Ambassadors combined 2

  • የዲፕሎማቲክ ስራተኞች ወደ ምድብ ሀገሮቻቸው የትዳር አጋሮቻቸውን ይዘው መሄድ ሙሉ መብት ያላቸው ቢሆንም የትዳር አጋሮቻቸው በመንግስት በጀት ደሞዝ ተከፋይና የመንግስት ተቀጣሪ አድርጎ መውሰድ አዲስ ክስተት ነው

ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ በተለያዩ ሀገራት ከተመደቡ አምባሳደሮች መካካል የተወሰኑት የትዳር አጋሮቻቸውን በመንግስት ተሿሚነት ማስመደባቸውን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ምንጮች ለዋዜማ አጋለጡ።

በዲፕሎማቲክ ምደባ ላይ ወትሮም ቢሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ሲፈጥር መቆየቱን የተናገሩት የመስሪያ ቤቱ ባልደረቦች አሁን የተደረሰበት ደረጃ ግን የገዥውን ፓርቲም ሆነ የሀገሪቱን ጥቅሞች የሚፃረር ነው ብለዋል።

በሰኔ ወር መጨረሻ ከሚንስትርነት ለተነሱና ለሌሎች አስራ ሁለት የገዥው ፓርቲ አባላት የዲፕሎማቲክ ሹመት መሰጠቱን ያስታወሱት ምንጮቻችን በዩናይትድስቴትስ የተመደቡት አቶ ካሳ ተክለብርሀን ባለቤታቸው የኤምባሲው ባልደረባ ሆነው እንዲመደቡ አድርገዋል።
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ወሮ አስቴር ማሞ ባለቤትም እንዲሁ የዲፕሎማቲክ ኮር አባል በመሆን ከመንግስት ደሞዝ የሚቆረጥላቸው ተቀጣሪ ተደርገው አብረው ተጉዘዋል።
ሌላው በተመሳሳይ ባለቤታቸውን ያሾሙ ባለስልጣን በቤልጂየም ብራስልስ አምባሳደር የተደረጉት አቶ እውነቱ ብላታ ሲሆኑ የትዳር አጋራቸውን ለማሾም ከውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጋር ከፍተኛ እሰጥ አገባ እንደነበረባቸውና በኋላም ተፈቅዶላቸው ሚስታቸውን ይዘው መጓዛቸውን ያገኘነው መረጃ  ያመለክታል።

በሰኔ ወር በተደረገው ሹመት በተለይም ብራስልስ የተመደቡት የአቶ እውነቱ ብላታ ሚስቴ በጀት ተመድቦላት ትቅጠር የሚለው ጥያቄ ከሌሎች በተለየ ውድቅ በተደረገ ሰአት በቀጥታ ኦህዴድ ጣልቃ እንደገባበትም ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
የአምባሳደሮችም ሆነ የዲፕሎማቲክ ስራተኞች ወደ ምድብ ሀገሮቻቸው የትዳር አጋሮቻቸውን ይዘው መሄድ ሙሉ መብት ያላቸው ቢሆንም የትዳር አጋሮቻቸው በመንግስት በጀት ደሞዝ ተከፋይና የመንግስት ተቀጣሪ አድርጎ መውሰድ አዲስ ክስተት መሆኑን ያነጋገርናቸው የመስሪያቤቱ ባልደረቦች ይናገራሉ።
በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ወጣት ዲፕሎማቶች ዕድልም የሚዘጋ መሆኑን የሚያስምሩበት አሉ።

በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ከፍ ያለ ቁጥር በሚይዙት የብአዴንና የኦህዴድ አባላት የዲፕሎማቲክ ስራተኞች  መካከል ብርቱ ሽኩቻ መኖሩን የሚናገሩት የመስሪያ ቤቱ ምንጮች በፓርቲ ሽፋን ጥቅም የማጋበስ እንቅስቃሴ ጎልቶ መታየቱንና ይህም የሀገሪቱን ዲፕሎማሲ በብርቱ የሚጎዳ መሆኑን በአሁኑ ስዓት በዲፕሎማትነት ተመድበው የሚሰሩ አንድ ባልደረባ ነግረውናል።
“የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ስራ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይልቁንም በታሪክ ባለን ስኬታማ ስራ ምክንያት ተቀባይነታችን የጎላ ነው። አሁን በተያዘው መንገድ ከቀጠልን ለሀገሪቱም ውርደት ነው”  ይላሉ አስራ ሁለት አመታትን በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሰሩት እኒህ ግለሰብ።

“በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከግልና ከፓርቲ ጥቅም የበለጠ የሀገራቸውን ፍላጎት የሚያስቀድሙ በብቃት ደረጃም የተሻሉ የሚባሉ አንጋፋና ወጣቶች ያሉ ቢሆንም አሁን እየተሄደበት ያለው አስራር ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን ይሆናል” ይላል በአውሮፓ በዲፕሎማትነት ቆይቶ ከሶስት ዓመት በፊት ከመስሪያ ቤቱ የለቀቀ የቀድሞ ባልደረባ።
ቀደም ሲል በአምባሳደርነት አገልግለው ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ዲፕሎማቶችን በአስራ አንድ የተለያዩ የመግስት ተቋማት በሀላፊነት ለመመደብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ስምተናል።

የአገልግሎት ጊዜን ከጨረሱ በኋላ ወደ ሀገር ቤት አለመመለስ በተለይ በበታችና በመካከለኛ የዲፕሎማቲክ ሰራተኞች ዘንድ እየተበራከተ መምጣቱን የሚናገሩት የመስሪያ ቤቶ ባልደረቦች በአጠቃላይ ችግሮች ላይ ከሚንስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በኩል ምላሽ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።
ከሚንስትሩ መልስ ካለገኙ ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሄደው አቤት ለማለት ዕቅድ እንዳላቸው ሰራተኞቹ ይናገራሉ። ዝርዝር የድምፅ ዘገባውን ያድምጡት

https://youtu.be/MCh8cjsiPaw