ዋዜማ ራዲዮ- ዛሬ (ረቡዕ) ማምሻውን ከዋይት ሐውስ በወጣው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መግለጫ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅና ሀገሪቱን ወደመረጋጋት ለመመለስ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

በትግራይ የሚደረገው ጦርነት ያስከተለው ስብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን ያወሱት ባይደን እየተፋለሙ ያሉ ወገኖች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ፣ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ኋይሎች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትና ተቋማት ለብሄራዊ እርቅና መግባባት ቅድሚያ ስጥተው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን በማቆም ወደ ውይይትና የጋራ ሀገራዊ መግባባት መድረስ አስፈላጊ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አበክረው መክረዋል።


በትግራይ ያለው የስብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑንና በኢትዮጵያ ከአርባ አመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የረሀብ አደጋ በማንዣበቡ ሁሉም ተፋላሚ ሀይሎች የሰላም መንገድ እንዲከተሉ፣ ዕርዳታ ያለምንም መስተጓጎል ለተቸገሩት እንዲደርስ መንግስት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አሜሪካ ከአፍሪካ ህብረትና ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላትም ባይደን አስታውቀዋል። ለዚሁ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፊልትማን በዚህ ሳምንት ወደ ቀጠናው እንደሚመጡ የፕሬዝዳንት ባይደን መግለጫ ጠቁሟል።

አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሁሉንም ሀገሮች ፍላጎት ያማከለ ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት እንዳላትም አመልክተዋል።

ፊልትማን ከቀናት በፊት የአካባቢውን ሀገራት ጎብኝተው ከቀጠናው መሪዎች ጋር ቢነጋገሩም ከኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች በኩል በጎ ምላሽ አላገኙም ነበር። ይህን ተከትሎም አሜሪካ በሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማበረታቻ ማዕቀብ ጥላለች። [ዋዜማ ራዲዮ]