Members of NMA at the founding congress
Members of NMA at the founding congress

ዋዜማ ራዲዮ- የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የተባለ አዲስ ተቃዋሚ ብሄርተኛ ድርጅት ከሁለት ሳምንት በፊት በርካታ ሰዎች በተገኙበት በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳር ተመስርቷል፡፡ ንቅናቄው የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑትን ወጣቱን ዶክተር ደሳለኝ ጫኔን ሊቀመንበሩ አድርጎ መርጧል፡፡ ሊቀመንበሩ በምስረታ ጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር “ንቅናቄው በአማራ ሕዝብ ላይ ሲደርስ ለኖረው ግፍ የተሰጠ መለኮታዊ ምላሽ ነው” በማለት የገለጹት ሲሆን በመላው ዐለም የሚገኙ የብሄሩ ተወላጆችም ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አድርገዋል፡፡

የአማራ ብሄርተኝነት “ሀ” ብሎ የጀመረው በ1980ዎቹ አጋማሽ በያኔው “ክልል አራት” በብሄሩ ተወላጆች ላይ በደረሰው ጅምላ ግድያ ሳቢያ በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የሚመራው መላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ሲቋቋም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በርካታ የብሄሩ ተወላጆችም በመአሕድ ስም ለእስር፣ ስቃይ እና ግድያ ተዳርገዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዐመታት ደሞ የአማራ ሕዝብ ባካሄደው ጸረ-መንግስት ተቃውሞ በተለይ በየጎንደር፣ ደብረ ታቦር እና ባሕር ዳር ብዙ የሕይወት ዋጋ ከፍሏል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ የብሄሩ ተወላጆች ከሌሎች ክልሎች በሃይል መፈናቀላቸውም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ በእነዚህ እና በሌሎች ግፊቶች ሳቢያም ባለፉት ዐመታት ቤተ አማራ፣ ዳግማዊ መአሕድ፣ አንድ አማራ፣ አማራ መድህን የሚባሉ የፖለቲካ ቡድኖች የተቋቋሙ ሲሆን በውጭ ያሉ የብሄሩ ተወላጆችም ከአመት በፊት “የአማራ ድምጽ” የተሰኘ ራዲዮ ጣቢያ ጀምረዋል፡፡ እነሆ ሰሞኑን የመአሕድ ቀጣይ የሆነው ብሄርተኛ ንቅናቄ መመስረቱ ደሞ ብሄርተንነቱ ምን ያህል ስር እየሰደደ እንደሄደ አስረጅ ነው፡፡ “አማራ የሚባል ብሄር የለም” ለሚሉ ወገኖችም ብሄርተኞቹ አስረጅ የሚሆን ድርጅት ብቅ ብሎላቸዋል፡፡

እናም አሁን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ምን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊኖረው ይችላል? ለየትኞቹ ብሄርተኛ ድርጅቶች ስጋት ይሆናል? ምን ዐይነት ፈተናዎች እና ዕድሎችስ ይጠብቁት ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡[ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

* * *

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሀገሪቱም ሆነች የአማራ ብሄር ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ባሉበት ወቅት፣ ሆኖም ብሄርተኝነቱ ወደ ፖለቲካ ድርጅት ያድጋል ተብሎ ባልተጠበቀበት ሰዓት ነው ብንል ስህተት አይሆንም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ ካንድ ወር በፊት ከባሕር ዳር ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የአማራ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን እንዳያኮስሰው ምሁራን ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ በተማጸኑ ማግስት ነው እንግዲህ ብሄርተኝነቱ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ይዞ ከተፍ ያለው፡፡

ግፉዓንና ነፍጠኞች

ንቅናቄው የብዙ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች እና ትርክቶች እንዲሁም የተጠራቀመ ቁጭት ውጤት መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ ከ1960ዎቹ የተማሪ ንቅናቄ ጀምሮ የአማራ ብሄር በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ ባህሉንና ቋንቋውን በሃይል የጫነ ጨቋኝ ብሄር ነው፣ ያለፉት ስርዓቶች ተጠቃሚ ነው፣ የአሃዳዊት ኢትዮጵያ አቀንቃኝ፣ ነፍጠኛ እና ትምክህተኛ ነው፣ እንዲሁም ብሄርተኝነቱ ለሀገር ሕልውና አደገኛ ነው የሚሉት ፕሮፓጋንዳዎች ሰለባ ሆኖ መኖሩ ለብሄርተኝነቱ ማደግ ገፊ ምክንያቶች እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡

