The poetዋዜማ ራዲዮ- “የባለቅኔው ኑዛዜ” ሰሞኑን የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡ የአንድ ‹‹ተራ›› ገጣሚ ግርድፍ ግለታሪክ የሰፈረበት መጽሐፍ፡፡ ብዙ የጅዝብና (hippie) ሕይወት የኖረ፣ ትንሽ ኮስታራ ሕይወትን በስሱ ያጣጣመ የአንድ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ ቅንጭብ ታሪክ፡፡ ሰውየው በ1946 ወልዲያ ተወልዶ በ1996 ዓለም ገና ሕይወቱ አለፈች፡፡ ትንሽ ትንሽ የጋሽ ስብሐትን የሚመስል ሕይወት፣ ትንሽ ትንሽ የብአዴን ታጋዮችን የሚመስል ሕይወት፣ ብዙ ብዙ የጎዳና ሕይወት ኖሯል፡፡ ይህ ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ወይም አያ ሙሌ ይባላል፡፡

የአያ ሙሌ ነገር ግራ ነው! ሕይወቱም ሲበዛ ዥንጉርጉር ናት፡፡

ለምሳሌ ተራ ገጣሚ ነው እንዳንል እጅግ ተወዳጆቹ ሙዚቃዎች የርሱ አሻራ ያረፈባቸው ኾነው እናገኛለን፡፡ ብኩን ሰው ነው እንዳንል በኢህአፓ እሳት ፖለቲካ ዉስጥ ተወልዶ፣ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ነዶ፣ በብአዴን በስሎ፣ በNGO ደመወዝ ከብሮ፣ በኢህአዴግ ላዕላይ ቤት ገብቶ፣ በጋዜጠኝነት ሠርቶ፣ ከመንግሥት አፓርታማ ተበርክቶለት የሴኮ ቱሬ ጎረቤት ኾኖ የኖረ ሰው ነው፡፡

ደግሞ ያን ሰምተን ለአንቱታ ስናዘጋጀው ድንገት ሥራውን ጥሎ ይጠፋል፡፡ ዘበኛ፣ ኩሊ፣ ወዛደር፣ ጎዳና ተዳዳሪ ይሆናል፡፡  ብቻ ያያ ሙሌ ነገር ለወሬም አይመች፡፡

ያኔ ኢህአዴጎች እንደገቡ ሰሞን (ለነገሩ እጃቸውን ይዞ አዲሳባ ካስገቧቸው ሰዎች ዉስጥ አንዱ እሱ ራሱ ነው) አንድ የከበረ ወዳጁ ወደ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ክበብ ይዞት ይገባል፡፡ የአያ ሙሌን ቆሸሽ ማለት የተመለከተ ታጋይ ዋርዲያ  ‹‹አታ…ተመለስ!›› ሲል ሙሌን በቁጣ ያስቆመዋል፡፡ “አይ…ከኔ ጋር ነው ነው፣ ችግር የለም” ብሎ ወዳጁ ከለላ ሰጥቶ ያስገባዋል፡፡ ሙሌ ወደ ወስጥ ከመግባቱ በፊት ግን አንድ ነገር ከነከነው፤ ተመልሶ ወደ ታጋዩ ዋርዲያ ጆሮ ጠጋ ብሎ  ‹‹ትናንት በበረባሶ አርገህ ገብተህ ዛሬ በረባሶ ያረገ መናቅ ጀመርክ?›› ብሎት ገባ፣ በትግርኛ፡፡

