state departmentዋዜማ ራዲዮ- የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የስብዓዊ መብት ይዞታ ላይ የተሰማውን ቅሬታ ለማቅረብና ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ ያቀናል።
የአሜሪካ የስብዓዊ መብት ጉዳዮች ሀላፊ ቶም ማሊዋንስኪን ጨምሮ አምስት ተወካዮችን ያካተተ ልዑካን በቀጣዮቹ  ቀናት አዲስ አበባ ይደርሳል።
ከሀምሌ ወር ጃምሮ በአማራ ክልል እንዲሁም ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳውን ህዝባዊ አመፅ ለመፍታት መንግስት የሄደበት መንገድ ችግሩን የሚፈታ አይደለም የሚል እምነት ያለው የአሜሪካ ልዑካን ቡድን በዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ፣እስርና ግፍ በብርቱ እያሳሰበው መምጣቱን ሲገልፅ ቆይቷል።

በቅርቡ ለእስር በተዳረጉት የኦሮሞ ኮንግረስ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና እና በወህኒ እየተሰቃዩ ባሉት ሌሎች የፖለቲካ መሪዎች፣ጋዜጠኞችና የመብት ተከራካሪዎች ጉዳይ ዙሪያም የአሜሪካንን አቋም በማብራራት በሀገሪቱ መሰረተ ሰፊ የፖለቲካ ማሻሻያ እንዲደረግ ለመጠየቅ መታቀዱንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዋዜማ ምንጮች አስረድተዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ታህሳስ 4 ቀን  የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የስብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ጋር ለመመካከር ዝግ ስብሰባ ለማዘጋጀት ማቀዱን  የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ሀሳብ ያካፍላሉ የተባሉ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል አስተያየት ሲጠየቁ ነበር።
የአሁኑ የመጀመሪያ ጉዞ በስብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ የበለጠ የሚያተኩር ሲሆን በፖለቲካ ማሻሻያ ዕቅዶች ዙሪያ ግፊት የሚያደርግ ሌላ ቡድን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ምንጮቻችን ነግረውናል።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ባለው ለዘብተኛ አቋም ሳቢያ ከተለያዩ አካላት ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ የመብት ተሟጋቾች የተለያዩ የማግባባት ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።
በቅርቡ ለዋዜማ አስተያየት የሰጡ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አማካሪ “የዋሽንግተን አስተዳደር የኢትዮጵያን መንግስት ላለማስቆጣት በብዙ ጉዳዮች ላይ ለዘብተኛ አቋም ነበረው፣ ይህ ግን የሚቀጥል አይመስለኝም” ብለዋል።
“ከመጪዎቹ ቀናት ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስድ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይደረጋል። ማሻሻያ ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ ግን ጠንከር ያለ እርምጃ መውስድ አስፈላጊ መሆኑን ከመግባባት ተደርሷል” ይላሉ አማካሪው።