ዋዜማ ራዲዮ- የአማራ ባንክ መቋቋምን ተከትሎ ከ1987 ዓ.ም ወዲህ የባንኩ ዘርፍ ሶስተኛውን ማዕበል እያስተናገደ ነው። የመጀመሪያው የ1987ቱን ህገ መንግስት ተከትሎ የግል ባንኮች መጀመርና መስፋፋት በዘርፉ አዳዲስ የውድድር መንፈስ ይዞ ብቅ ማለቱ ይታወሳል። ሁለተኛው የባንክ ዘርፉ አብይ ክስተት (ማዕበል) 2000 ዓም በኋላ የተቋቋሙና በስርጭትም ሰፋ ብለው የታዩት ባንኮች ይዘውት የመጡት ፉክክር ነው። ሶስተኛው የባንኮች ብርቱ የፉክክር ዘመን ባለፉት ሶስት ዓመታት ከወለድ ነፃ፣ ማይክሮ ፋይናንስና የቤቶች ባንኮች መስፋፋትን ተከትሎ የተጀመረው ነው።
22ኛ የኢትዮጵያ ባንክ ሆኖ ሰኔ 11 2014 ዓ.ም በይፋ ስራ የጀመረው አማራ ባንክ የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ውድድር ወደ አዲስ ምዕራፍ እየወሰደው መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ዋዜማ ራዲዮ አሰባስባለች። ባንኩ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ የተቀላቀለበት 6.5 ቢልየን ብር ካፒታል በግሉ ዘርፍ ከተደረጉ የፋይናንስ ዘርፍ የጅማሮ ኢንቨስትመንት ቀዳሚ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የበጀት አመቱ ሁለተኛ ሩብ አመት የሪፖርት መጽሄት እንደሚያሳየው የመንግስቶቹን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ባንኮች ካፒታል 167.1 ቢሊየን ብር መድረሱን ያሳይና ከዚህ ወስጥ 81 ቢሊየን ብር ካፒታሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የልማት ባንክ ሆኖ ቀሪው 86 ቢሊየን ብር የግል ባንኮች መሆኑን ይጠቅሳል። አማራ ባንክ ከግል ባንኮቹ ጠቅላላ ከፒታል ስምንት በመቶውን ያክል ይዞ ነው ስራ የጀመረው።
ብሄራዊ ባንክ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲጠቀምበት በነበረው ህግ የባንክ መመስረቻ ካፒታል 500 ሚልየን ብር ሲሆን ይህ የካፒታል መጠን ከዚህ በኋላ አዲስ ለሚመሰረት ባንክ ጥቅም ላይ እንደማይውልና በጥቂት አመታት ውስጥም ስራ ላይ ያሉ የግል ባንኮች ካፒታላቸውን ወደ 5 ቢሊየን ማሳደግ እንዳለባቸው ግዴታ ተቀምጦባቸዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደተስተዋለው ብዙ በምስረታ ላይ የነበሩ ባንኮች የ500 ሚልዮን ብሩን መነሻ ካፒታል ማሟላት አቅቷቸው ምስረታቸው መክኖ ያውቃል።
የአማራ ባንክ የማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ታምሩ ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት በ70 የባንክ ቅርንጫፎች ስራውን የጀመረው አማራ ባንክ እስከ ሰኔ 30 2014 አ.ም ባቀደው መሰረት 100 ቅርንጫፎችን ከፍቷል። ብዙ የግል ባንኮች 100 ቅርንጫፍ ለመድረስ ቢያንስ አመት ወስዶባቸዋል።
“በዘርፉ ላይ መነቃቃትን እየፈጠርን እንደሆነ እናስባለን ይህም የተለያዩ ባንኮች እየወሰዱት ባለው እርምጃ ሊታይ ይችላል።” ብለውናል አቶ አስቻለው ።