ሙሌ ትግርኛ ብቻ ነው እንዴ ታዲያ አቀላጥፎ የሚናገር? ግዕዙስ፣ አፋርኛስ፣ ኦሮሚኛውስ፣ አረብኛና እንግሊዝኛወስ፣ ፈረንሳይኛውስ…በሁሉም ይቀኝባቸዋል፡፡ ትንሽ ልጅ እያለ እንደውም ‹‹ጋይድ›› ነበር፡፡ ሊስትሮም ነበር፡፡ ሊስትሮ እያለ የአንድ ደንበኛውን ካልሲ በቀለም ቡሩሽ አበላሽቶ እጅግ ጥብቅ ኩርኩም ቀምሷል፡፡ ያቺ ኩርኩም እስከዛሬም ታመኛለች ይል ነበር፣ በሕይወት ሳለ፡፡ ታዲያ ለመጀመርያ ጊዜ ኤን ጂ ኦ ተቀጥሮ ረብጣ ብር ያገኘ ለት በሲሶው ጠርሙስ ዉስኪ ገዝቶ ጫማ ይጠርግባት የነበረችው ቦታ ላይ ሄደና ዉስኪውን ሙሉ እዚያው አርከፈከፈው፡፡ ሙሌ በቀለኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በቀለኛ ቢኾን ግን ሐብታም ኾኖ መኖር ነበረበት እኮ!

ደግሞ ማርክሲስት ብለነው ልናልፍ ስንል መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ ባለ ደረጃ አጥንቷል፣ ከቤተክርሲያ ደጅ አይጠፋም፡፡ ዉሎ አዳሩም እዛው ነበር ይሉናል፣ የሚያውቁት፡፡ ታዲያ ቆራጥ ክርስቲያን ነበራ! ስንል ቁርዓንን 30 ጁዝ “ሀፍዟል* ይሉናል፡፡ እንዲያው ወሎ ዉስጥ ከቄሶችና ከሼካዎች እኩል ማውራት ይቻለዋል ብለው ይመሰክሩለታል፡፡ ብቻ የአያ ሙሌ ነገር ግራ ነው፡፡

በ1992 ለወጣው ፈርጥ መጽሔት ትንሽ ስለአስተዳደጉ ፍንጭ ሰጥቶ ነበር፣ ያን ዕለት ለጋዜጠኛ እንዲህ አለው…፡፡

“…ምን መሰለህ፣ እኔ ዲቃላ ነኝ፤ አባቴ ትግሬ ናቸው፤ እናቴ የዋድላ ደላንታ ሴት ናት፡፡ ወልዲያ ዉስጥ ሙጋድ የሚባል ቦታ እናቴ ከፊት ለፊት ጠላ ትሸጥ ነበር፡፡ አባቴ ደግሞ በጓሮ በኩል ጨው ይሸጣል፡፡ እናቴ ጠላውን እየሸጠች ታንጎራጉራለች፡፡ እንጉርጉሮዋ የኒህን ቄስ ቀልብ ጠለፈ፡፡ ቄሱ ሽማግሌ ቢልኩ አይሆንም ይባላሉ፡፡ እናቴና አባቴን የምታገናኝ አንዲት በር ነበረች፡፡ ቄሱ አይሆንም ሲባሉ በሯን ገንጥለው ገቡ፡፡ እኔ ተወለድኩ፡፡…”

ብጽአት ስዩም ‹‹አደራ ልጄን አደራ›› እያለች በእንባ የምታዜመውን ግጥም የጻፈላት ሙሌ ነው፡፡ ለአበበ ተካ ‹‹ወፊቱ››ን የጻፈለት ሙሌ ነው፡፡ ለሀና ሸንቁጤ፣ ለኩኩ ሰብስቤ እያልን ብንቀጥል ማቆምያ የለንም፡፡ ቆንጥሮ እየሰጠ አንበሽብሿቸዋል፤ ፍዝ ኾኖ አድምቋቸዋል፡፡ እነሱን የዝና ማማ ላይ ሰቅሎ እሱ እታች ወርዶ ይተኛል፡፡ ጎዳና፡፡

ሙሌ ድሮ ድሮ እንደ ኢህአፓም እንደ ብአዴን አድርጎት ነበር፡፡ ምን አድርጎት ነበር ብቻ! ቆራጥ ታጋይ ነበር እንጂ፡፡ በኢህአዴግ አምናለሁ ይል ነበር፣ አፍ አውጥቶ፡፡ ከተበላሹም አለቃቸውም እያለ ይዝት ነበር፡፡ እነ በረከት፣ እነ ታምራት ላይኔ፣ እነ ሕላዌ ዮሴፍ የሙሌ ግጥም ነፍሳቸው ነበር፡፡  ሙሌ የወልዲያ ልጅ ይሆን እነጂ አባቱ የትግራይ ሰው ናቸው፡፡ ለትግልና ለታጋዮች የቀረበውም ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የኢህዲን (ብአዴን) 20ኛ ዓመት ላይ ግጥም እንዲያቀርብ ተጋበዘ፡፡

