ዋዜማ ራዲዮ- የትግራይ ክልል ጸጥታ ሃይሎች እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከገቡ ሁለተኛ ቀናቸው ሆኗል፡፡ በክልሉ የሚካሄደው ግጭት ምን መልክ እንዳለው ግን አስተማማኝ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ትናንት በድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው መግለጫ፣ በክልሉ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ከክልሉ ጸጥታ ሃይል ጎን እንደተሰለፈ የገለጸ ሲሆን፣ ፌደራል መንግሥቱ ግን አስተባብሏል፡፡

እነዚህ እና መሰል ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክተው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጺዮን ገ/ሚካዔል (ዶ/ር) ዛሬ፣ ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013፣ በክልሉ ቴሌቪዥን በትግሬኛ ቋንቋ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ደብረ ጺዮን በመግለጫቸው ያነሷቸውን አንኳር ነጥቦች ዋዜማ እንደሚከተለው ተርጉማ አቅርባለች፡፡

ስለ ወታደራዊ ሁኔታዎች

  1. የተወሰነ የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ትግራይ በአድያቦ በኩል ወደ ኤርትራ ገብቷል፡፡ ይህም የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ትግራይን ለማጥቃት ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተባብሮ እየሠራ መሆኑን ነው፡፡ በምዕራብ ትግራይ የሚካሄደው ውጊያ እንደቀጠለ ነው፡፡ በደቡብ ትግራይ በተለይም በአፋር ክልል በኩል ፌደራል መንግሥቱ ተጨማሪ ጦር ሠራዊት እያሰማራ እንደሆነ ተረድተናል፡፡
  2. ትግራይን ለመውረር የሚንቀሳቀስ ማናቸውም ሃይል ግን መውጫ አይኖረውም፡፡ የተከፈተብን ግልጽ ጦርነት ነው፤ ወረራ ነው፡፡ እናም የምናካሂደው ጦርነት ፍትሃዊ እና ሕልውናችን ለማስጠበቅ የምናደርገው ጦርነት ነው፡፡ በእጃችን ያለውን ከባድ ጦር መሳሪያ በቅርብ እና በሩቅ በሚገኙ የትግራይ ጠላቶች ላይ መጠቀም እንችላለን፡፡ ከጦር ግንባር ውጭ በትግራይ ሕዝብ ላይ በየትኛውም ቦታ ጥቃት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ባሉበት ቦታ ለመምታት የሚያስችለን አቅም ፈጥረናል፡፡ ከእንግዲህ ጠላቶቻችን ባሉበት ቦታ ሁሉ ርምጃ እንወስድባቸዋለን፡፡
  3. በትግራይ ክልል የሠፈረው የመከላከያ ሠራዊቱ ሰሜን ዕዝ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ለማስከበር ከክልሉ መንግሥት ጋር ተባባሪ እየሆነ ነው፡፡ የሠራዊቱ ዕዝ ከትግራይ ጎን የቆመው ግን የፌደራል መንግሥቱን ሴራ እና እንቅስቃሴ በመቃወም እንጅ የትግራይ ጸጥታ ሃይል አስገድዶት አይደለም፡፡ በክልሉ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊቱ ከባድ ጦር መሳሪያዎችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ለትግራይ ሕዝብ ደኅንነት እና ጥቅም እንዲውሉ ተደርገዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በእጁ የገባውን ከባድ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞ ለውስጥ እና የውጭ ወረራ የሚመክት ይሆናል፡፡ ከባድ ጦር መሳሪያዎች በእጃችን ስለገቡ እና ሕዝባችንም ጸኑ ዐላማ ስላለው፣ ከአሁን በኋላ በትግራይ ጦርነት ይኖራል የሚል ዕምነት የለንም፡፡

ስለ ወለጋው ጥቃት

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ባለፈው ሳምንት በንጹሃን የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የተፈጸመው ጥቃት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ቀደም ሲል ጠይቋል፡፡ የፌደራሉ መንግሥት ግን ጉዳዩን የአማራ ሕዝብን በማነሳሳት ትግራይን ለማጥቃት አውሎታል፡፡ ለጥቃቱ ተጠያቂ መሆን ያለበት ከጥቃቱ ጥቂት ቀደም ብሎ መከላከያ ሠራዊቱ ከአካባቢው እንዲነሳ ያዘዘው ፌደራል መንግሥቱ እንጅ የትግራይ ክልል መንግሥት ሊሆን አይችልም፡፡

የትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈጸም ስላሉት ጥቃት

ፌደራል መንግሥቱ በሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን እንዲወጡ እያደረገ ነው፡፡ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ባለሃብቶችንም ማሰር ጀምሯል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]