ዋዜማ ራዲዮ ያደረገችው የዘርፉ ቅኝት እንደሚያሳየውም የአማራ ባንክ መመስረቱን ተከትሎ የንግድ ባንኮች ከሰራተኛ ደሞዝ ከማስተካከልና ጥቅማ ጥቅም ከመስጠት ጀምሮ አዳዲስ ፈተናውን የመቋቋሚያ መላ እየቀየሱ ነው።
መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አንስቶ ነባር የብድር ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካታ ሰራተኞች ለቀው አማራ ባንክን እንደተቀላቀሉ መረዳት ችለናል።
በተለይ የብድር ባለሞያዎች ሲለቁ በነሱ አማካኝነት ነባር የባንኩን ደንበኞች ይዘው መሄዳቸው የተለመደ በመሆኑ ባንኩ በወለድ እና በውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ላይ ተጽእኖው ቀላል አይደለም።
“ከባንኩ ልምድና እድሜ ጠገብነት አንጻር አዲስ ባንክ ሲመሰረት ከንግድ ባንክ ሰራተኛ መውሰዱ አዲስ ነገር አይደለም” ያሉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የንግድ ባንክ የስራ ሀላፊ “የአማራ ባንክ ከሌሎች ባንኮች አንጻር ግዙፍ ከመሆኑ ውጭ በቅርቡ ስራ የጀመረው ጸሀይ ባንክም ከንግድ ባንክ ሰራተኞችን ወስዷል” ብለውናል።
“ይህ ከኛ ሰራተኛ መቀነሱን ብቻ ሳይሆን ለገበያው የምናበረክተውንም የሰው ሀይል ያሳያል” የሚሉት ሀላፊው “ አሁን ላይ ትኩረታችን ከስር ያሉ ሰራተኞችን እያበቃን ወደ ሀላፊነት ማምጣትና አዳዲስ ሰራተኞችን መተካት ላይ ነው” ብለውናል።
ዋዜማ ራዲዮ ከመረጃ ምንጮቿ መረዳት እንደቻለችውም ንግድ ባንኩ በዚህ አመት 4,300 ሰራተኞችን ለመቅጠር ከተገደደባቸው ምክንያቶች አንዱ በዚሁ ተጽእኖ ምክንያት የለቀቁበትን ሰራተኞች ቁጥር ለማካካስ ነው ።
በቀጣይ አመትም በሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን የመቅጠር እቅድ አለው።በቅርቡም የሰራተኞችን ደሞዝ በ40 በመቶ ለመጨመር የባንኩ ማኔጅመንት መወሰኑን ይህም ከሰራተኛ ማህበሩ ጋር ያላስማማው መሆኑን ተረድተናል። ነባር ሰራተኞች እንዳይለቁ በሚልም የደረጃ እድገት እየሰጠ ይገኛል።
ከንግድ ባንክ ውጭ አቢሲኒያ ባንክ ለሰራተኞቹ ደሞዝ እንደሚጨምርና ጉርሻ (ቦነስ) እንደሚሰጥ ለሰራተኞቹ በደብዳቤ ገልጿል።አቢሲኒያ ባንክ እስካሁን ባለው መረጃ የፋይናንስ ዘርፉ ከፍተኛ ደሞዝ ከፋይ ሲሆን አሁንም የደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ውድድሩ አካል ሆኗል። ከሶስት እስከ ስድስት ወር ጉርሻ (ቦነስ) ከእርከን እና ደሞዝ ጭማሬ ጋር ለሰራተኞቻቸው ለማቅረብ የተዘጋጁ ባንኮች እንዳሉም ሰምተናል።
ለአማራ ባንክ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በርካታ የሰው ሀይል ያስረከበው ዳሽን ባንክ የበጀት መዝጊያውን ተከትሎ እንደ ሰራተኞች የስራ አፈጻጸም እስከ አምስት ወር ደሞዝ የሚደርስ ጉርሻ (ቦነስ) ለመክፈል የመዘጋጀቱ መነሻም የውድድር ስጋት መሆኑን ከባንኩ ምንጮቻችን ሰምተናል።