ሙሌ ትልልቆቹ ብአዴኖች ባሉበት መድረክ ላይ ወጥቶ እንዲህ ተቀኘ…፣

ምንም ነኝ ግን አማራ

ለዚያውም ደሜ አረንጓዴ

የፈጠረኝን አምኜ፣ በጎቼን ከተኩላ ጋር የማሰማራ

ምንም ነኝ ግን አማራ

ኩራት እንጂ ሞት ያልፈራሁ

አማራ ነኝ መቃ አንገት፤ ራሴ ከብዶኝ የማልንገታገት

የሰው ጣባ ሥር የማልለገት፤

ማንም እንዳስመለከተው ያሻውን ስም ቢያወጣልኝ

እድሜ ላባይ ጣና ልጅ ያን ቀን የማስቆርሰው፣ ድፎ ዳቦ አያጣልኝ

ያው ወንድሞቼ ይመስክሩ

በናት ጡት ወተት ባይሰክሩ

የዛሬ ሃያ ዓመት ተክራርዋ ወርደውም ባልመከሩ

ምንም ነኝ ግን አማራ!

በዚህን ጊዜ ብአዴኖች አንገታቸውን ደፉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ይፈሩት ጀመር፡፡

አያ ሙሌ የከተማ ባህታዊ

በዚህ መጽሐፍ የተወሱ በርካታ ገጠመኞች ሙሉጌታ ተስፋዬን የሱፊ ፈላስፋ፣ የከተማ ባህታዊ አንዳንዴም ንግርት አዋቂ ያስመስሉታል፤ ሊኾንም ይችላል፡፡

አንድ ቀን ሙሌ አዲስ ጫማ ገዝቶ መንገድ ሲያቀና አንድ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ የኔ ቢጤ አይቶ ይጠራቸውና፣ “እስቲ ይሄን ይለኩት” ይላቸዋል፡፡ “የኔ ቢጤውም ልኬ ነው ይሆነኛል” ይሉታል፡፡ “በሉ ይሂዱ” ብሏቸው እርሱ በባዶ እግሩ መንገዱን ቀጠለ፡፡

አያ ሙሌ በየአድባሩ በየአገሩ በአብያተ ክርስቲያኑ ሁሉ እየዞረ እንደ ለማኞች ሆኖ ለምኖ የተሰጠውን መልሶ ለለማኞቹ ማደል ጀምሮ ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ የአለቃ ተስፋዬ ልጅ ሚካኤል ሲለምን ታዬ ተብሎ ተወራበት፡፡ እሱ ግን ግድ አልነበረውም፡፡ “እብዶች” አያ ሙሌን ካዩ አይለቁትም፡፡ ይከተሉታል፤ ይወዱታል፡፡ በተሻለ ያወሩታል፡፡ ለምሳሌ ወልዲያ አባ ግርሻ የሚባሉ አንድም ሰው የማይቀርባቸው በአእመሮ መታወክ የሚሰቃዩ ሰው ነበሩ፡፡ ሙሌ ግን ጠጅ ቤት ወስዶ አብሯቸው ዉሎ ያድር ነበር፡፡ በሰላም፡፡

አንድ ቀን ደግሞ አንድ እንጨት የተሸከሙ ሰውዬን በመንገድ ያገኝና ‹‹እስካሁን አልሸጡትም?›› ይላቸዋል፡፡ ሰውየውን ለካ ሌላ መንገድ ላይ ሲዳክሩ ቀደም ብሎ አይቷቸው ነበር፡፡ “ገዥ አጣሁ ልጄ” አሉት፡፡ “ስንት ነው?” ይላቸዋል፡፡ ሁለት ብር መኾኑን ሲነግሩት አምስት ብር ሰጥቶ “በሉ ይጣሉትና ሄደው ይረፉ” ብሎ አሰናበታቸው፡፡

