ዋዜማ ራዲዮ- የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፣ ዳኞች በሙሉ ሌብነት ላይ የተሠማሩ እንደሆኑ አድርገው ለተናገሩት ያልተገባ ንግግር ማስተካከያ እንዲያደርጉ በጽሁፍ ባወጣው መግለጫ መጠየቁን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግቧል።

የክልሉ ዳኞች ማኅበር ጠቅላይ ሚንስትሩ “አንደኛ ደረጃ ሌቦች ዳኞች ናቸው” በማለት መናገራቸው፣ በአገሪቱ ዳኞች እና በጠቅላላ በዳኝነት ተቋሙ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ያላስገባ ንግግር ነው ሲል ወቅሷል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በሌብነት ተግባር ላይ የተሠማሩ ውስን ቁጥር ያላቸው ዳኞችን ብቻ ለይተው መውቀስ ይገባቸው እንደነበር የጠቆመው ማኅበሩ፣ እሳቸው ግን ልዩ ጥናት እና ማስረጃ በሚፈልግ ጉዳይ ላይ ሁሉንም ዳኞች በጅምላ በሌብነት መፈረጃቸው ተገቢ ያልሆነ ፍረጃ ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጧል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ሕዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን አመኔታ የሚያሳጣ፣ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒ እንዳይሆን የሚያደርግ፣ የፍርድ ቤቶችን ገጽታ የሚያበላሽ፣ ሙያቸውን አክብረው የሚሠሩ ዳኞችንና ቤተሰባቸውን የሚያሸማቅቅና ሞራላቸውን የሚነካ፣ ገለልተኛ የዳኝነት አካል መኖሩን አምነው ሙዓለ ንዋያቸውን በአገሪቱ ማፍሰስ የሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች በፍትህ ሥርዓቱ አመኔታ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ እንደሆነ ማኅበሩ በመግለጫው አብራርቷል።