Ethiopian Cabinet meeting -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ከተመረጡ ተሸከርካሪዎች ላይ በሂደት የሚቀንስ እና የሚያስቀር የውሳኔ ሃሳብ ታኅሳስ 20፣ 2014 ዓ.ም በተካሄደው ሦስተኛው የሚንስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አጽድቋል።

የመንግሥት የነዳጅ ድጎማን የማንሳት እቅድ እንዳለ ሆኖ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ በነዳጅ ዋጋ መሸጫ ታሪፍ ላይ ተደጋጋሚ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የፈጠረ ሲሆን፣ በሕዝቡ ዘንድም ምሬትን አስከትሏል፡፡ (ይህ ዘገባ ከተጠናቀረ በኋላ፣ መንግሥት ከግንቦት 1፣ 2014 ዓ ም ጀምሮ በነዳጅ ዋጋ ላይ  አዲስ ጭማሪ አድርጓል።

ለአብነትም፣ ባንድ ሊትር ቤንዚን ላይ 5 ብር 11 ሳንቱም የተጨመረ ሲሆን፣ በጭማሪው መሠረት 31 ብር ከ71 ሳንቲም የነበረው አንድ ሊትር ቤንዚን ወደ 36 ብር ከ82 ሳንቱም አሻቅቧል። መንግሥት አዲሱን የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ የጨመረው፣ ለነዳጅ የሚያደርገውን የ82 በመቶ ድጎማ ባላነሳበት ሁኔታ ነው።

መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እና ድጎማውን ለማንሳት በምክንያትነት የሚያነሳው ለበርካታ ዓመታት በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያወጣ በተጠቃሚው ላይ የሚወድቀውን የዋጋ ጫና ወጪ ሲደጉም መቆየቱ ለከፍተኛ ወጭ ስለዳረገው እንዲሁም ሕገወጥ ነጋዴዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባውን ነዳጅ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገራት በማሸሽ በተሸለ ዋጋ እየቸረቸሩት መሆኑን ነው።

የነዳጅ ድጎማ መነሳት አብዛኛውን ፍጆታዋን ከውጭ ለምታስገባው ወደብ አልባዋ አገር  የአውሮፕላን፣ የመርከብ፣ የሕዝብ እና የእቃ ጫኝ ትራንስፖርት ዋጋ በከፍኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ያድርገዋል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስጋታቸውን ሲሰነዝሩ ይሰማሉ፡፡

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የፓርተነርሽፕና ኮምንኬሽን ባለሙያ እና የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶ/ር ስሜነህ በሴ፣ መንግሥት ውሳኔውን በድጋሚ ካላጤነው ማኅበራዊ ቀውስ ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ለዋዜማ ገልጸዋል።

እንደ ሚንስተሮች ምክር ቤት ውሰኔ የነዳጅ ድጎማውን የማንሳቱ ሂደት በመጭው ሐምሌ የሚጀምር ሲሆን፣ ድጎማው ለግሉ ዘርፍ በየሦስት ወሩ 25 በመቶ እየተነሳ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚያልቅ ይሆናል። ለመንግሥት ተሸከርካሪዎች ደሞ 10 በመቶ በየስድስት ወሩ እየተነሳ፣ በአምስት ዓመት ከድጎማ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው የዜጎች የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ በተዳከመበትና የዋጋ ንረቱ ባሻቀበበት በዚህ ወቅት ገበያው አስከሚረጋጋ ድረስ የነዳጅ ድጎማ መነሳት የለበትም ባይ ናቸው። የነዳጅ ድጎማ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ እየናረ ለመጣው የማዳበሪያ ዋጋ ድጎማ በማድረግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በገበሬው ምርት ማካካስ እንደሚሻል ዶ/ር ስሜነህ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዶ/ር ስሜነህ ጨምረውም፣ ውሳኔው አሁን ካለው የዋጋ ጭማሪ በላይ ነገ ተነገ ወዲያ የሚያስከትለው ተጨማሪ የዋጋ ንረት እና የዋጋ ውድነቱ የሚፈጥረው ማኅበራዊ ቀውስ ሊታሰብበት እንደሚገባ ወይም ነጋዴዎች በውሳኔው ሳቢያ ካሁኑ ነዳጅ በመደበቅ ሰው ሰራሽ ችግር እንዳይፈጥሩ ቢያንስ ዓለማቀፍ ገበያው እስኪረጋጋ መንግሥት ድጎማውን ቢቀጥል እንደሚሻል መክረዋል። 

የፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ተመራማሪው ዶ/ር ክፍሉ ገደፌ ሞላም፣ ተመሳሳይ ሃሳባቸውን ለዋዜማ አጋርተዋል። በአርባ ምንጭ ዩንቨርሰቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር መብራቱ አለሙም፣ የነዳጅ ድጎማ ከተነሳ ወንጀል እና ሥርዓተ አልበኝነት ሊንሰራፋ ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

የኑሮ ውድነት እና አስፈላጊ የመንግሥት የፖሊሲ ምላሾች

በአሁኑ ጊዜ በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚስተዋለው ከመጠን ያለፈ የዋጋ ጭማሪ፣ የሸማቾችን የመግዛት አቅም በማዳከም የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ይገኛል። መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ አፋጣኝ ርምጃ ካልወሰደ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል በማለት የዘርፉ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው።

የየካቲት 2014 ዓ.ም ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ33.6 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ41.9 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ የማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡ የሚያዚያ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ደሞ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ጋር ሲነጻጸር የ36.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። አጠቃላይ የዋጋ ንረቱ ባለፈው መጋቢት 34.7 በመቶ ነበር። የምግብ ዋጋ ብቻ በ42.9 በመቶ ጨምሯል።