አያ ሙሌ በደህናው ጊዜ በቤተመንግሥት በከፍተኛ የመንግሥት ስብሰባዎች መዝጊያ ላይ ሁሉ ግጥሞችን ያቀርብ ነበር፡፡ ቦረና ድረስ ሄዶ የዋለልኝ መኮንን ታዋቂ ዘጋቢ ፊልም ለመጀመርያ ጊዜ የሠራውም እሱ ነበር፡፡ መንግሥታዊ መጽሔትና ጋዜጣ ላይ ሂሳዊ ጽሑፎችን እያቀረበ የተደላደለ ኑሮ ሲኖር ቆየ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ድንገት ከኢህአዴግ ሰዎች ራቀ፡፡ ሽጉጡን አስረክቦ፣ መንግሥት የሰጠውን ቤት ጥሎ ጎዳና ወጣ፡፡ ላይመለስ፡፡

የኾነ ቀን ግን ወዳጆቹ ፈልገው አፈላልገው ደመወዙን ይዘውለት መጡ፡፡ ያልሠራሁበትን አልበላም ብሎ ሳይቀበል ቀረ፡፡ ሕይወቱንም በኬሻ በጠረባ አደረገ፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ የኾነ መልዕክተኛ ታምራት ላይኔ በጥብቅ እንደሚፈልገውና እርሱም ሊያደርሰው እንደመጣ ይነግረዋል፡፡ አያ ሙሌ አጭር መልስ ሰጠ ‹‹ አመሰግናለሁ፤ መንገዴን ለይቻለሁ!››

በሌላ ጊዜ ደግሞ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበረው በረከት ስምኦን አያ ሙሌ ያለበት ድረስ ደፍሮ በመምጣት በግል አናግሮት ነበር፡፡ ‹‹እንዲህ ለመሆን ነው ሥራህን የተውከው? በል ወደ ሥራህ ተመለስ፣ ቢያንስ ጥለኻት የመጣሃትን የ11 ዓመት ሕጻን ልጅህ አታሳዝንህም?›› ይለዋል፡፡ አያ ሙሌ ቱግ ብሎ ምላሽ ሰጠ፡፡ “የኔ ልጅ ሕጻን አይደለችም፣ አንተን በአንድ ዓመት ትበልጠሀለች፡፡”

የአያ ሙሌ ወዳጆችና የነፍስ ልጆች

በርከት ያሉ አድናቂዎችና የነፍስ ልጆች ነበሩት፡፡ ብዙዎቹ የጎዳና ልጆች ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የጥበብ ወዳጆች፡፡

ከአያ ሙሌ የጥበብ ወዳጆች አንዱ ጋሽ ስብሐት ነው፤ ሌላኛዋ ስንዱ አበበ ናት፡፡ ስንዱ የሙሌን ሁለት ልጆች  እሱ ጎዳና ከወጣ በኋላ በማሳደግ፣ በተባይ እየተበላ የሚሰቃየውን አያ ሙሌንም ቢኾን እንደነገሩ በመያዝ፣ አልፎ አልፎ ጎዳና ድረስ ሄዶ ምግብ በማቀበል ረድታዋለች፡፡ አራት ኪሎ ማለዳ ካፌ አካባቢ በሚገኘው አፓርታማዋ መጥቶ በር ላይ ቁጢጥ ይላል፣ ሲርበው፣ ሲጠማ፡፡ (በርግጥም ስንድን እጅግ ይወዳት ነበር ይባላል፣ ሙሌ፤ ስሟንም ጉኖ ዘበናይ ነበር የሚላት፡፡ ስንዱም አዋዋሏ ተጽእኖ አድርጎበት ይሆን እንጃ ብቻ አንዳንዴ እሷም እንደሙሌ ከመስመር ትወጣ ነበር ልበል?፣ እርሷም እኮ የምትታወቀው ከመስመር የወጡቱ ወዳጅ በመኾን ነው፡፡