ባለፉት ሃያ ዐመታት ደሞ ማንነትን መነጠቅ፣ ከፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መገለል፣ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ጥሰት፣ የፖለቲካ ውክልና መሳሳት፣ ከቀዬ መፈናቀል ለመሳሰሉ ድርብርብ በደሎች መጋለጡ የአደባባይ ሚስጢር ከሆነ ቆይቷል፡፡ ባለፉት ሦስት ዐመታት መንግስት ፍትሃዊ ጥያቄ ላነሱ ተቃዋሚዎች የተጠቀመው ሃይል፣ የብሄሩ ተወላጆች መፈናቀል፣ ሕወሃት እና መንግስት የወልቃይት ማንነትን ጥያቄ እና ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ማካለል ጉዳይ የያዙበት መንገድ ለብሄርተኝነቱ ማደግ ብሎም ለንቅናቄው መመስረት እርሾ እንደሆኑ መታዘብ ይቻላል፡፡

በጠቅላላው ላለፉት ሕወሃት/ኢሕአዴግ እና አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ትርክቶች እና እኩይ ድርጊቶች በተቃራኒው ለአማራ ብሄርተኝነት መጎልበት ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል ማለት ይቻላል፡፡ ብአዴንም ቢሆን ሌሎች የአማራ ድርጅቶች እንዳይፈጠሩ እና ብሄርተኝነቱ እንዳይጎለብት ተግቶ በመስራት ነው የሚታወቀው፡፡ ለንቅናቄው ምስረታ እንቅፋት ሳይፈጥር መቅረቱ ግን አንዳንድ ወገኖች የለውጥ አቅጣጫ ይዟል ብለው እንዲያምኑ ያደረገ ይመስላል፡፡ የኦሕዴድን ያህል ይፋ ሳይወጣ ተቃዋሚ ተፈጠረበት እንጅ የአዲሱ ንቅናቄው ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔም በብአዴን ውስጥ የለውጥ ትግል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለአማራ ሕዝብ ሲባል ንቅናቄያቸው ብአዴንን አምርሮ እንደሚታገለውም ነው ሲናገሩ የተደመጡት፡፡

ውልውል በኢትዮጵያዊነትና አማራነት መሀከል

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ በተስፋ፣ በጥርጣሬ፣ በስጋት፣ በተግዳሮት እና ዕድል ታጅቦ ነው ወደ ተቃውሞው ፖለቲካ ጎራ ብቅ ያለው ማለት ይቻላል፡፡ እንደማንኛውም ብሄርተኛ የፖለቲካ ድርጅት ከውጭም ከውስጥም ተቃውሞዎች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ ከውስጥ የአማራ ብሄር ተወላጆች ውልውል ውስጥ ያሉ መሆናቸው አንዱ ችግር ነው፡፡ የአማራው ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር ይላተማል ብለው የሚሰጉ ቀላል አይደሉም፡፡ በርግጥም ብሄርተኝነቱ በኢትዮጵያ አንድነት መቃብር ላይ ቢለመልም ግድ የማይላቸው ብሄርተኞች ብቅ ብቅ እያሉ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እንዲያውም ብሄሩ ላይ ለሚደርሰው መጠቃት ግንባር ቀደም ተጠያቂው የአንድነት ትርክቱ ነው ባዮች ናቸው፡፡

የአማራ ብሄርተኝነትም ሆነ ንቅናቄው ለሀገሪቱ ሕብረ ብሄራዊ አንድነት አደገኛ መሆን አለመሆኑ የሚወሰነው ግን በንቅናቄው ቀጣይ ትርክት ላይ ነው የሚሆነው፡፡ ምናልባት ብሄርተኞቹ ዋና አላማቸው ርዕተ ዐለምን መስበክ ሳይሆን፣ የብሄሩን ሕልውና ማስቀጠል መሆኑን ደጋግመው መጥቀሳቸው ግን አንድነት አቀንቃኞችን ስጋቱን ለማለዘብ ያግዝ ይሆናል፡፡ በአማራ ብሄር ሕልውና ላይ የተጋረጠው አደጋ፣ ለሀገሪቱ ህልውና ጭምር አደገኛ ነው የሚለው የንቅናቄው አቋምም አንድ ማስታገሻ ሊሆን ይችላል፡፡

