Abiy Ahmed, Photo AFP
Abiy Ahmed, Photo AFP

ዋዜማ ራዲዮ- የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ ካቢኔ ሹም ሽር ከድሮው ከጅምሩም በተለየ መነጽር እንዲታይ ያስገደዱት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ባንድ በኩል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የቀውስ ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር ናቸው፡፡ የተረከቧት ሀገር እና መንግስት ብሎም ገዥው ድርጅት ከገቡበት ቀውስ እንዲወጡ ያዋቀሩት ካቢኔ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚም ለቀውሱ ራሱን ዋነኛ ተጠያቂ ስላደረገ ከዚህ ቢያንስ ፖለቲካዊ ይዘት ለሌላቸው መስሪያ ቤቶች ሙያተኞችን በብቃታቸው ብቻ ሹመው ከፊል ሙያተኛ ወይም ቴክኖክራቲክ ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ መጠበቁ ግድ ነበር፡፡

በሌላ በኩል የካቢኔ ሹም ሽሩ የመጀመሪያ ፈተናቸው ወይም (litmus test) በመሆኑ አመራራቸው ምን ሊመስል እንደሚችል ግልጽ አቅጣጫ እንደሚያሳዩበት የተጠበቁበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ካቢኔው ሁለንተናዊ ቀውሱን ሊፈታ እንደሚችል እና ሀገሪቱም ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንድትጀምር በር ከፋች እንደሚሆን ተስፋ የተጣለው ለዚህ ነበር፡፡ [በጉዳዩ ላይ የተዘጋጀ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

ካቢኔው ግን የፖለቲካ ሹመኞች ስብስብ ነው የሆነው፡፡ ያውም ደሞ ከክልል ቢሮዎች ተዛውረው የተሾሙት 10 ያህሉ አዳዲሶቹ ሹሞች ባብዛኛው ከአባል ድርጅቶችና ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተውጣጡ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ አንድም የፓርቲው አባል ያልሆነ ሹም አለማካተቱ ይህነኑ ነው ያረጋገጠው፡፡

ውክልናና የፓርቲ ታማኝነት

ብዙውን ጊዜ የሚንስትሮች ሹመት ለምን በፖለቲካ መመዘኛ ይሆናል? የሚል ጥያቄ ሲነሳ በተደጋጋሚ የሚሰጠው መልስ ሚንስትሮች የፖለቲካ ሹሞች መሆናቸው የገዥውን ግንባር ፖሊሲዎች ጠንቅቀው አውቀው አጠቃላይ አቅጣጫ እንዲሰጡ እንጅ ዋናውን ሥራ የሚሰሩትማ ሚንስትር ደዔታዎችና ከዚያ በታች ያሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ናቸው የሚል ነው፡፡ ይሄ ሙግት ግን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እንደማያስኬድ በተደጋጋሚ ታይቷል ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የመንግስት እና ፓርቲው መዋቅር ስለተቀላቀለ እንኳን በስልጣን ላይ ያሉት ፖለቲከኞች በፓርቲው መዋቅር ብቻ የተወሰኑትም በቦርድ አመራርነት ሰበብ በፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እንደሆኑ የታወቃል፡፡

እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲሶቹን ሹሞቻቸውን ሲሾሙ ቀደም ሲል በነበሩበት ሥልጣን ምን የተለየ ስኬት እንዳስመዘገቡ በዝርዝር አላሳወቁም፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ሥራ አስፈጻሚውን አካል መሞገት ጀምሮ የነበረው ፓርላማ ሹም ሽሩን ያለ በቂ ክርክር በሙሉ ማጽደቁ ጨርሶ ሀገሪቱና መንግሥት ካሉበት አጣብቂኝ አንጻር የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ፓርላማው ያሳየው መንፈስ በጣም ቀዝቃዛ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