ለምሳሌ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስትሰራ ድርጅቱ ከሰጣት የጥያቄ ዝርዝር አፈንግጣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን እንዲህ ጠየቀቻቸው፤

“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከርዕሰ ጉዳያችን ወጣ እንበልና ኢትዮጵያ በድርሰት እንድታብብ ያደረጉ እነ ሐዲስ አለማየሁ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ስብሀት ገብረእግዚያብሔር እና ሌሎችም ዛሬ አስታዋሽ አጥተዋልና ችላ ተብለው ክብራቸው በማይመጥን ሁኔታ እየኖሩ ነው፤ ለመሆኑ መንግሥት እነዚህን ሰዎች ከወደቁበት ለማንሳት ምን አቅዷል?”

መልስ የማያጡት የነበሩት ሰው መልስ መስጠት ጀመሩ፤

“እርግጥ ነው ያልሻቸውን ሰዎች እናውቃቸዋለን፣ በመጽሐፎቻቸው ተምረናል፡፡ እናደንቃቸዋለን፡፡ ከአንድ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር ለይተን ግን የምናደርግላቸው ምንም ነገር አይኖርም፤ አራት ነጥብ፡፡”

በማግስቱ መሥሪያ ቤቷ ስንዱ አበበን በሥነ ምግባር ጉድለት…ምናምን ብሎ አሰናበታት፡፡ የአያ ሙሌን የባለቅኔው ምህላን የግጥም ስብስብ ከየትም ከየትም ሰብስባ ያሳተመችው እሷ ናት፡፡ ሙሌ ጻፈው፣ ጥሎት ይሄዳል፤ ዞሮም አያየው፡፡ ዘፋኞች ግን ከሥር ከሥሩ የሚጥለውን እያነሱ ይከብራሉ፡፡

የከተማ ባሕታዊው አያ ሙሌ

አያ ሙሌ ድምጻዊ አበበ ተካ በገነነበት ወቅት የዘፋኙ ሥራ አስኪያጅ በመሆን በየክፍለ ሀገሩ ይዞር ነበር፡፡ ያን ሰሞን በርከት ያለ ገንዘብ ያገኘበት ጊዜ ነበር፡፡ እንዲያዉም አዲሱ ገበያ አንድ ግቢ ቤት የዓመት ኪራይ ከፍሎ ልጆቹን በሥርዓት ማሳደግ ጀምሮ ነበር፡፡ ያን ሰሞን ከአበበ ተካ ጋር ጎንደር በሄደበት አጋጣሚ በርከት ያሉ የተቸገሩ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ያያል፡፡ “ኑ ወዲህ” ብሎ አሰልፎ ብዙ ሺ ብር ሲያድል ፖሊስ ሁኔታው ጥርጣሬ ፈጥሮበት አያ ሙሌን ቁጥጥር ሥር ያውለዋል፡፡ አበበ ተካ ነው ሄዶ ያስፈታው፡፡ ብቻ ያያ ሙሌ ነገር ግራ ነው፡፡

ገጣሚ ሙሌጌታ ተስፋዬ እጅግ በከፋ ድህነት እንዳደገ ይነገራል፡፡ ቡና ቤት እየሠራች ስላሳደገችው እህቱ የጻፈውን ሐና ሸንቁጤ ዘፍነዋለች፡፡ ‹‹አደራ ልጄን አደራን›› ብጽአት ተጫውተዋለች፡፡ ለካንስ ከሕይወቱ እየጨለፈ ነው የሚያስለቅሳቸው፡፡

“እኔ በልጅነቴ በባዶ ሆዴ ነበር የተማርኩት፡፡ እናቴ ምሳ የምታቀርብለኝ ምግብ ከሌላት እኔን ላለማየት በሩን ቆልፋ ትጠፋ ነበር፡፡” ብሏል በአንድ ወቅት፡፡

