yuanአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጀት (IMF) የቻይና መገበያያ ገንዘብ ዩዋን ከአለም አምስቱ የመጠባበቂያ ክምችት ገንዘብ አንዱ ተደርጎ እንዲሰራበት ከሰሞኑ ወስኗል ፡፡ IMF ዩዋንን ከ ዶላር ፣ ከዩሮ፣ ከፓውንድ እና ከጃፓኑ የን እኩል የመጠባበቂያ ክምችት እና የመገበያያ ገንዘብ ማከማቻ ውስጥ ወይም በእንግሊዝኛው Special Drawing Rights (SDR) ውስጥ ማካተቱ የቻይና የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ እየጨመረ መሄዱን ያስረገጠ ውሳኔ ነው ተብሎለታል ፡፡

(መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝሩን ያሰማችኋል አድምጡት)

ዩዋን በአራቱ ዋና ዋና የአለምአቀፍ ገንዘብ ድርጅት ክምችት(SDR) ውስጥ መካተቱ በአለም የምጣኔ ሀብት ቅርጽ ላይ የአዲስ ዘመን መባቻ ምልክት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ ፡፡ ቻይናን የመሰለ የአሜሪካ አጋር ያልሆነ አገር ገንዘብ የ IMF መጠባበቅያ ገንዘብ ሲሆን ዩዋን የመጀመርያው ነው ፡፡ ይህ ደግሞ የአሜሪካ አጋር ያልኾነው የአለም ክፍል የኢኮኖሚ ሀይሉ እያደገ መምጣቱን ያሳያል የሚል ግምትም ተሰጠቶታል፡፡

የአለምን ምጣኔ ሀብት መዘውር የያዙት የአለም ባንክ እና የአለም ገንዘብ ድርጅት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካ እና በአጋሮቿ አማካኝነት በኒው ሀምሻየር ዩናይትድ ስቴትስ የተቋቋሙ ድርጅቶች መኾናቸው ይታወቃል፡፡አሜሪካ የዘመናችንን የፋይናንስ እና የገንዘብ ስርኣት ስትዘረጋ ማለትም የአለም ባንክን እና የአለም ገንዘብ ድርጅት እንዲቋቋሙ መንገዱን ያመቻቸችው ካለፈው ስህተቱዋ በመማር እንደነበረም ይነገራል ፡፡ ከአንደኛው የአለም ጦርነት በፊት ከመልከአምድር አቀማመጥዋ የተነሳ ፤ በቅርብ ሊያጠቃት የሚችል ጠላት ስለሌላት እና ሁለቱንም ውቃየኖሶች -ፓስፊክ እና አትላንቲክን ስለምትገዛ የንግድ መስመሮችን ደህንነት ለማስጠበቅ የምትዋጋው ጦርነት አልነበረባትም። ይህም ለአሜሪካ ብልጽግና አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል ፡፡

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያው ላይ ማለትም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 1945 የአሜሪካ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከአጠቃላዩ የአለም ምርት 50 በመቶውን የሚያክል ነበር ፡፡ከእንግሊዞች የበላይነት ማክተም በሁዋላ የተከተለው የአሁኑ የዓለም ስርዓት፤ ቀድሞ ከነበረው በጣም የተለየ ነው፡፡በቆዳ ስፋት ዩናይትድ ኪንግደም የአሁኑዋን አሜሪካ አንድ-ሰላሳኛ ስትሆን- የአንግሊዞቹ የበላይነት ይመነጭ የነበረው በቅኝ ግዛትነት ከያዟቸው ሀገራት በሚገኝ ሀብት ነበር ፡፡

የአሜሪካ የአለም መሪነት ከቅኝ ግዛቱ ታሪክ የሚለየው መሪነቷ የሚመነጨው በኃይል በማስገደድ ሳይሆን ስርኣት በማስቀመጥ ጫና በመፍጠር ላይ የተመረኮዘ በመኾኑ ነው ፡፡ ይህ ማለት ግን ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሌሎች አገራት ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ተቆጥባ ነበር ማለት አይደለም ፡፡