የአመት ማለቂያ ላይ ጉርሻ (ቦነስ) መክፈል በባንኮች ዘንድ የተለመደ ቢሆንም በችግር ውስጥ ባለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባንኮች እያደረጉ ያሉት ፉክክር በዘርፉ እየተካረረ የመጣውን ውድድር አመላካች ነው።
የአማራ ባንክ የማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ ዳይሬክተር አቶ አስቻለው እንዳሉንም ከባንኩ ከ180 ሺህ በላይ ባለ አክስዮኖች 50 በመቶው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው ።ባንኩ አዲስ አበባ ዋነኛ የደንበኞቹ መሰረትም ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ነው። የኢትዮጵያ ባንኮች ካሏቸው ሙሉ ቅርንጫፎች 35.5 በመቶ በአዲስ አበባ ብቻ እንዳሉ የብሄራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል ።
የአማራ ባንክ 20 በመቶ ባለ አክስዮኖች በአማራ ክልል ፣ 30 በመቶው ደግሞ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ነዋሪዎች ናቸው። ከግል ባንኮች የአማራ ክልልን የባንክ ገበያን አቢሲኒያ እና አባይ ባንክ የሚፎካከሩበት ሆኖ ቆይቶ ነበር። በተለይ ባጫ ጊና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ ባንኩ በክልሎች ላሉ ተፈናቃዮች የ100 ሚሊየን ብር እርዳታን ሲያከፋፍል ለአማራ ክልል አነስተኛ ገንዘብ ደርሶታል በሚል የተቃውሞ ዘመቻ የባንክ ሂሳብን ወደ ሁለቱ ባንኮች የማዞር አዝማሚያ ነበር። አሁን ደግሞ አማራ ባንክ ሌላ የክልሉ ተወዳዳሪ ሆኗል።
“ባንኮችን በዚህ ደረጃ ለውድድር የሚያበቃ ነገር መከሰቱ በመልካም ጎኑ የሚታይ ነው” የሚሉት የብሄራዊ ኢኮኖሚ እቅድ ባለሙያው አቶ ጌታቸው አስፋው ናቸው። ይህም የውጭ ባንክ ቢገባ በዘርፉ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ከባድ ውድድር ከወዲሁ የሚጠቁም ሆኖ በመልካም ጎኑ ቢነሳም ግን የንግድ ባንኮች በተለይ በሚከተሉት የወለድ ምጣኔ አሰራር ሳቢያ እያጋበሱት ካለው ትርፍ አንጻር አሁን ላይ እንከፍላለን ያሉት ቦነስ እና እንጨምራለን ያሉን ደሞዝ ያን ያክል የሚደንቅ አይደለም ይላሉ አቶ ጌታቸው።
የኢትዮጵያ ባንኮች ለአስቀማጮቻቸው ከዋጋ ንረት በእጅጉ ያነሰ ወለድ በመክፈል ይተቻሉ። በአማካይ 35 በመቶ በሆነ የዋጋ ንረት ባንኮች ለአስቀማጮች 7 በመቶ ብቻ ወለድ በመክፈል ተበዳሪዎች ከዋጋ ንረት በታች ብድር እየሰጡ የተጋነነ አትራፊ እንዲሆኑ ሲያደርጉም ይታያል።
የብሄራዊ የኢኮኖሚ እቅድ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ባንኮች አሁን ለፉክክር ከሚጠቀሙበት መንገድ ይልቅ በወለድ ምጣኔ እና ተገቢውን የስጋት ትንተና በማድረግ ለብዙው ማህበረሰብ ብድር በማቅረብ እንዲሁም በአገልግሎት ጥራት ቢወዳደሩ ይሻላል ይላሉ።
ምክንያቱም ይላሉ ባለሙያው ኢትዮጵያ ውስጥ የአክስዮን ገበያን የመሰሉ የፋይናንስ ገበያዎች እየተለመዱ ሲመጡ በማያዋጣ ወለድ ገንዘብ ማስቀመጥን ማንም ስለማይመርጥ ባንኮች ከወዲሁ የሚወዳደሩበትን መንገድ ሊያስቡበት ይገባል ባይ ናቸው አቶ ጌታቸው። [ዋዜማ ራዲዮ]