የወላጅ እናቱ እናት የኾኑት አያቱ እናንዬ ቀን የለበሱትን ቀሚስ ማታ እንደ ብርድልብስ እያለበሱ ነበር ያሳደጉት፡፡ እናንዬን በጣም ይወዳቸዋል፡፡ እርሳቸው የሞቱ ቀን እንዳዘነው ያዘነበት ወቅት የለም፡፡ እናንዬ በገሀድ የማይታይ ነገር ይታያቸው ነበር ይባላል፤ የጅብ ቋንቋም ይረዱ ነበር፡፡ ጅብ ሲጮኸ አይ እከሌ ሊሞት ነው ብለው ይናገራሉ፤ ያሉት ሲኾን በገሀድ ይታይ ነበር፡፡ ታዲያ እንደ አናንዬ ሁሉ አያ ሙሌም አልፎ አልፎ ነገሮች ይገለጡለት ነበር ይላል ግለታሪኩን የጻፈው ፋሲካ ከበደ፡፡ የሚገርመው አያ ሙሌና የአሁኑ ቢሊየነር ሼክ አላሙዲ ወልዲያ ዉስጥ ጎረቤታሞች ነበሩ፡፡

ለምሳሌ አንድ ቀን አለም ገና አካባቢ የመነኮሳትን ቀሚስ የለበሱ አንዲት ሴትዮ አተኩሮ ካያቸው በኋላ “ወይ እማማ! በገመድ ታንቀው ሊሞቱ ነው ማለት ነው?” ብሏቸው ሲያልፍ አብሮት የነበረው ወዳጁ ‹‹ምነካህ ሙሌ፣ ጎረቤት ናቸው እኮ…›› ይለዋል፡፡ ከጊዜ በኋላ ሴትየዋ ሞቱ፤ በገመድ ታንቀው፡፡

በአንድ ወቅት ደግሞ ሃያ ሁለት አካባቢ በሚያዘወትርበት ቤት አንድ ሳቅና ጨዋታ የሚያበዛን ልጅ ‹‹ልትሰበር ነው›› አለው፡፡ ሌላ ቀንም እንዲሁ ፌዝ ሲያበዛ  ‹‹ወንዝ ሊወስድህ ነው›› አለው፡፡ ልጁ ከጊዜ በኋላ ክፍለ ሀገር በሄደበት መሞቱ ተሰማ፡፡ ሲጣራ ደራሽ ወንዝ ወሰደው ተባለ፡፡፡

በሌላ ቀን ደግሞ አያ ሙሌ ጓደኛውን በሌሊት ቀስቅሶ ተነስና ፍቅረኛህን ከቤቷ ጠርተህ ይዘሀት ና ይለዋል፡፡ አሻፈረኝ ይላል፡፡ ሙሌ ጎተጎተው፡፡ በዚህ ዉድቅት ሌሊት ፍቅረኛውን ማስጠራት የከበደው የሙሌ ወዳጁ እስኪነጋ ዎክ ማድረግ ይጀምራል፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ዎክ አድርጎ ሲመለስ ልጅቱ ከአንድ ወንድ ጋር ከሆቴል ስትወጣ አገኛት፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ አሜሪካን ግቢ ከመንፈስ ልጁ ጋር በችግር ጎዳና ላይ ሳለ ሙሌ ድንገት ከጎዳናው እምር ብሎ ተነስቶ አንድ ሙስሊም ሰውዬን በአረብኛ ያናግራቸውና ተመልሶ ጎዳናው ላይ ቁጭ ይላል፡፡ ሰውየው ቆየት ብለው የታሰረ ረብጣ ብር በሾፌራቸው ይልኩለታል፡፡ ሙሌም ‹‹መልስላቸው፣ እኔ ለማኝ አይደለሁም ›› ሲል ብሩን ሳይቀበል ቀርቷል፡፡

በሌላ ወቅት ደግሞ አንዲት ተከታዩ የነበረች ልጅ ቤት ድንገት ይሄድና ‹‹ነፍስሽ ጠርታኝ ነው የመጣሁት፤ እንዴት እንደዚህ አይነት ቆሻሻ ሀሳብ ታስቢያለሽ? አትውሸክሸኪ፡፡” በማለት ከገሰጻት በኋላ ‹‹ማር ይስሀቅ›› የሚባል መጽሐፍ እንድታነብ አዟት ነበር፡፡ የሚገርመው ታዲያ ልጅቷ የምትኖርበትን አድራሻም ኾነ ራሷን የማጥፋት ሐሳብ እንደነበራት ትንፍሽ ብላለት አታውቅም ነበር፡፡