ከውጭ ሲታይ ደሞ የአማራ ብሄርተኝነት በቀጥታ ከኦሮሞ ብሄርተኝነት ጋር ይላተማል የሚል ውለውል ያላቸውም አሉ፡፡ ንቅናቄው በትርከቱ የሀገሪቱን ጥንታዊ ገናና ታሪክ የሚሰብክ መሆኑ ደሞ ለኦሮሞ ብሄርተኞች መጎርበጡ አይቀሬ ነው የሚሆነው፡፡ በርዕዮተ ዐለሙ ወደፊት የሚያይ ብሄርተኛ ድርጅት መሆንን ትቶ የአማራ ብሄርተኝነትን በጽኑ መሰረት ለማቆም ሲል የኋላ ትርክቶችን ከረር ባለ ቋንቋ እያስተጋባ፣ ከኦሮሞ ብሄርተኝነት ጋር አተካሮ የሚገጥም ከሆነ ብሄርተኞችን ማስበርገጉ ላይቀር ይችላል፡፡

ከፓርቲው አማራ ምን ያተርፋል?

የአማራ ብሄርተኝነት መጠንከር ውሎ አድሮ በአማራ ክልል ነዋሪ በሆኑ ሌሎች ብሄረሰቦች ላይ በተለይም በኦሮሞ ብሄረሰብ ላይ ስጋት ሊደቅን ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች አይጠፉም፡፡ በርግጥ ስጋቱን ተጨባጭ የሚያደርግ እዚህ ግባ የሚባል ፍንጭ እምብዛም አልታየም፡፡ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የአገው ብሄረሰብም በሕገ መንግስት እና በተግባርም ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ብሄረሰቦች መሆናቸውንም እንዲህ ላለው ስጋት አንድ መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ከአማራ ብሄርተኝነት እና ከንቅናቄው መመስረት እነማን ተጠቃሚ ይሆኑ ይሆን? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ምናልባት ብቸኛው ተጠቃሚ የሚሆነው በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ያለው የአማራ ብሄር ተወላጅ እንደሚሆን ነው መናገር የሚቻለው፡፡ ንቅናቄው ደሞ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የብሄሩ ተወላጆች የፖለቲካ ውክልና እና እንደ አስፈላጊነቱ ደሞ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲያሰጣቸው እንደሚታገል ግልጽ አድርጓል፡፡ ምን ያህል እንደሚሳካለት ግን ከአሁኑ መተንበይ የሚቻል አይደለም፡፡ በክልሉ ያለው የአማራ ሕዝብም ቢሆን እንደ ኦሮሞ ብሄር ወጣቶች በኢመደበኛ እና ሕቡዕ አደረጃጀት ለመብቱ ቢታገል ይሻላል? ወይንስ ባንድ ብሄርተኛ ንቅናቄ ስር? የሚለው ጥያቄ ራሱ ገና የሚያወያይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

በንቅናቄው መመስረት ስጋት የሚያድርባቸው ወገኖች ግን በርከት ያሉ እንደሚሆኑ መናገር ይቻላል፡፡ ሕወሃት፣ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች፣ ግንቦት 7 እና የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኝ ሃይሎች ስጋት ከሚሰማቸው ቡድኖች ግንባር ቀደም ተጠቃሸ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ምናባዊ ወይንስ እውነታ መሆኑ ሌላ ጉዳይ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአማራ እና ኦሮሞ ብሄር ትብብር የተሰጠው “ኦሮማራ” የሚባለው ስያሜ ሕወሃትን ያስበረገገ ይመስላል፡፡ በብአዴን እና ኦሕዴድ መካከል ያለውን ግንኙነትም “መርህ አልባ ጉድኝት ነው” በማለት ሲያጣጥለው የነበረው ለዚህ እንደሆነ ነው ብዙዎች የሚያምኑት፡፡ አፍቃሬ-ሕወሃት የሆኑ ድረ ገጾችም ሰሞኑን በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው ብአዴን ሆነ ብሎ ጸረ-ሕገ መንግስት የሆኑ፣ አክራሪ የአማራ ብሄርተኞች እንዲደራጁ ፈቅዷል የሚል ወቀሳ ሲያቀርቡበት ሰንብተዋል፡፡ የንቅናቄው መመስረት በትግራይ ሕዝብ ላይ የተቃጣ እንደሆነም በድረ ገጽ ጽፈው አስራጭተዋል፡፡ ለዚህም እንደ አስረጅ ሊነሳ የሚችለው ምናልባት የንቅናቄው ሊቀመንበር በንግግራቸው ብሄር-ተኮሩ ፌደራላዊ ሥርዓቱን እንደገና ለማዋቀር እንደሚታገሉ መጥቀሳቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ንቅናቄው እንደ ንግስት ይርጋ እና ደመቀ ዘውዱ ያሉ የወልቃይት አማራ ማንነት መብት ግንባር ቀደም ተሟጋቾችን ለብሄርተኝነቱ እንደ ምልክትነት መጠቀሙም ለሕወሃት መራራ ክኒን መሆኑም አይካድም፡፡