አሁን ዋናው ጥያቄ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የፖለቲካ ሹመትን ለምን መረጡ? የሚለው ነው፡፡ አንዱ ምክንያታቸው በአባል ፓርቲዎች መካከል የታየው የሥልጣን ሽኩቻን ለማስታገስ ተፈልጎ የተረገ እንደሆነ መገመት ይችላል፡፡ በአባል ድርጅቶች መካከል አለመተማመን መስፈኑን ራሱ ኢሕአዴግ ያመነ መሆኑ እና በመካከላቸውም የሥልጣን ሽኩቻ መኖሩ በስፋት ሲዘገብ መኖሩ ይህንኑ ግምት ለእውነታ የቀረበ ያደርገዋል፡፡

ከሥልጣን ድልድሉ ከድርጅት አንጻር ጎልተው የወጡት ኦሕዴድ እና ሕወሃት ብቻ ናቸው፡፡ ኦሕዴድ ቁልፍ ሥልጣኖችን በመያዙ፣ ሕወሃት ደሞ ነባር ቢያንስ ከመጋረጃው ጀርባ ዘዋሪነቱን አስጠብቆ መቀጠሉ… በተለይ ኦሕዴድ ቀድሞውኑም “የፌደራል ሥልጣን ይዤ በሀገሪቱ ሁነኛ ሚና መጫወት እፈልጋለሁ፤ ይገባኛልም” በማለት በገዥው ግንባር ውስጣዊ ባህል ባልተለመደ አኳኋን አቋሙን ያንጸባረቀ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን እንደተመኘው ጠቅላይ ሚንስትርነቱን፣ የሀገር መከላከያ ሚንስቴርን፣ አቃቤ ሕግን፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ብሄራዊ ደኅንነት አማካሪነትን፣ ጉምሩክ እና ሀገር ውስጥ ገቢን ብሎም ኢነርጂን መቆጣጠር ችሏል፡፡

ሕወሃት ደኅንነቱን እና ፋይናንስን ይዟል፡፡ በድርጅት በኩል ደሞ የግንባሩን ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የሕወሃት ምክትል ሊቀመንበር በሆኑት በወይዘሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚያብሄር በኩል ተቆጣጥሯል፡፡ ይህን ስልጣኑም የግንባሩ ሊቀመንበር እና ጠቅላይ ሚንስትሩን ስልጣን ለማመዛዘን ሊጠቀምበት ይችላል፡፡

አማራ ክልል አንደኛው የሕዝባዊ አመጽ ማዕከል እና በህዝብ ብዛትም ሁለተኛ ቢሆንም ብአዴን ግን በድልድሉ የረባ ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ እዚህ ላይ በብሄር ፌደራላዊ ሥርዓት ለምትመራ ሀገር አንድን ብሄር ለሚወክለው ኦሕዴድ ቁልፍ ሥልጣኖችን ጠቅልሎ መስጠት በተግባር አደገኛ አይሆንም ወይ? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ የሚገባው ነው፡፡