አያ ሙሌና ድርቅ

እጅግ በአስቸጋሪ ድህነት ዉስጥ ያደገው ሙሌ እጅግ አሳዛኝ የረሀብ ክስተቶችን ተመልክቷል፡፡ በድርቁ ጊዜ በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ የጃፓን ተራድኦ ድርጅት ዉስጥ ይሠራ ነበር፡፡ ለያውም ዳጎስ ያለ ገንዘብ እየተከፈለው፡፡ በአንድ ዕለት ከመቅጽበት ሥራውን ጥሎ ጠፋ፡፡ ለምን እንደጠፋ ለረዥም ዓመታት ለማንም ትንፍሽ ብሎ አያውቅም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ለወዳጁ ዳዊት ከበደ ወይሳ ነገረው፡፡ ለጽሑፍ ስለማይመች እዚህ ጋር አላካተትኩትም፡፡ ሙሌ ያን የሕጻናት ረሀብ ከተመለከተ በኋላ ጠፋ ጠፋ፡፡ ከዚያ በኋላ ዘለግ ላለ ጊዜ አየሁት የሚል ሰው አልነበረም፡፡ በየ10 ዓመቱ ከጎበኙን ድርቆች ዉስጥ የ67፣ የ77፣ የ87 በይበልጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በድርቅ ላይ ከተጻፉ ጽሑፎች ደግሞ በብዙዎች ሕሊና የቀረችው የሙሌ ቅኔ ናት፡፡ እውነት ከመንበርህ የለህማ! የምትለው፡፡

ምነዋ መንግሥተ ሰማይ የምህረትሽ ቀን ራቀ

ምነው ትንግርትሽ ረቀቀ

ምነው ኪዳንሽ ታጠፈ መዝሽ ወዘናሽ ነጠፈ

እንደ ደጎሳ ድፍድፍ ላቦትሽ ተንጠፈጠፈ

አሳርሽ ጠሎ አሰፈፈ

እያለ የሚቀጥለው ይህች ድንቅ ሥራው አስራ ምናምን ገጽ አንዲት ሳይደናቀፉ በቃል የሚወጧት ቅኔ ናት፡፡ ምናልባት የሙሉጌታ ተስፋዬ Masterpiece ልንላት እንችል ይሆናል፡፡

አያ ሙሌና ዘፋኞች!

ሙሌ የተመጠነ ጨዋታና ቀልድም ያውቃል፡፡

አንድ ቀን ተፈራ ነጋሽ አያ ሙሌን ይዞት ሆቴል ከበድ ያለ ምሳ ካበላው በኋላ ‹‹ባክህ እስቲ ስለ ድህነት ቆንጆ ግጥም ሥራልኝ ይለዋል፡፡ ‹‹ተፌ ስለድህነት ከሆነ ያን ሁሉ ምግብ ከመጋበዝህ በፊት አትነግረኝም ነበር?›› ብሎት ነበር፡፡

አያ ሙሌ ድምጻዊ አበበ ተካን ‹‹በምሰራልህ ሥራ የቃል ኪዳን ሚስትህን ከአሜሪካ ካላመጣኋትማ ምኑን ባለቅኔ ሆንኩት ብሎት ነበር፡፡ ካሴቱ ከወጣ በኋላ ደግሞ አበበ ተካ ‹‹እሙ ነይ እሞ እሞ ነይ›› ስዘፍን ስሜት ዉስጥ ስለምገባ አለቅሳለሁ ቢለው ሙሌ ቀበል አርጎ ‹‹አይ አቤ! ደሞ አንተ ምን ታለቅሳለህ፡፡ እኔ ነኝ እንጂ የማስለቅስህ” ብሎት ነበር፡፡ እሞ ነይን ለቅድስት ድንግል ማርያም ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጸበት ሥራው እንደሆነ ይነገራል፡፡

