Photo-FILE
Photo-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በአያት ፀበል ኮንዶሚንየም አቅራቢያ የሚገኘውን ሰፊ ገላጣ መሬት የአዲስ አበባ መስተዳደር በሊዝ ለባለሀብቶች ካስተላለፈ በኋላ ላለፉት አስራ ሁለት ወራት ባለሀብቶች ቦታውን መረከብ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መሬቱን ለዓመታት ሲያርሱ የኖሩት ገበሬዎች መሬታችንን አናስነካም በማለታቸው ነው፡፡

በ15ኛ ዙር የሊዝ ጨረታ ተሸንሽነው ለባለሀብቶች የቀረቡት መሬቶች ብዛት ከአንድ መቶ ሀምሳ በላይ ሲሆኑ አሁን ችግሩ የተፈጠረበት አካባቢ የሚገኙት ቦታዎች በቁጥር 42 ብቻ ናቸው፡፡ ድምር ስፋታቸውም ከ15 ሄክታር አይበልጥም፡፡ በአካባቢው ለረዥም አመታት በግብርና የሚተዳደሩ የኦሮሞ ተወላጅ ገበሬዎች ሰፍረውበት በእርሻ ስራ ሲተዳደሩበት የነበረ ሲሆን በልማት ሳቢያ ቀስ በቀስ ወደ ዳር ሲገፉ ቆይተው አሁን የከተማዋ ጫፍ ወደሆነው አያት ፀበል ደርሰዋል፡፡ አሁን የቀረቻቸውን ባዶ ቦታ አስረክቡ ሲባሉ ነው ከሰሙኑ በእምቢታቸው ፀንተው ፍጥጫ ዉስጥ የገቡት፡፡

አሁን አለመግባባቶች እያንዣበቡበት የሚገኘው የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አካባቢ ትልቁ የ40-60 ፕሮጀክት እየተገነባበት ያለበት ሥፍራ ነው፡፡ ከዚህ ስፍራ በቅርብ ርቀት ስፖርት ፌዴሬሽን ወደፊት ሊያስገነባ ያቀደው ስታዲየም ማሰሪያ ቦታ እንዲሁም የመቄዶኒያ የአእምሮ ሕሙማን መርጃ የወደፊት ማዕከል ይገኛል፡፡ ከዚህ ዉጭ ቦታው የሚታረስ ገላጣ መሬት ሆኖ የቆየ ነው፡፡

በ15ኛው ዙር የመሬት ጨረታ አሸናፊዎች ቦታውን ለማልማት ዉል ሲገቡ ከአራት እስከ ዘጠኝ ፎቅ ግንባታ ለማካሄድና ግንባታቸውንም በ3 ዓመታት ዉስጥ ለማጠናቀቅ ነበር የተፈራረሙት፡፡

በሊዝ አሰራር ደንብ የጨረታው አሸናፊዎች ስማቸው በአዲስ ልሳን በተገለፀ በ10 ቀናት ዉስጥ ቀርበው የአሸነፉበትን ዋጋ 10 ወይም 20 በመቶ በሲፒኦ ገቢ ካደረጉ በኋላ ከሊዝ ጽህፈት ቤት ጋር የግንባታ መጀመርያና ማጠናቀቂያ ዉል እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡ መስተዳደሩ መሬቶቹ ወደሚገኙበት ክፍለከተሞች ሸኚ ደብዳቤ በመጻፍ ቦታዎቹን ባለሞያዎች ሸንሽነው ለባለሀብቶች እንዲያስረክቡ ያዛል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ዉስጥ ሲሆን አሁን የግጭት ስጋት በሆነበት የወረዳ 10 አካባቢ ግን  ሂደቱ 12 ወራትን ፈጅቷል፡፡

ከትናንት በስቲያ በስፍራው ተገኝተው የነበሩ የዋዜማ ምንጮች እንደገለጹት በክፍለከተማው የመሬት ሽንሻኖ ባለሞያዎች በደንብ አስከባሪዎች ታጅበው የልኬት ስራ በመስራት ቦታውን ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡ ባለሞያዎቹ ችካል ተክለው ከተንቀሳቀሱ በኋላ ባለሀብቶች ቦታው እንደደረሱ ገበሬዎች ችካሎቹን በሙሉ በመነቃቀል ጥለዋቸዋል፡፡