አማራና ሌሎች

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሕወሃትንም ሆነ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ውልውል ውስጥ መክተቱም አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ብሄርተኞች አዲሱ ንቅናቄ የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኝ ሃይሎችን ሊገዳደርልን ወይም ሊከፋፍልልን ይችላል የሚል ስሌት እንዲይዙ ሊያደርጋቸው ይችላልና! እናም ንቅናቄው ከብአዴን፣ ከሕወሃት እና ከኦሮሞ ብሄርተኛ ድርጅቶች ጋር ወደፊት የሚኖረው መስተጋብር የትኛው ስሌት ያመዝናል? በሚለው ይወሰናል፡፡

የሕወሃት መሪዎች በቅርቡ መቀሌ ላይ ባደረጉት ስብሰባ “ሞተው ተቀብረዋል ያልናቸው አስተሳሰቦች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በይፋ ሲንጸባረቁ እየሰማን ነው” በማለት በቁጭት ሲናገሩ መደመጣቸው በጠቅላይ ሚንስትር አብይ ፋና ወጊነት ገና ዳዴ እያለ ያለው የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ትርክት ምን ያህል ስጋት እንደሆነባቸው ቁልጭ አድርጎ ነበር ያሳየው፡፡ ከዚህ አንጻር ታዲያ ምናልባት የህወሃት ብሄርተኞች የአማራ ብሄርተኝነትን በተወሰነ ደረጃ ይፈልጉት ይሆን? ብለን ብንጠይቅ ስህተት አይሆንም፡፡

የአርበኞች ግንቦት 7 ም መሪዎችም የአማራውን ንቅናቄ መመስረት እንደሰሙ ፈጥነው ነበር ለድርጅታቸው አደጋ መሆኑን የገለጹት፡፡ የንቅናቄው ደጋፊዎችበበኩላቸው እንደ ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ካሉ ብሄርተኛ ድርጅቶች ጋር የትግል አጋነት የመሰረተ ድርጅት እንደምን የብሄር አደረጃጀትን እንደ አደጋ ለመቆጠር ምን ሞራል አለው? ሲሉ ነው ጥያቄ-አዘል ትችት ነው ያቀረቡበት፡፡ የሀገር ውስጡ ፖለቲካ ካልተቀየረ በስተቀር ይሄ ቅራኔ የብሄሩን ተወላጆች መከፋፈሉ አይቀርም፡፡ ቀደም ሲልም በሰሜኑ ክፍል በመንግሥት ሠራዊት ላይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ የብሄሩ መብት ተሟጋቾች ጥቃት የሚያደርሱት ዱር ቤቴ ያሉ የአማራ ብሄር ተወላጅ ታጋዮች ናቸው ሲሉ ሌሎች ደሞ የለም፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች ናቸው እያሉ ሲወዛገቡ እንደነበርም አይረሳም፡፡

የአማራ ብሄርተኛ ድርጅት መቋቋም ከሚገባው ጊዜ በላይ ዘግቷል የሚሉ ወገኖች ያሉትን ያህል፣ በትክክለኛው ወቅት መመሰረቱን የሚገልጹም አሉ፡፡ የሆነው ሆኖ በመጣበት ጊዚ ራሱን የመአሕድ ወራሽ አድርጎ ማቅረቡን እያየን ነው፡፡ ይህን የታዘቡ አንዳንድ ወገኖችም ንቅናቄው ከወዲሁ የራሱ ማንነት ያለው፣ የአዲሱ ትውልድ ብሄርተኛ ድርጅት አድርጎ ራሱን ቢያቀርብ ይሻለው እንደነበር ምክር-አዘል አስተያየት ሲሰጡ ይሰማሉ፡፡ ንቅናቄው ከተሳካለት በድጋፍ መሰረቱ ከኦሮሞ ብሄርተኝነት ቀጥሎ በሀገሪቱ ሁለተኛው ጠንካራ ድጋፍ ያለው ብሄርተኛ ሃይል የመሆን ዕድል አያጣም፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ ]

https://youtu.be/l8abxrKQ2U8