የኦሕዴድና ህወሀት ሚዛን ጥበቃ

አጠቃላይ የሥልጣን ድልድሉ በኦሕዴድ እና ሕወሃት መካከል በተደረገ ድርድር የተሰራ ቀመር ነው የሚመስለው፡፡ ምክንያቱም ከሁለት ትላልቅ ክልሎች ተቃውሞ ስለበረታበት ኦሕዴድን በስልጣን በማንበሽበሽ፣ ብአዴንን በከፊል ለማግለል መፈለጉ የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህም ብአዴን እና ኦሕዴድ በድርጅትም ሆነ በሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ ቅርርቦሽ ለመፍጠር ባሳዩት መነቃቃት ላይ ውሃ ለመቸለስ ይመቸዋል፡፡ የራሱን ሰዎች ወደ ፊት ማምጣት አለመፈለጉም በከፊል ይህንኑ ነው የሚጠቁመን፡፡ በርግጥ ኦሕዴድም የኦሮማራ ትርክትን እና የብአዴኑ ዕጩ ደመቀ መኮንን ከጠቅላይ ሚንስትርነቱ ውድድር ራሳቸውን በማግለል ዋሉለት የተባለውን ውለታ ወደ ጎን የመግፋቱ ነገር በፖለቲካ ስሌት አንጻር ሊያየው ይችላል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ደሞ እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ሁሉ ላለፉት ሦስት ዐመታት ሲያነሳቸው ከነበሩት አንኳር ቅሬታዎች መካከል ደሞ በፌደራላዊ ሥርዓቱ ፍትሃዊ የፖለቲካ ሥልጣንና ሃብት ክፍፍል ተጠቃሚ መሆን እና ፍትሃዊ ልማት ማግኘት ይገኙበታል፡፡ ድልድሉ ከአማራ ክልል አንጻር ብቻ ሳይሆን ደቡብ እና ሌሎች ታዳጊ ክልሎች ሊኖራቸው ከሚገባው ድርሻ አንጻር ነው መመዘን ያለበት፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግር ብሄራዊ አንድነትን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆናቸውን ደጋግመው ጠቅሰው ነበር፡፡ ለብሄራዊ አንድነትን ፈር ቀዳጅ ሊሆኑ ከሚችሉት ሁነኛ ተግባራዊ ማስተካከያዎች መካከል ደሞ ፍትሃዊ የፖለቲካ ሥልጣን ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፓርላማው ባጸደቀላቸው ድልድል ግን ብሄራዊ አንድነትን እንደምን ሊያሳኩት እንደሚችሉ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ-መራሹ መንግሥት ከሁለት ዐመት ወዲህ ጀምሮ የፌደራል የፖለቲካ ሹመት እና በሲቪል ሰርቪሱ የሚደረገው ቅጥር ባጠቃላይ በዘፈቀደ መሆኑ ቀርቶ በብሄር ተዋጽዖ ቀመር እንዲሰራ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ እንዳለም መረሳት የለበትም፡፡

በርግጥ የሥልጣን ድልድሉን እንደወረደ የሚወስዱ አንዳንድ ወገኖች የፖለቲካ ሥልጣኑ ቁልፍ ከሕወሃት ወደ ኦሕዴድ እንደተሸጋገረ ያስቡ ይሆናል፡፡ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ዲፕሎማቶችም በዚህ መልኩ የተረዱትን ወደ መንገስቶቻቸው ሪፖርት እንዳደረጉ ዋዜማ መረጃ አላት፡፡

በተጨባጭ ያለው ሃቅ ግን እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዋናው የሥልጣኑ ዘዋሪ ሕወሃት ሆኖ መቀጠሉ ነው፡፡ በርግጥ ያ ማለት ሌሎች አባል ድርጅቶች የሚደለደልላቸውን የፌደራል ስልጣን በዋዛ ይመለከቱታል ማለት አይደለም፡፡ ድርጅቶቹ ይቅርና በድርጅቶች የተማረረው፣ ሆኖም ግን የሥልጣን ድልድሉ መስፈርት የብሄር ማንነት መሆኑን ስለሚያውቅ በድልድሉ ቅር ሊሰኝ ይችላል፡፡

አባል ድርጅቶች ተሿሚዎቻቸውን ያቀርባሉ

ሌላው ጠቅላይ ሚንስትሩ የፖለቲካ ሹመትን ባይፈልጉት እንኳ አሁን በብዛት የተጠቀሙት ኢሕአዴግ ዛሬም የአፈጻጸም አቅም ማነስ እንጅ የፖሊሲና የመስመር ችግር የለብኝም የሚለውን ትርክቱን ባለመቀየሩ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢሕአዴግ የምልመላ እና ምደባ መርህም ስላልተለወጠ ጭምር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ተሹዋሚዎቹ በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት ይሾሙ እንጅ አሰራሩ ግን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ለአባል ድርጅቶች በሚሰጠው ኮታ እና አባል ድርጅቶችም በሚያቀርቡት የዕጩ ተሸዋሚ ዝርዝር መሠረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይህ ሁሉ የሆነው እንግዲህ ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ የካቢኔ ሹምት ከዚህ በኋላ በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ሳይሆን በብቃት ብቻ እንዲሆን ቃል በገባ እና ጠቅላይ ሚንስትር አብይም ይህንኑ እንደሚከተሉ በበዓለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግር ፍንጭ በሰጡ ማግስት ነው፡፡ ባጭሩ ድልድሉ ኢሕአዴግ ከራሱ አመራሮች ውጭ ሌሎች ዜጎችን በብቃታቸው እና ሙያቸው መሠረት ወደ ራሱ አቅርቦ ለማሰራት ፈጽሞ ፍላጎት እንደሌለውና ዝግጁም እንዳልሆነ በግልጽ ያሳየበት ድልድል ነው ማለት ይቻላል፡፡

