old-qerraዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ አሮጌው ቄራ በሚባለው ጭርንቁስ ሰፈር ይገኝ የነበረው ሰፊ ገላጣ ሜዳ በተለምዶ “ጉርሻ ሜዳ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በጉርሻ ሜዳ በስፋት እንደሚነገረው “ጉርሻ” አይሸጥም፡፡ ኾኖም ትራፊ ምግቦች በስስ ፌስታል እየተቀበቡ  አምስት፣ አምስት ብር ለድሆች የሚቸረቸርበት ሥፍራ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ላለፉት ዓመታት የከተማዋ ችግረኞች ምሳና እራት በፌስታል የሚሸምቱበት ይህ እውቅ ስፍራ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ አገልግሎቱን እንዲያቋረጥ ተደርጓል፡፡ የወረዳ 1 የአሮጌው ቄራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያና የአራዳ ክፍለ ከተማ ጤና ቢሮ ናቸው በጋራ አካባቢው እንዲዘጋ የወሰኑት፡፡  በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሆች በአካባቢ ሜዳ ላይ ተመግበው በዚያው አካባቢ ፈንጠር ብለው ስለሚጸዳዱ ለጤናቸው አደገኛ ኹኔታ ተፈጥሯል ተብሏል፡፡

ከጤና ስጋት ባሻገር ፖሊስ አካባቢው የወንጀለኞች መሸሸጊያ እየኾነ መምጣቱን ይናገራል፡፡ በስፍራው በቁጥር በርከት ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎችና ሥራ አጥ ወጣቶች ምሳና እራት ሰዓት ላይ የሚገኙ ሲኾን ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አቅመ ደካሞችና ነዳያንም አካባቢውን ያዘወትሩታል፡፡ በየቀኑ በግምት ከአምስት መቶ አምሳ እስከ ሰባት መቶ ሰዎች በአንድ ጊዜ ምሳና እራት ለመመገብ ወደዚህ ቦታ ይመጣሉ ተብሏል፡፡

“ጉርሻ ሜዳ” ዘወትር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዙርያ ከሚገኙ ሆቴሎች የተሰበሰቡ ትራፊ ምግቦች በትልልቅ ማዳበሪያዎች ተቋጥረው በሰው ጉልበት ተጭነው በነጋዴዎች አማካኝነት ስፍራው ከደረሱ በኋላ በልብስ ማጠቢያ ሳፋ ላይ ይገለበጣሉ፡፡ ከዚያም ተመጋቢዎች ሲመጡ በስስ ፌስታል እየተቋጠረ ለችርቻሮ ይቀርባል፡፡ እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ትራፊ ምግቡን በአምስት ብር ገዝተው እዚያው ቁጢጥ በማለት በደቦና በተናጥል ይመገቡታል፡፡ ይህ የሚኾነው በጠራራ ፀሐይ ከቤተ መንግሥት ወደ ንግድ ማተሚያ በሚወስድ አዲስ አስፋልት ዳርቻ ነው፡፡ የተመጋቢዎች ከዕለት ዕለት በቁጥር እየጨመረ መምጣት እንዲሁም ተመጋቢዎች ከሄዱ በኋላ ደግሞ ሥፍራው ላይ የሚያንዣቡቡ ጆፌ አሞራዎች በስፋት መታየት የጤና ባለሞያዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ ቦታውን የሚያዋስነውን የሸራተን ማስፋፊያ ሰፊ ሜዳን ጨምሮ ወንጀለኞች በዚያ አካባቢ መበራከታቸው አሳስቦታል፡፡

ከትናንት በስቲያ አካባቢው በፖሊስ አሰሳ ከተደረገበት በኋላ የተወሰኑ የምግብ ሻጮች በማዳበሪያና በጆንያ ከያዙት ትራፊ ምግብ ጋር በፖሊስ ታፍሰው ተወስደዋል፡፡ በአካባቢው የተለመደው የምግብ መቸርቸር ሥራም ትናንትናም ኾነ ዛሬ እንዳልተካሄደ ለመመልከት ችለናል፡፡ ይልቁንም በርከት ያሉ ፖሊሶች በአካባቢው ቆመው ለምግብ ግዢ የሚመመጡ ደንበኞችን ሲበትኑ ታይተዋል፡፡

በአካባቢው በልማት ምክንያት በርካታ ጭርንቁስ ቤቶች የፈረሱ ቢኾንም አዳዲስ ግንባታዎች ለአመታት ባለመካሄዳቸው ተፈናቃዮች ተመልሰው ቦታው ላይ ተጠልለው ይታያሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጠጊያ ያጡ እጅግ ድሀ የኾኑ ነዋሪዎች በከፊል በፈራረሱ ቤቶች ገብተው ይኖሩባቸዋል፡፡ በሥፍራው የላስቲክ ቤት ቀልሰው የሚኖሩ ዜጎችም በርካታ ናቸው፡፡ አካባቢው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የሚገኝ ሲኾን ከቴዎድሮስ አደባባይ አምፊ ቲያትር ጀርባ ይዞ እስከ ቤተ መንግሥት ጋራዥ፣ እንዲሁም ከሊሴ ገብረማርያም የጀርባ በር ጀምሮ ኦርማ ጋራዥን ይዞ እስከ ሸራተን ማስፋፊያ አጥር የሚገኙ ሰፈሮችን የሚያካትት ነው፡፡