ይዞታቸውን አጥሮ ለማስከበር በትናንትናው ዕለት ከስፍራው የተገኙ ባለሀብቶች ችካላቸውን ለማግኘት ስላልቻሉ ለወረዳው አቤቱታ ቢያቀርቡም ወረዳው ነገሩ በጥንቃቄ መያዝ ስላለበት እንዲታገሱ ነግሯቸዋል፡፡ ገበሬዎቹ ትናንት ከሰዓት ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ይበልጥ ተቃውሟቸውን ለመግለጥ በሚመስል ሁኔታ በሬዎቻቸውን ጠምደው አካባቢውን ማረስ ጀምረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ለዋዜማ ዘጋቢዎች አስተያየት የሰጡ አንድ አልሚ እንደተናገሩት ቦታው እንዲህ አይነት የይገባኛል ጥያቄ ያለበት መሆኑን አስቀድመው ቢያውቁ ኖሮ እንደማይወዳደሩ ተናግረዋል፡፡

የወረዳው ኃላፊዎች በበኩላቸው ነገሮች ተካረው ወዳልተፈለገ ግጭት እንዳያመሩ ከሚል ስጋት ሁኔታውን በጥንቃቄ ለመያዝ እየሞከሩ ይመስላል፡፡ በኦሮሚያ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ የአዲስ አበባ አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች መጠነኛ ስጋት ያጋጠማቸው ሲሆን በተለይ በፉሪና በሱሉልታ የሚገኙ ዘናጭ ቤቶች የዋጋ ተመናቸው በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል፡፡ ወትሮ እስከ 12 ሚሊየን ብር ያወጡ የነበሩ መኖርያ ቤቶች ከአመጹ ወዲህ በ8 ሚሊየን ብር ገዢ ማጣታቸው አስገራሚ ሆኗል፡፡ የስጋቱ ምንጭ ደግሞ ቤቶቹ የተሰሩት ገበሬዎችን በማፈናቀል ስለነበረና አካባቢውን የበቀል እርምጃ ያሰጋዋል በሚል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አመጽ በማንኛውም ጊዜ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ፍርሃት የገባቸው ባለሀብቶች ችግር ይፈጠርባቸዋል በሚባሉ አካባቢዎች መሬትና ቤት ከመግዛት መቆጠባቸው ነው የዋጋ መዉረድ ያስከተለው፡፡

በተያያዘ ዜና በወረዳ 10 አያት ፀበል አካባቢው የሚገኙ ገበሬዎች ርስታችንን አንለቅም ብለው እያረሱት የሚገኙት ቦታ ለገበሬዎቹ ተገቢው የካሳ ክፍያ መከፈሉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ እንደነዚህ ምንጮች ገለጻ ለነዚህ ገበሬዎች የካሳ ክፍያ የተፈጸመው ባልተለመደ ሁኔታ አንድ ጊዜ ብቻም ሳይሆን ሁለት ጊዜ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ካቢኔው ለገበሬዎቹ የጠየቁት እንዲከፈላቸው በማዘዙ ነው፡፡ ለገበሬዎቹ የመጀመርያው ካሳ የተከፈላቸው ከ አምስት  አመታት በፊት ቢሆንም ቦታው ለልሚዎች ሳይተላለፍ በመቆየቱ በድጋሚ የግብርና ሥራ ሲሰሩበት ኖረዋል፡፡ የካሳ ክፍያው በጊዜ መራዘም የተነሳ እንዳልተከፈለ ተቆጥሮ በድጋሚ እንዲከፈላቸው የተወሰነው ምናልባትም ነገሩ እንዳይካረር ከመሻት እንደሆነ ምንጮቹ ይናገራሉ፡፡

ዛሬ ጧት የዋዜማ ምንጮች ቦታውን የጎበኙ ሲሆን አካባቢው ሙሉ በሙሉ በገበሬዎቹ መታረሱን፣ ምንም አይነት የፀጥታ ኃይል በስፍራው አለመኖሩን ለመመልከት ችለዋል፡፡ መንግሥት አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ገበሬዎቹን በኃይል ከመሬታቸው ያስለቅቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳደር በቅርቡ በከተማዋ ዳርቻ ከሚገኙ ገበሬዎች ጋር ባደረገው ዉይይት ከመሬታቸው የሚፈናቀሉ ገበሬዎች ለካሬ የሚሰጠው የካሳ ክፍያ በቂ እንዳልሆነ እንደሚረዳ ገልጾ፣ ገበሬዎች ካሳ ካገኙ በኋላ ኑሯቸውን ሊደጉም የሚችል ፕሮጀክት እያዘጋጀ መሆኑን፣ በልማቱም ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ በዉይይቱ የተገኙ አንድ ገበሬ ‹‹እኛ እኮ ዶሮ አይደለንም፣ 24 ብር ምን እንድናደርግበት ነው የምትሰጡን?›› ብለው ምሬታቸውን እንደገለፁ ሸገር ሬዲዮ ከሳምንታት በፊት ዘግቧል፡፡