አያ ሙሌ ያቺን ሰዓት

አያ ሙሌ የፈጠራቸው በይበልጥ በኢህአፓ ዘመን ይጽፋቸው ከነበሩ ጽሑፎቹ የተወሰዱና አሁን ጥቅስ መኾን የቻሉ አባባሎች አሉት፡፡ በወቅቱ እሱ ካገነናቸው አባባሎቸ ዉስጥ ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ሰው የጠፋ ዕለት የምትለዋ ትታወሳለች፡፡ አያ ሙሌ ግን ሰው የሚኾንለት ሰው አልነበረውም፡፡

ለበርካታ ጊዜያት በየገዳማቱ ይጠፋ ነበር፡፡ በእንጦጦ ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት ጾም ጸሎት ያዘውትር ነበር፡፡ ለተወነሱ ቀኖች በተመስጦ ያለምግብ ያሳልፍ ነበር፡፡ አንድ ወቅት ቤት ሲገባ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ እጅግ ከመራቡ የተነሳ ያገኘውን በርበሬ በዉሀ በጥብጦ በመጠጣቱ ለሰዓታት ራሱን ስቶ ነበር፡፡ ከነቃ በኋላም…ከሰው ፊት ይህ በርበሬ ይሻላል ብሎ ተናገረ፡፡

አንድ ቀን ደግሞ የዘፈን ግጥም ክፍያ 20ሺ ብር ተቀብሎ በሚያዘግምበት ሰአት “አንተ፣፣አንተን እኮ ነው ና ተሸከም…!” በማለት አንድ ሰው ቢጠራው “ወንደሜ ሆይ! በፍቅር አጠራር ብትረጠራኝ ኖሩ በነጻ እሸከምልክ አልነበር” ብሎት መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ሰውየው ተበሳጨ፣ “ከምትለምን ሰርተህ አትበላም? ለማኝ” ሲልም ሰደበው፡፡

አያ ሙሌ ከአፍቅሮተ ነዋይ የራቀ የከተማ መናኝ ነበር፡፡ መታወቂያ፣ ስልክ፣ እድር፣ የመኖርያ ቤትም ሆነ ቋሚ አድራሻ አልነበረውም፡፡ ወገን ዘመድ የሚለው ሰውም እንዲሁ፡፡ የሚኖረውም በእምነት ነው ‹‹እንደ ወፊቱ ልዋል›› ይል ነበር፣ አዘውትሮ፡፡ ከሥራዎቹ ሁሉ የአበበ ተካን ወፊቱን አብልጦ የሚወደው ለዚሁ ይሆን?

አያ ሙሌ ድንገት አምርሮ የሚያለቅስባቸው ጊዜያትም ነበሩ፡፡ በግንቦት ወር 1996 አሁን ማረፍ ነው የምፈልግው ብሎ ቤት ተከራየ፡፡ ወይዘሮ ከበቡሽን ሲሰናበትም…”ነገርኩሽ አልሰማሽም፣ ልሄድ ነው አልረሳሽም” ብሏቸው ነበር፡፡ የፒያሳን አቀበት እየወጣ ቴድሮስ አደባባይ ሲደርስ ድንገት ሐሳቡን ቀይሮ ወደ ጎላ ሚካኤል ዞሮ አማትቦ ዘለግ ላለ ሰዓት ፀለየ፡፡ ሦስት ቁጥር አውቶብስ ይዞ ዓለምገና ሄደ፡፡ አንድ ሆቴል ዉስጥ 13 ቁጥር መኝታ ይዞ አደረ፡፡ ጓደኞቹ ግማሽ በድን ኾኖ ከሆቴሌ ሲያወጡት የሆቴሉ ዘበኛ እንዲህ ተናገሩ፡፡

“ኸረ ይሄ ሰው ነብይ ሳይሆን አይቀርም፡፡እንዲችው ሌሊቱን ሙሉ ለጆሮ የሚከብዱ ነገሮችን ሲናገር ነው ያነጋው”

በነገታው ነሐሴ 28፣ ቀን 1996 ዓ.ም አረፈ፡፡