በተያያዘ ዜና ከዚሁ የአሮጌው ቄራ ጉርሻ ሜዳ አቅራቢያ አዲስ የተሠራውን አስፋልት ተሻግሮ ለሸራተን ማስፋፊያ ተብሎ በከፊል በታጠረው ሰፊ ሜዳ ላይ ከበድ ያሉ ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ አንድ የፖሊስ መኮንን ለዋዜማ ተናግሯል፡፡ ከሁለት ወር በፊት በሸራተን ማስፋፊያ ሜዳ በጎረምሶች በቡድን የተደፈረች ሴት መኖሯንና ከቀናት በኋላ ራሷን እንዳጠፋችም ይኸው የፖሊስ መኮንን ለዋዜማ ተናግሯል፡፡ ኾኖም ጉዳዩ ወደ ሚዲያ እንዳይደርስ ስለተወሰነ በፖሊስ ፕሮግራም እንኳ አልተነገረም ይላል፡፡

አካባቢው ተደጋጋሚ ወንጀሎች የሚፈጸሙበት፣ በጠራራ ፀሐይ የሞባይል ነጠቃ የሚካሄድበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህም የሚኾነው ለሸራተን ማስፋፊያ የተያዘው ቦታ የመሬት አቀማመጥ ከ20 ሄክታር በላይ የሚሰፋ ወጣ ገባ የበዛበት ከመሆኑም ባሻገር ለመሸሸግ ምቹ በመኾኑ ነው፡፡ የጸጥታ ኃይሎችም ቢኾን ወደ ውስጥ ገብተው ክትትል ለማድረግ የሚደፍሩት ሥፍራ አልሆነም፡፡ በአካባቢው ከመሸ በኋላ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ መብራት ስለሌለው አስፈሪ ገጽታን ይላበሳል፡፡ የፖሊስ ኃይልም ቢኾን ወደ ስፍራው አይጠጋም፡፡ በዚህም የተነሳ ለወንጀልና ለወንጀለኞች መሸሸጊያ ምቹ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በቡድን እንደተደፈረች የተገለጸው የዚህች ሴት ዝርዝር ማንነት በይፋ ማወቅ ባይቻልም ድርጊቱ መፈጸሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ጭምር እንደሚያውቁ የዋዜማ ሪፖርተር በአካባቢው በተዘዋወረችበት ወቅት ማረጋገጥ ችላለች፡፡ በዚህ ለሸራተን ማስፋፊያ ተብሎ በታጠረ አደገኛ ስፍራ በአምስት ወንዶች እንደተደፈረች የተነገረው ይህች ሴት ከአዳማ እንደመጣች የታወቀ ሲኾን በቀጣይ ቀናት ደፋሪዎቿን ጠቁማ ካስዝያዘች በኋላ ራሷን እንዳጠፋች ተነግሯል፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን ለሕዝብ ያላሳወቀው በባለሀብቱና በመንግሥት ላይ አሉታዊ ምስል ይፈጥራል በሚል እንደሆነ ለዋዜማ ሐሳቡን ያጋራው ይህ የፖሊስ መኮንን ግምቱን ሰጥቷል፡፡

በሸራተን ማስፋፊያ ሜዳ ዉስጥ ዉሀ ያቆሩ ኩሬዎች ተፈጥረዋል፡፡ በዚያ ገላቸውን የሚታጠቡና ልብሳቸውን የሚያጥቡ የጎዳና ልጆችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ የሸራተን ማስፋፊያ ሜዳ ተብሎ የታጠረው ስፍራ ከሸራተን ዋና በር አንስቶ የፖስታ ቤት ጀርባን ተከትሎ በንግድ ማተሚያ አድርጎ እስከ አሮጌው ቄራ፣ እንዲሁም ፊት በር ዞሮ ፖሊስ ጋራዥ ጋር የሚገጥም ነው፡፡  ብዙዎቹ ወንጀሎች የሚፈጸሙት በአሮጌው ቄራ አቅጣጫ በተገነጣጠሉ አጥሮች በኩል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም ከሰሞኑ አጥሩን በድጋሚ የማደስ፣ የጥበቃ ማማን የመገንባት እንዲሁም በስፍራው የማኅበረሰብ አቀፍ ጊዝያዊ ፖሊስ ጣቢያ ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ በተመሳሳይ ሁኔታ ለችግረኛ ዜጎች ምግብ የሚያቀርቡ ሰፈሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ ኾኖም የአተት ወረርሽኝ በገባ ወቅት አካባቢዎቹ በጤና ቢሮ ሠራተኞች አማካኝነት እንዲዘጉ ተደርገው የቆዩ ቢኾንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድጋሚ መከፈት ጀምረዋል፡፡

የሸራተን ማስፋፊያ ሜዳም ለረዥም ጊዜ የተረፈ ምግብ ማደያ ኾኖ ቆይቷል፡፡ በስፍራው በርካታ የወንጀል ሪፖርቶች መብዛታቸውን ተከትሎ ከአንድ ወር ወዲህ ያደጉ ሳሮች፣ አረሞች፣ ሙጃዎች እና ቁጥቋጦዎች በመኪና አየታጨዱ ይገኛል፡፡ ኾኖም ምንም አይነት የግንባታ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