የመንግሥት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲና ከአንድ ዓመት በፊት ወደሥራ የገባው የአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምን ለውጥ እንድመጣ ዋዜማ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹን ጠይቃለች።

ዶ/ር ስሜነህ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና የአስር ዓመት የልማት ዕቅዱ በታሰበው መንገድ ላለመሄዳቸው ማሳያው ከፍተኛው የዋጋ ንረት እንደሆነ ይናገራሉ። የዋጋ ንረቱ ባሁኑ ወቅት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ብቻ ሳይሆን፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ጭምር እየተፈታተነ መሆኑን ዶ/ር ስሜነህ ተናግረዋል። ምሁሩ ጨምረውም፣ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ ችግሩ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከተፈጠሩ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ጋር የተያያዘ መሆኑን መንግሥት አምኖ መቀበል አለበት ባይ ናቸው።

አገሪቱ ገና ከሰሜኑ ጦርነት ባላገገመችበት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ ተጽዕኖ በበረታበት፣ ድርቅ በቀጠለበት እና የአገር ውስጥ ምርት በተዳከመበት በዚህ ጊዜ፣ የወጪ ንግድን ለማበረታታት በሚል የብርን የመግዛት አቅም ከጊዜ ጊዜ የማዳከሙ ውሳኔ የዋጋ ንረቱን ይበልጥ እንዳባባሰው እና “በእሳት ላይ ጭድ የመጨመር” ያህል እንደሆነ ዶ/ር ስሜነህ ያስረዳሉ።

ችግሩን ለማቃለል መንግሥት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚባሉ እና ምርትና እሴት ሊጨምሩ የሚችሉ ዘርፎችን ለይቶ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ናቸው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ለመቀነስም፣ የፖሊሲ እና አስተዳደራዊ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ባለሙያው አስተያየታቸውን ለዋዜማ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል በብሄራዊ ባንክ እየተወሰዱ ያሉ የትኛውም ዓይነት የፊስካልና የገንዝብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች የሚፈለገውን ለውጥ እያመጡ አለመሆኑን እና የግብር አሰባበሱ ፍትሃዊ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ መንግሥት ጠንካራ ፊስካል ፖሊስ መተግበር እንደሚጠበቅበት ዶ/ር ስሜነህ ጠቁመዋል።

ዶ/ር ስሜነህ ከኑሮ ውድነቱ ጋር አያይዘው ያነሱት ሌላው ችግር ደላሎች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ሚና መስፋቱን ነው። አምራቾች ያመረቱት ምርት ተጠቃሚዎች ዘንድ በተመጣጣኝ ዋጋ ሳይደርስ መኻል ላይ ደላሎች እየተቀራመቱት እና ገበያው እንዳይረጋጋ እያደረጉ መሆኑን የሚጠቅሱት ምሁሩ፣ መንግሥት ምርቱ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚዎች እንዲደርስ ምቹ የትራንስፖርት ዘዴ መቀየስ አለበት ብለዋል። ግብር የማይከፍሉ ደላሎች በገበያው ላይ ያላቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ዶ/ር መብራቱም ይጋሩታል። አገሪቱ ቀደም ሲል ስትመራበት በነበረው የገበያ ሥርዓት ምትክ አዲስ የገበያ ሥርዓት አለመዘርጋቱ ገበያውን ለደላላ እንዳጋለጠው እና ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ዶ/ር መብራቱ አብራርተዋል።

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪው ዶ/ር ክፍሉም አሁን በአገሪቱ ያለውን ችግር ለመረዳት መንግሥት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እና የልማት ዕቅዱን እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል። ዶ/ር መብራቱ በበኩላቸው፣ አገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የልማት ዕቅዱ በምን ያህል ደረጃ እየተተገበሩ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።

ባሁኑ ወቅት በገበያው ላይ የሚታየው የመንግሥት ጣልቃ ገብነትነ እና የገበያ ማረጋጋት ሚና የሚፈልገውን ያህል አለመሆኑ እና የነጋዴው ስግብግነትም መጨመሩን የጠቀሱት ዶ/ር መብራቱ፣ መንግሥት በአጋጣሚው ጥቅማቸውን ማስጠበቅ በሚፈልጉ በሸማቾችና በንግድ ተቋማት ውስጥ ያሉ የመንግሥት አካላት ላይ ጠንካራ ርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያለው የቤተሰብ ምጣኔ በግልጽ እንደማይታወቅ የገለጹት ዶ/ር መብርሃቱ፣ የሕዝብ ቆጠራ በወቅቱ ሳይካሄድና ግልጽ የሆነ የስነ ሕዝብ መረጃ በሌለበት በተለይም በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሥራ አጥ ብዛት፣ የጡረተኞችና መስራት ያቆሙ ሰዎች ብዛት፣ በሥራ ላይ ሊውል የሚችለው የሰው ኃይል እና ሌሎችም ሁኔታዎች በግልጽ በማይታወቁበት ሁኔታ መንግሥት የሚያቅዳቸው ዕቅዶች እና የፖሊሲ ርምጃዎች በመረጃ ያልተደገፉ ስለሚሆኑ፣ የፖሊሲ እና የማሻሻያ ውጤቱ ተገማች እንዳይሆን እና ከዚያም አልፎ ትርጉም አልባ እንዲሆን እንደሚያደርጉት ገልጸዋል፡፡

እኝሁ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እንደሚሉት፣ ለአጭር ጊዜ መፍትሄ  የሸማቾች ማኅበራትን ማጠናከር እና ማደራጀት እንዲሁም የደላሎችን ሚና መቀነስ እና አስተዳደራዊና የፖሊሲ ርምጃዎችን በመውሰድ ምርትን በማሳደግ ገበያውን ማረጋጋት የመንግሥት ቀዳሚ ሥራ መሆን አለበት፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]