ዋናው የሕዝቡ ሥር የሰደዱ ችግሮች እና ቅሬታዎች የተከማቹት በክልሎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ እናም የፌደራል መንግሥት ሚንስትሮች የክልሎች ሕዝቦችን ችግሮች በዋናነት ሊቀርፉ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ሥራ ላይ ያለውን ፖሊሲ ለማስፈጸም ሁነኛ መዋቅራዊ ለውጥ እና ብቁ አስፈጻሚ የሰው ሃይል መደልደል ያለባቸው ራሳቸው የክልል መንግሥታት ናቸው፡፡ ችግሩ ኢሕአዴግ የሚመራው ፌደራል መንግስት ፈር ሳይቀድላቸው ክልሎች በተናጥል እንዲህ ዐይነቱን ሁነኛ የለውጥ አቅጣጫ መከተል ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ደሞ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ ሹመት ቀደም ብሎ የኦሕዴድ እና ብአዴን ሥራ አስፈጻሚዎች ለመጨረሻ ጊዜ ያወጧቸውን መግለጫዎች ብናይ ድርጅቶቹ ቢፈልጉ እንኳ ይህን ማድረግ እንደማይችሉ ግልጽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በሌላ በከል ደሞ በአዲሱ ድልድል እንደተለመደው ፌደራል መንግሥቱ የክልሎችን ሰው ሃይል ራሱ የመሰብሰብ አካሄድ መከተሉ ክልሎችን እንደሚጎዳቸው መረሳት የለበትም፡፡ ከፌደራል ወደ ክልል አንድ ወይም ሁለት ባለስልጣናትን መውሰድ የቻለው ኦሕዴድ ብቻ ነው፡፡

ባጠቃላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ የቀውስ ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆናቸው ከወደቀባቸው ከባድ አደራ አንጻር ተስፋ የሚሰጥ ካቢኔ ይዘው አልቀረቡም፡፡ ካቢኔያቸው ብዙ ትርጉም እንዳይሰጠው የሚያደርገው መሠረታዊ መዋቅራዊ እና የፖሊሲ ማሻሻያ በሌለበት ሀኔታ የተሾመ ካበኔ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ የሀገሪቱ ውስብስብ ቀውስ ግን ሹመኞችን ከማሸጋሸግ አልፎ የመዋቅር፣ የፖሊሲ እና ርዕዮተ ዐለም ለውጥ እንደሚያሻው ግልጽ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ችግሩ አሁን ይቅርና ወደፊትም በዚህ ረገድ ማሻሻያ እንደሚኖር ጠቅላይ ሚንስትሩ በቂ ፍንጭ አልሰጡም፡፡ እንዲህ አይነት ለውጦች ሳይኖሩ ደሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀይ መስመር ያሏቸውን ሙስና እና የሕዝብ አግልግሎት መጓደልን ለማስተካከል እና ለመቆጣጠር እንደሚቸግራቸው ግልጽ ነው፡፡

የካቢኔ አወቃቀሩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያዊያን፣ ዐለም ዐቀፍ የመብት ተሟጋቾችና ምዕራባዊያን መንግስታት ባጠቃላይ በእሳቸው የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማየት ተስፋ ጥለው የነበሩትን ወገኖች ሁሉ ላሁኑ አንገት የሚያስደፋ ነው የሚሆነው፡፡ [በጉዳዩ ላይ የተዘጋጀ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/kVOpqA52dAQ