ቤቶች ዙርያ ያሉ ቦታዎች በላስቲክና ቆርቆሮ የሚሸነሸኑ የንግድ ቦታዎችም የሚሰራጩበት መንገድ እንዲሁ አድሏዊ ነው።

የምክትል ከንቲባው ቢሮ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን ለሁለት ወራት ያህል ደጋግመን ብንጠይቅም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።[ዋዜማ ራዲዮ]