[ዋዜማ ሬዲዮ]  በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ተገንብቶ በቅርቡ  ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የአብርሆት ቤተ-መጽሃፍትን የማስተዳደር ሐላፊነት በጊዜያዊነት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊሰጠው መሆኑንና በሚቀጥሉት ቀናት ርክክብ ሊፈፀም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ሰምታለች። 

በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ምክትል ሃላፊ አቶ መሬሳ ሉካሳም ይህንኑ ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

ቤተ-መጻህፍቱን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ በጊዜያዊነት እንዲያስተዳድረው ከውሳኔ የተደረሰው ዩኒቨርሲቲው የረዥም ጊዜ  ልምድና ብቁ የሰው ሃይል ስላለው መሆኑን ያነጋገርናቸው ምንጮቻችን ገልፀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የተመረቀው በሃገሪቱ ግዙፉ እና ከ1.1ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው አብርሆት  የህዝብ ቤተመጻህፍ በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ የህዝብ ቤተ-መጽሃፍትን ከሚያስተዳድረው እና ተጠሪነቱ ለባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከሆነው ከአዲስ አበባ ቤተ-መጻህፍት (ዞን አራት ቤተ-መጻህፍት) ተለይቶ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠበት ምክኒያት “ተቋሙ ወደ 12 የሚጠጉ ግዙፍ የኮሌጅ ቤተ-መጻህፍት ከማስተዳደር ልምዱ እና ይህንን ግዙፍ ቤተ-መጻህፍት ለማስተዳር የተሸለ ነው ተብሎ ስለታመነበት” መሆኑን ምክትል ሃላፊው አቶ መሬሳ ሉካሳ ተናግረዋል፡፡

ቤተ-መጽሃፍቱ ከተመረቀ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው ለአስተዳደሩ፣ ለአይሲቲ ክፍሉ እንዲሁም የቤተ-መጻህፍት ባለሞያዎችን ካለው ሰራተኛ በማምጣት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።፡፡ 

ዩኒቨርሲቲው ቤተ-መጽሃፍቱን የሚያስተዳድረው ግን ለቦታው ብቁ የሚሆኑ እስተዳደሮች እስኪመጡ፣ የአገልግሎጽ ስርዓቱ በሁለት እግሩ እስኪቆም ፣መሟላት ያለባቸው ግብአቶች እስኪሟሉ ሲሆን ይህም ከተከናወነ በኋላ ተቋሙ ለከተማ መስተዳድሩ መልሶ እንደሚያስረክብ የዋዜማ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ስድስት ኪሎ የሚገኘው የአዲስ አበባ ቤተ-መጻህፍት ወይንም በቀድሞው መጠሪያ ስሙ ዞን አራት ቤተ-መጻህፍት በቀጥታ በስሩ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን 79 የህዝብ ቤተ-መፃህፍትን በተዘዋዋሪም  108 የወረዳ ወጣት ማእከል ቤተመጻህፍትን እያስተዳደረ ነው፡፡

መጻህፍት-ቤቱ ካለው ልምድ፣ ከታሪክ ባለቤትነቱ እንዲሁም በውስጡ ካሉት በሞያው ረዥም እድሜ ካስቆጠሩት ሰራተኞቹ አንጻር አብርሆት ቤተ-መጻህፈትን ለማስተዳደር “ብቁ” ሆኖ አለመወሰዱ ቅር የሚያሰኝ ነገር መሆኑን ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ለቤተ-መጻህፍቱ ቅርበት ያላቸው አካላት ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይታወቁ ከነበሩት አንዱ የሆነው የማዘጋጃ ቤት ቤተ-መጻህፍት ከ19 ዓመት በፊት የተዘጋ ሲሆን መጻህፍቱና ንብረቶች ወደ ዞን አራት ቤተመጻህፍት እንዲዛወር ተደርጓል፡፡

በእድሳት ላይ የሚገኘው የከተማው መስተዳደር ህንፃ እድሳቱ ሲጠናቀቅ እንደቀደመው ሙሉ ሳምንት ለህዝብ ክፍት የሚሆን ቤተ-መጻህፍት ባይሆንም በሳምንቱ የእረፍት ቀናት ለህብረተሰቡ ክፍት የሚሆን ለመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ደግሞ ዘወትር አገልግሎት እንዲሰጥ መታቀዱን ስምተናል። [ዋዜማ ሬዲዮ]