እንደ ተፈጥሮ ህግ ሆኖ አነስተኛ ገቢ ያለቸው ሀገሮች ሁኔታ ሲመቻችላቸው ፤ ከበለጸጉት አገሮች ይልቅ ፈጥነው ያድጋሉ ፡፡ ግሎባላይዜሽን ፤ የአለም ደህንነት እና ነጻ ንግድ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለራሳቸው ታሪክ እንዲሰሩ እድል ፈጠሩ ፡፡ ተፈጥሮአዊው እድገቱ ቀጥሎም በሁሉም ክፍለ አህጉራት ያሉ ሀገሮች በፍጥነት እያደጉ ሲሄዱ ፤ በ1945 ከሌላው የዓለም አገራት ጋር ሲነፃጸር 50 በመቶ ያህል የነበረው የአሜሪካ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በ 2015 ወደ 22 በመቶ ዝቅ አለ ፡፡በመኾኑም ከዚህ እውነታ አሜሪካ ሳትፈልግ ለመቀበል የተገደደችው ሀቅ በሌላ የአለም ክፍል በተፈጠረው እድገት ምክንያት የኢኮኖሚ የበላይነቱዋ እየተሸረሸረ መሄዱን ነው ፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ 2000 እስከ 2008 በነበረው ዓመት በተለምዶ ብሪክስ ተብለው የሚጠሩት ብራዚል ፣ራሽያ ፣ህንድ፣ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ እድገታቸው ከፍተኛ ነበር ፡፡አሜሪካ እና አገሮቹዋን ክፉኛ የመታው በ 2008 የተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ የአለምአቀፉን የገንዘብ ድርጅት በየአገራቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ እንዲታደግ አስገድዶታል፡፡ በአይኤምኤፍ ውስጥ ያለው አድሎአዊ የኾነ ድምጽ የመስጠት ድርሻ ፤አሁን በአውሮፓን ኢኮኖሚ ላይ ያሚታየውን የበላይነት እንዲፈጠር ምክንያት ኾኗል፡፡
ባለፉት አምስት አመታት አውሮፓ ከአይኤምኤፍ እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል ፡፡ከ 2010 ጀምሮ ማሻሻያ ተደርጎ ፤ራሽያ እና ቻይና ያላቸው ድምጽ የመስጠት አቅም በጣም ሲያድግ ፤ ህንድ እና ብራዚልም ከአስሩ ዋና ዋና ሀገሮች ውስጥ ተካተዋል ፡፡

የሰሞኑ ውሳኔ ዩዋን ለንግድ እና ለፋይናንስ አገልግሎት በስፋት በጥቅም ላይ እንዲውል ሲያግዝ ፤ ዩዋንን በአለም የመጠባበቅያ ገንዘብነት እንዲካተት ግፊት ሲያደርግ ለነበረው የቻይና መንግስት ትልቅ ድል ነው ፡፡ ውሳኔው የቻይና መንግስት የፋይናንስ ሴክተሩን ነጻ ማድረጋቸው ማሳያ እንደሆነም ተዘግቧል ፡፡ የዩዋን እንደመገበያያ እና መጠባበቅያ ክምችት ከሚያገለግሉ ገንዘቦች ጋር መቀላቀል ለቻይና ጥቅም ቢኖረዉም የራሱ ችግሮች አሉት፡፡ የሃገሪቱ እድገት በተቀዛቀዘበት በአሁኑ ወቅት ፣ ከምንዛሬ ውሳኔ አንጻር የ አይኤምኤፍን መስፈርት ለማሟላት ቻይና በገንዘቧ ላይ ያላትን ጥብቅ ቁጥጥር አሳልፋ ስለምትሰጥ በኢኮኖሚዋ ላይ የተወሰነ አለመረጋጋት ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል፡፡
የ IMF ማኔጂነግ ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ በዋሽንግተን በሰጡት አስተያየት ይህ ውሳኔ የቻይና ባላስልጣናት የሀገሪቱን የገንዘብና ፋይናንስ ሴክተር ለማሸሻል ባለፉት አመታት ላደረጉት ጥረት እውቅና መስጠት ነው ብለዋል ፡፡ይህ ውሳኔ በ IMF ለመጠባበቅያ ገንዘብ የተቀመጠ ስሌት ወይም special drawing rights መሰረት የዩሮን ተጽእኖ እየቀነሰ መሄድ እና የዩዋንን እየጠነከረ መሔድ ማሳያ ነው ፡፡ ይህም ኾንኖ የአሜሪካን ዶላር ስራ ላይ በመዋል አሁንም ሰፊውን ድርሻ ይይዛል ፡፡ በሌላም በኩል ሀገሮች ከቻይና ጋር በሚያደርጉት ንግድ ዩዋንን በቀጥታ መጠቀማቸው ቻይና ሌላ የውጭ ምነዛሪ ለመግዛት የምታወጣውን ወጭ እና በመሃል ያሉ የፋይናንስ ተቋማትን ተጽእኖ ይቀንስላታል፡፡
በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የንግድ ፖሊሲ ፕሮፌሰር ኤስዋር ፕራሳድ እንደሚሉት ዩዋን የአሜሪካን ዶላር የያዘዉን የውጭ ምንዛሪ መጠባበቅያነት እና መገበያያነት የበላይነት በመጠኑም ቢሆን ይቀንሳል ፡፡ከዚህም በተጨማሪ ዩዋን ከአለምአቀፉ ኢኮኖሚ ጋር የበለጠ መተሳሰሩ የንግድን ልውውጥ በዩዋንም እንዲኾን ስለሚፈቅድ ምእራባውያን ያላቸውን ሰብአዊ መብት በመጣስ በሚከሰሱ ሀገሮች ላይ ማዕቀብ የመጣል አቅም ያሳጣቸዋል።